ፈልግ

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር ለመንፈሳዊ ተጓዦች ክፍት ከተደረገ በኋላ፤ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር ለመንፈሳዊ ተጓዦች ክፍት ከተደረገ በኋላ፤ 

በቤተልሔም የቅዱስ ባለወልድ ባዚሊካ መከፈት ፍቅርን እና ተስፋን የጨመረ መሆኑ ተገለጸ።

ክቡር አባ ኢብራሒም ፋልታስ፣ በቤተልሔም የቅዱስ ባለወልድ ባዚሊካ መከፈት በክርስቲያን እና ሙስሊም ማኅበረሰብ መካከል ፍቅርን እና ተስፋን የጨመረ መሆኑ ገለጹ። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በቤተልሔም ከሰማንያ ቀናት በላይ ተዘግቶ የቆየው የባለወልድ ካቴድራል ለነጋዲያን እና አገር ጎብኝዎች ክፍት መደረጉን፣ በቅድስት አገር የባዚሊካው አስተዳደር አማካሪ የሆኑት ክቡር አባ ኢብራሒም ገልጸዋል። አካባቢውን ከፍተኛ ኤኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳጋጠበው የገለጹት አባ ኢብራሒም፣ የቤተልሔም ከተማ በቱሪዝም አገልግሎት የምትታገዝ መሆኑን ገልጸው፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ገቢዋ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ መቆየቱን አስረድተዋል።

የቫቲካን ዜና፤

እሑድ ግንቦት 16/2012 ዓ. ም. በኢየሩሳሌም ከተማ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር ለመንፈሳዊ ተጓዦች ክፍት ከተደረገ በኋላ በቤተልሔምም የባለወልድ ካቴድራል መከፈቱ ለቅድስቲቱ አገር ሕዝቦች መልካም የተስፋ ምልክት መሆኑን ክቡር አባ ኢብራሒም አስረድተዋል። ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ዘጠና ከመቶ አካባቢውን ለሚጎበኙ እንግዶች መስተንግዶን በማቅረብ አገልግሎት የሚተዳደሩ መሆኑን ገልጸው፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ አካባቢው ከተዛመተበት ከሦስት ወራት ገደማ ወዲህ ምንም ዓነት አገልግሎት ማቅረብ ያልተቻለ መሆኑን ክቡር አባ ኢብራሒም አስረድተዋል።

በቅድስት አገር የሚገኙ መንፈስዊ ሥፍራዎች ለነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ክፍት እንዲሆኑ ውሳኔን ያስተላለፉት ሦስቱ የሐይማኖት ተቋማት ተጠሪዎች፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል ክቡር አባ ፍራንቸስኮ ፓቶን፣ የግሪክ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ቴዎፊሎስ 3ኛ እና የአርመን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ኑራን ማኑጂያን መሆናቸው ታውቋል። መንፈሳዊ የንግደት ስፍራዎች ለጎብኚዎች ክፍት በተደረጉበት ጊዜ ወረርሽኙን ለመከላከል ሲባል የተለያዩ ደንቦችም የወጡ መሆኑ ታውቋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ከ2002 ዓ. ም. ጀምሮ የቤተልሔም ከተማ ነዋሪ የሆኑን ክቡር አባ ኢብራሒም፣ አካባቢው ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ እንግዶችን ከማስተናገዱ በተጨማሪ የፍልስጤማዊያን ክርስቲያን እና ማስሊማን ወንድሞች እና እህቶች በሕብረት የሚኖሩበት ሥፍራ መሆኑን አስረድተዋል። የእነዚህ ሁለት ወንዳማማች ሕዝቦች በአካባቢው መገኘት ለኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖን ማበርከቱን ግብጻዊው ክቡር አባ ኢብራሒም አስረድተዋል።

አካባቢው ለጎብኝዎች ክፍት መሆኑ ለአካባቢው ሕዝብ እና ለፍራንችስካዊያን ማኅበር ደስታን የጎናጸፈ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ኢብራሒም፣ በቤተልሔም የባለወልድ ካቴድራልን በጋራ ለሚያስተዳድሩ የግሪክ ኦርቶዶክስ እና ለአርመኒያ ኦርቶዶክስ ወንድሞቻችንም ደስታን የፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል። ሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት ባዚሊክስውን ለመክፈት ዕድል ያገኙት የፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ክቡር አቶ ማሐመድ ሺታዬ ጋዜጣዊ መግለጫ በኋላ መሆኑን ክቡር አባ ኢብራሒም አስረድተዋል።

እስካለፈው ሳምንት ድረስ ሁለቱ መንግሥታት፣ በእስራኤል እና በፍልስጤም መንግሥታት መካከል መልካም ግንኙነት ተፈጥሮ እንደነበር ያስታወሱት አባ ኢብራሒም፣ ከፍልስጤሙ ፕሬዚደንት ከክቡር አቶ ማህሙድ አባስ በኩል በቀረበው ውሳኔ መሰረት ግንኙነቱ መቋረጡን አስታውሰው፣ ባሁኑ ጊዜ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ያለ መሆኑ አስረድተዋል። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የግንቦት ወር የምህለላ ጸሎት በቅድስት ካታሪና ቤተክርስቲያን እና በሌሎች ቁምስናዎች እየቀረበ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ኢብራሒም፣ በቤተልሔም ከተማ የቅዱስ ባለወልድ ባዚሊካ እንደገና መከፈቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች የተስፋ ምልክት መሆኑን ገልጸው፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በከተማው ውስጥ የሞቱት ቁጥር ያልተመዘገበ መሆኑን ገልጸው ይህም የእግዚአብሔር ጥበቃ ነው ብለዋል።                 

27 May 2020, 13:26