ፈልግ

የፋጢማው እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደሰ - በፖርቱጋል የፋጢማው እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደሰ - በፖርቱጋል 

የፋጢማው እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደሰ - በፖርቱጋል

የፋጢማው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ የሚገኘው በፖርቱጋል ሀገር ነው፡፡ የፋጢማው እመቤታችን ቤተመቅደስ የመቁጠሪያ እመቤታችን ባዚሊካ በመባልም ይታወቃል፡፡ ከመቁጠሪያ እመቤታችን ባዚሊካ በተጨማሪ እመቤታችን ለሦስቱ ልጆች ስትገለጽ በተቀመጠችበት በትልቁ የሾላ ዛፍ ስፍራ የተሠራው ሎስ ፐሬን የሚባለው ቤተጸሎት፣ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ሐውልት፣ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሦስቱም ልጆች ማለትም ለሉቺያ ዶስ ሳንቶስ እና ለአጎቱዋ ልጆች ጃቺንታና ፍራንቸስኮ ማርቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በታየችበት ስፍራ የተሠራው ቤተጸሎት ይገኛሉ፡፡ በየወሩ 13ኛው ቀን እ.አ.አ. ከግንቦት 13 ቀን 1917 ዓ. ም. እስከ ጥቅምት 13 ቀን 1917 ዓ. ም. ድረስ ሉቺያና ሁለቱም የአጎቱዋ ልጆች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ያዩአት እንደ ነበር ይነገራል፡፡ በዚያን ጊዜ ሉቺያ የ10 ዓመት ልጅ፣ ፍራንቸስኮ የ9 ዓመት ልጅ፣ ጃቺንታ ደግሞ የ7 ዓመት ልጅ ነበረች፡፡ ልጆቹ ሰለ እመቤታችን አጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም መገለጽ ሲተርኩ ከርሷ መገለጽ በፊት "የሰላም መልአክ" ይታያቸው እንደ ነበረም ይናገሩ ነበር፡፡ ይኸው "የሰላም መልአክ" ድሮም ማለትም ከእመቤታችን ማርያም መገለጽ በፊት እ.አ.አ. በ1916 ዓ. ም. ታይቷአቸው እንደ ነበረም ይተርካሉ፡፡ ሉቺያ በበኩሏ ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም መገለጽ ስትናገር፣ "ማርያም ከፀሐይ የበለጠ ብሩህ ብርሃን ያላት፣ ከመስተዋት ድንጋይ በበለጠ ሁኔታ ብርሃን የምታስተላልፍ፣ በሚያንጸባርቅ ውኃ የተሞላች፣ በሚያቃጥሉ የፀሐይ ጮራዎች የተከበበች ነበረች" ብላለች፡፡

ከሉቺያ ምስክርነት እንደምንረዳው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሦስቱም ልጆች በመጀመሪያ ያለቻቸው "ኃጢአተኞችን ለማዳን ተጋድሎ አድርጉ" ነበር፡፡ በዚህ ዐይነት ወገባቸውን በጣም አጭር በሆኑ ገመዶች ይታጠቁ ነበር፡፡ በጣም ሙቀታማ በነበሩ ቀናትም ውኃ መጠጣት ይተው ነበር፡፡ ብዙ ተመሳሳይ የተጋድሎ ተግባራት ይፈጽሙ እንደ ነበረም ይነገራል፡፡ ከሁሉም እጅግ በጣም ጠቃሚ መልእክት፣ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በፋጢማ የመገለጿ ምስክር ለነበሩ ለሦስቱም ልጆች አበክራ አደራ ያለቻቸው የመቁጠሪያ ጸሎት በየቀኑ እንዲደግሙ ነበር፡፡ ይኸውም ለዓለም ሰላም ሆነ ለግል ሰላምም ቢሆን የመቁጠሪያ ጸሎት ወሳኝ ነገር መሆኑን እንዲረዱ ለልጆቹ ደጋግማ እንደ ተናገረችም ከቤተመቅደሱ ታሪክ ለመረዳት እንችላለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የታየቻቸው ልጆች ዘመዶች ሳይቀሩ በዚያን ጊዜ የአንደኛው ዓለም ጦርነት ተዋጊዎች ነበሩ፡፡ ሉቺያ ዶስ ሳንቶስ ከዓመታት በኋላ እንደ ተረከችው በሁለተኛው የመገለጿ ዕለት ማለትም እ.አ.አ. በሰኔ 13 ቀን 1917 ዓ. ም. እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ጃቺንታና ፍራንቸስኮስ በልጅነታቸው እንደሚሞቱ ተናግራ ነበር፡፡

ሉቺያም በበኩሏ ቶሎ ብለሽ ጃቺንታንና ፍራንቸስኮን ወደ ሰማይ ውሰጂአቸው እንዳለቻትና እመቤታችንም፣ "በርግጥ በቶሎ ወደ ሰማይ እወስዳቸዋለሁ፤ አንቺ ግን በዓለም ላይ ትንሽ ትቆዪአለሽ፡፡ ምከንያቱም ጌታ ኢየሱስ እኔ በዓለም ላይ እንድታወቅና እንድወደድ ይፈልጋልና፡፡ በአንቺም አማካይነት በዓለም ላይ የእኔ እጅግ ንጹሕ ልብ አክብሮት እንዲስፋፋም ይፈልጋልና" እንዳለቻትም ከሉቺያ ምስክርነት ለመዳት ይቻላል፡፡ በርግጥም ፍራንቸስኮስና ጃቺንታ ከእምቤታችን በፋጢማ ከመገለጽ ሁለት ዓመት በኋላ ማለትም እ.አ.አ. በ1919 ዓ. ም. እንደ ሞቱ ከፋጢማው የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ታሪክ ለመረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ  እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀን 2000 ዓ. ም. ፍራንቸስኮስና ጃቺንታ ብፁዓን ናቸው ብለው በይፋ አውጀዋል፡፡ በተጨማሪም ደግሞ እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ (2013- ) ፍራንቸስኮስንና ጃቺንታን ቅዱሳን ናቸው ብለው በይፋ አውጀዋል፡፡ እነዚህም በሰማዕትነት ሳይሞቱ ቅዱሳን የተባሉት የመጀመሪያዎቹ ሕፃናት ቅዱሳን ናቸው፡፡

ስለ ሦስቱ የፋጢማ ምስጢሮች ከተነሣ ደግሞ፣ በአንደኛው ምስጢር እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሦስቱም ልጆች የገሃነመ እሳትን አሰቃቂ ሁኔታ እንዳሳየቻቸው መስክረዋል፡፡ በሁለተኛው ምስጢር ደግሞ ስለ አንደኛው ዓለም ጦርነት መጠናቀቅና ስለ ሁለተኛው ዓለም ጦርነት መጀመር እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሦስቱም ልጆች ነግራቸዋለች፡፡ በተጨማሪም፣ በሁለተኛው ምስጢር ራሺያ ለእመቤታችን ማርያም እጅግ ንጹሕ ልብ የተለየ እንዲሆን እንደምትፈልግም ነግራቸዋለች፡፡ ብዙዎቹ እንደሚገምቱት ይህንን የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያምን ምኞት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ. በመጋቢት 25 ቀን 1984 ዓ. ም. ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ይኸውም የተባበሩት የሶቪየት መንግሥታት እ.አ.አ. በታህሳስ 26 ቀን 1991 ዓ. ም.  ከመበታተናቸው በፊት ለመላው ዓለም ለራሺያም ጭምር ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን በመስጠት ነበር፡፡ የፋጢማ የሦስተኛው ምስጢር በቫቲካን ተደብቆ የቆየ ሲሆን አንድ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከሌሎች ብዙ ጳጳሳትና ካህናት ጋር በመስቀል ሥር በተራራ ላይ በወታደሮች እንደሚገደሉ ይናገር ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ሦስተኛውን ምስጢር እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀን 1981 ዓ. ም. ቱርካዊው ታጣቂ፣ መሐመት ዓሊ፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስን ለመግደል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረገው ሙከራ ጋር ታያይዘዋለች፡፡ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ራሳቸው ከግድያው ሙከራ ሕይወታቸውን የጠበቀችው የፋጢማው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ነበረች ተናግረዋል፡፡ ይኸውም እርሷ በመገለጽ የጥይቱ መርዝ እንዲከሽፍ እንዳደረገችውና ወደ ሆስፒታል በሩጫ ሲወሰዱ አእምሮአቸውን ሳይስቱ እርሷን እየተመለከቱ እንዲቆዩ እንደ ረዳቻቸውም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ተናግረው ነበር፡፡

የፋጢማ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ማርያም የመጀመሪያው ቤተመቅደስ ሥራ የተጀመረው እ.አ.አ. በ1928 ዓ. ም. ሲሆን የተመረቀው እ.አ.አ. በጥቅምት 7 ቀን 1953 ዓ. ም. ነበር፡፡ የፋጢማ እመቤታን አጅግ ቅድስት ማርያም አክብሮት እንዲስፋፋ አያሌ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ለምሳሌ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛው (1939-1958) እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀን 1942 ዓ. ም. እና በህዳር 1 ቀን 1950 ዓ.ም. እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም አክብሮት እንዲስፋፋ በሐዋርያዊ መልእክታቸው አደራ ብለው ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ጳውሎስ 6ኛው (1963-1978) በግንቦት 13 ቀን 1967 ዓ. ም. ከእህት ሉቺያ ጋር አብረው ለመጸለይ ወደ ፋጢማ መሄዳቸው ይታወሳል፡፡ በበኩላቸው ደግሞ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ (1978-2005) እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀን 1981 ዓ. ም. ከተደረገባቸው የግድያ ሙከራ ሕይወታቸውን ስለ ጠበቀች የፋጢማ እመቤታችን እጅግ ቅዱስት ድንግል ማርያምን ለማመስገን እ.አ.አ. በግንቦት 12 ቀን 1987 ዓ.ም. እንደ መንፈሳዊ ተጓዥ ወደ ፋጢማ በመሄድ በማግሥቱ የዓመታዊ ክብረ በዓሏ ተካፋይ እንደ ነበሩ ይነገራል፡፡ በዚያም አጋጣሚ ማለትም እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀን 1987 ዓ. ም. የሰውን ልጅ በሙሉ አደራ ለእመቤታችን እጅግ ንጹሕ ልብ እንደ ሰጡም ይነገራል፡፡ የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ዋና ዓመታዊ ክብረ በዓል የሚከበረው እ.አ.አ. በግንቦት 13 ቀንና በጥቅምት 13 ቀን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዓመቱን በሙሉ በበጋ ወራት ብዙ ምእመናን ወደ ፋጢማ መንፈሳዊ ጉዞ እንደሚያደርጉ ይታወሳል፡፡ በተለይም ደግሞ እ.አ.አ. በየዓመቱ በግንቦት 13 ቀን እና በጥቅምት 13 ቀን 75000 ያህል መንፈሳውያን ተጓዦች በትንሿ የፋጢማ ከተማ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያምን ለማክበር ይሰበሰባሉ፡፡ ሕይወታችን ለፋጢማ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ልብ የተለየ ይሁን፡፡ የፋጢማዋ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወታችንን ከክፉ አደጋ ሁሉ ትታደግልን፡፡

የቫቲካን ዜና

29 May 2020, 20:01