ፈልግ

የፖምፔይ እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ - በጣልያን  (ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በ2015 የፖምፔይ ማርያም ቤተመቅደስ በጎበኙበት ወቅት) የፖምፔይ እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ - በጣልያን (ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በ2015 የፖምፔይ ማርያም ቤተመቅደስ በጎበኙበት ወቅት) 

የፖምፔይ እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ - በጣልያን

የፖምፔይ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ የሚገኘው በደቡብ ጣልያን ሲሆን ከናፖሊ ከተማ 24 ኪሎ ሜትር ርቆ ነው። ፖምፔይ በመላው ዓለም የሚታወቀው በሚገባ በተጠበቁ ፍርስራሾቹ አማካይነት ነው። ፍርስራሾቹም እ.አ.አ. በ79 ዓ.ም. በቬሱቪዩስ ተራራ ላይ የተከሠተው የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታ ውጤት እንደ ሆኑም ይነገራል። የፖምፔይ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ የመቁጠሪያ እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ በመባልም ይታወቃል። ከቬሱቪዩስ ተራራ ፍርስራሽ 2 ኪሎ ሜትር ርቆ የተሠራው የፖምፔይ ከተማ እ.አ.አ በ1659 ዓ.ም. ታላቅ የወባ ወረርሽኝ አጋጥሞት ነበር። በወረርሽኙም ከከተማው ሕዝብ አብዛኛው እንደ ሞተ ይነገራል። ከወረርሽኙ በፊት ተሠርቶ የነበረው ቤተክርስቲያን እ.አ.አ. በ1740 ዓ.ም. ፈርሶ በቦታው ሌላ ቤተክርስቲያን እንደ ተሠራም ይነገራል። ከፖምፔይ ነዋሪዎች መካከል የባዕድ አምልኮ የሚያካሂዱ ብዙ ሰዎች እንደ ነበሩ ሲነገር ሕዝቡን ይዘርፉና ያሸብሩ የነበሩት ወንበዴዎችም እንደ ነበሩበት ይነገራል። ይሁን እንጂ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ልጆችዋን ምንም ጊዜ አትተዋቸውም። በጣም አስቸጋሪ ስፍራዎችንም በመምረጥ ለርሷ ታማኝ ለሆኑት ሁሉ ድንቅ ነገር እንደምታደርግ አሳይታለች። እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የፖምፔይን ከተማ የራሷ ምርጥ ስፍራ እንዲሆን ለማድረግ እንደ ተዋናይ የተጠቀመችው ባርቶሎ ሎንጎ (1841-1926) የተባለውን ግለሰብ ሲሆን በመጀመሪያ ደረጃ በጣም የማይሆን ምርጫ ይመስል ነበር።

የቫቲካን ዜና

ነገር ግን ከሰይጣን አምልኮ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሰ በኋላ ባርቶሎ ሎንጎ ለቀድሞ ኃጢአቱ ካሣ ለማቅረብ ለድሆችና ለበሽተኞች አገልግሎት የሚሰጥ ያንድ ቡድን አባል ሆኖ ነበር። በዚህ ዐይነት እ.አ.አ. በ1872 ዓ.ም. ከወንበዴዎች ከሚከላከሉት ከሁለት የታጠቁ ሰዎች ጋር ሆኖ ወደ ፖምፔይ ደረሰ። እዚያም በደረሰ ጊዜ የከተማውን ነዋሪዎች የዕውቀት ማነስ፣ ድህነትና የሃይማኖት አልባነትን በማየቱ በጣም አዘነ። በሌላ በኩል ደግሞ ስለ ክርስትና እምነት በነበረው ጥርጣሬ ከራሱም ጋር ይታገል ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳለ እ.አ.አ. በጥቅምት 9 ቀን 1872 ዓ.ም. በቁምስናው ቤተክርስቲያን ደጃፍ ሲያልፍ “መዳን ከፈለግህ የመቁጠሪያን ጸሎት አስፋፋ” የሚል ድምፅ ሰማ። ይህ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ራሷ ለባርቶሎ የሰጠችው የተስፋ ቃል ነበር። ባርቶሎ ሎንጎም በበኩሉ ምንም ሳይዘገይ በቁምስናው የጸሎት ፕሮግራም በማዘጋጀት አያሌ ካህናት ስለ መቁጠሪያ ጸሎት ጠቃሚነት እንዲናገሩ አደረገ። በዚህ ዐይነት በጨዋታ፣ በእሽቅድድም፣ በሎቴሪና በበዓላት አማካይነት የመቁጠሪያ ጸሎት እንዲያስፋፋ ለማድረግ ችሏል።

የመቁጠሪያ ጸሎት የማስፋፋት ተልእኮውን ለማጠናቀቅ እ.አ.አ. በጥቅምት ወር 1873 ዓ.ም. በመፈራረስ ላይ የነበረውን የፖምፔይን ቤተክርስቲያን ማደስ ጀመረ። በታደሰው ቤተክርስቲያን የመቁጠሪያ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕል ለማሳል ወሰነ። እ.አ.አ. በ1875 ዓ.ም. ላሰበው ዓላማ ተገቢ የሆነውን ሥዕል በናፖሊ ከሚገኘው ካንድ ገዳም አገኘ። ታደለች አግሬሊ የምትባል አንዲት የናፖሊ ወጣት ልጅ በማይድን በሽታ ተይዛ ትሰቃይ ነበረች። ነገር ግን እ.አ.አ. በየካቲት 16 ቀን 1884 ዓ.ም. በሕመም ትሰቃይ የነበረችው ልጅና ቤተሰቦችዋ የመቁጠሪያ ኖቬና  ጀመሩ። በዚህ ዐይነት የመቁጠሪያ ንግሥት እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም እ.አ.አ. በመጋቢት 3 ቀን 1884 ዓ.ም. በትልቅ ዙፋን ላይ ተቀምጣ፣ በመላእክት ታጅባ፣ በደረቷ ላይ መለኮታዊ ሕፃን አዝላ፣ በእጅዋም መቁጠሪያ ይዛ ለወ/ሪት ታደለች እንደ ተገለጸችላትም ይነገራል። ታደለችም በእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ውበት ከመደነቋም በላይ እንደ “መቁጠሪያ ንግሥት” ከሕመሙዋ እንድትፈውሳት ጠየቀቻት። እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያምም በበኩሏ “የመቁጠሪያ ንግሥት” ብላ በመጥራቷ በጣም በመደሰት ልመናዋን ለመፈጸም እምቢ እንደማትላት ከገለጸችላት በኋላ ሦስት የመቁጠሪያ ኖቬና እንድትጸልይና የጠየቀችው ሁሉ እንደሚፈጸምላት ነገረቻት። ወ/ሪት ታደለችም እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረቻት መሠረት ሦስቱን የመቁጠሪያ ኖቬና ከደገመች በኋላ ከበሽታዋ በርግጥ እንደ ዳነች ይነገራል። ከበሽታዋ ከዳነች ጥቂት ጊዜም በኋላ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለወ/ሪት ታደለች እንደ ገና በመገለጽ እንዲህ አለቻት፤ “ከእኔ ድጋፍ ለማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ሦስት የመቁጠሪያ ኖቬና በልመና፣ ሦስት የመቁጠሪያ ኖቬና ደግሞ ለምስጋና፣ ማድረግ ይኖርበታል”። ወደ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የሚደረገው የመቁጠሪያ ኖቬና የተጀመረውም በዚህ ዐይነት ነበር።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ፒዮስ 1ዐኛው (1903-1914) የፖምፔይን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስና ወደ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የሚደረገውን የመቁጠሪያ ኖቬና ይደግፉ እንደ ነበረም ይነገራል። አሁን በፖምፔይ የሚገኘው የመቁጠሪያ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ የተመረቀው እ.አ.አ. በ1939 ሲሆን በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛው (1939-1958) ዘመን የቫቲካን ዋና ጸሐፊ በነበሩት በካርድናል ማሊዮኔ ነበር የምረቃው ሥነ ሥርዓት የተከናወነው። በየቀኑ የፖምፔይን ቤተመቅደስ 10,000 የሚያህሉ መንፈሳውያን ተጓዦች እንደሚጎበኙም ይነገራል። ከዚህም ሌላ በዓመት ሁለት ጊዜ ማለትም እ.አ.አ. በግንቦት 8 ቀንና እ.አ.አ. በጥቅምት ወር የመጀመሪያው እሑድ ቢያንስ 100,000 የሚያህሉ መንፈሳውያን ተጓዦች በፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ የሚፈጸመው ታላቅ የቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ተካፋዮች እንደሚሆኑም ይነገራል። እ.አ.አ. በጥቅምት 21 ቀን 1979 ዓ.ም. ወደ ፖምፔይ ቤተመቅደስ በተደረገው ብሔራዊ መንፈሳዊ ጉዞ አጋጣሚ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ (1978-2005) የፖምፔይን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ እንደ ጎበኙም ይነገራል። ቀጥሎም እ.አ.አ. በጥቅምት 26 ቀን 1980 ዓ.ም. ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የፖምፔይ ቤተመቅደስ ዋና ተዋናይ የነበረው ባርቶሎ ሎንጎ ብፁዕ ነው ብለው በይፋ አውጀዋል። በዚያው አጋጣሚ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብፁዕ ባርቶሎ ሎንጎ “የመቁጠሪያ ጸሎት ሰው”፣ “የመቁጠሪያ ጸሎት ሐዋርያ” ነው ብለው ነበር። በዚህ ዐይነት እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለባርቶሎ ሎንጎ “የመቁጠሪያን ጸሎት ልምምድ የሚያስፋፋ ሰው ይድናል” በማለት የሰጠችው ተስፋ ሊፈጸም ችሏል። የመቁጠሪያን ጸሎት ጥቅም እንድንረዳ የፖምፔይ የመቁጠሪያ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን። አሜን።

 

08 May 2020, 13:01