የግንቦት 16/2012 ዓ.ም 6ኛው የፋሲካ ሳምንት ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር
“መንፈስ ቅዱስ በመንገዳችን ያበራልናል እንዲሁም ይደግፋል”
የእለቱ ንብባት
1. የሐዋ. 8፡5-8. 14-17
2. መዝሙር 65
3. 1ኛ ጴጥሮስ 3፡15-18
4. 14፡ 15-21
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
ኢየሱስ ስለ ራሱ መጸለዩ
ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ፤ ጊዜው ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ ከአንተ ለተቀበላቸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንዲሰጥ በሰው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥተኸዋልና። እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። የሰጠኸኝን ሥራ በመፈጸም በምድር አከበርሁህ። እንግዲህ አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ።
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ጸለየ
“ለእነዚህ ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። የአንተ ነበሩ ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደሆነ አሁን ዐውቀዋል፤ ምክንያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸው ተቀብለዋል፤ እኔም ከአንተ እንደ ወጣሁ በርግጥ ዐውቀዋል፤ አንተ እንደላክኸኝም አምነዋል፤ እነርሱ የአንተ ስለሆኑ እጸልይላቸዋለሁ፤ ለሰጠኸኝና የአንተ ለሆኑት እንጂ ለዓለም አልጸልይም። የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ በእነርሱም ከብሬአለሁ። ከእንግዲህ እኔ በዓለም አልቈይም፤ እነርሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፤ እኛ አንድ እንደሆንን፣ እነርሱም አንድ እንዲሆኑ በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው። እኔ ከእነርሱ ጋር ሳለሁ፣ በሰጠኸኝ ስም ከለልኋቸው፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ከአንዱ ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም።
“አሁን ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ነገር ግን ደስታዬ በእነርሱ ዘንድ የተሟላ እንዲሆን፣ አሁን በዓለም እያለሁ ይህን እናገራለሁ። ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ፣ እነርሱም ከዓለም ባለመሆናቸው ዓለም ጠልቶአቸዋል። የምለምንህም ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አይደለም። እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም። ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ ቀድሳቸው።
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
በዛሬው ዕለተ ሰንበት የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ዮሐ 14፡15-21) ሁለት መሠረታዊ መልዕክቶችን ያቀርባል -ትዕዛዛቱን መጠበቅ እና የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ።
ኢየሱስ ለእርሱ ያለን ፍቅር ትዕዛዛቱን ከመጠብቅ ጋር ያገናኛል፣ እናም በዚህ የመሰናበቻ ንግግሩ ላይ “ብትወዱኝ ትዕዛዜን ትጠብቃላችሁ” (ዩሐንስ 14፡15) በማለት የተናገረው በዚህ ምክንያት ነው። “ትዕዛዜን የሚቀበልና የሚጠብቀው እኔን ይወዳኛል” (ዮሐንስ 14፡ 21) በማለት አክሎ ይገልጻል። ኢየሱስ እንድንወደው ጠይቆናል ፣ ይህንን ጭብጥ በሚገባ ያብራራልናል፣ ይህ ፍቅር በእርሱ ፍላጎት ብቻ አይፈጸምም፣ ወይም በስሜት የሚፈጸም አይደለም፣ ነገር ግን የእርሱን መንገድ ማለትም የአባቱን ፈቃድ መፈጸምን ይጠይቃል። ይህ “እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ” በማለት ኢየሱስ በሰጠን የጋራ የፍቅር ትዕዛዝ ውስጥ ተገልጻል (ዮሐ 13፡34)። እርሱ “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እንዲሁ እኔን ውደዱኝ” ብሎ አልተናገረም፣ ነገር ግን “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” በማለት ነበር የተናገረው። እኛ እርሱን መልሰን እንድንወደው ሳይሆን እርሱ እኛን እንዲሁ ይወደናል። እናም የማይናወጥ ፍቅሩ በመካከላችን ተጨባጭ የህይወት ዓይነት እንዲሆን ይፈልጋል።
ደቀመዛሙርቱ በዚህ መንገድ እንዲጓዙ ለማገዝ፣ ኢየሱስ “ሌላ ጴራቂሊጦስ” ማለትም አፅናኝ ለመላክ ወደ አብ እንደሚፀልይ ቃል ገብቷል (ዮሐንስ 14፡16) በእርሱ ቦታ ሆኖ እነርሱን የሚከላከል እና እርሱን ማዳመጥ እንዲችሉ ልቦና የሚሰጣቸው እና የእርሱን ቃል በተግባር ላይ ማዋል እንዲችሉ ብርታት ይሰጣቸዋል። ወደ ክርስቲያን ልብ ውስጥ የሚገባ የእግዚአብሔር ፍቅር ስጦታ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ይህ ነው። ኢየሱስ ከሞተ እና ከሞት ከተነሳ በኋላ ፍቅሩ በእርሱ ለሚያምኑ እና በአብ ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም ለተጠመቁ ሁሉ ይሰጣል። መንፈስ ቅዱስ ራሱ ይመራቸዋል ፣ ያበራላቸዋል፣ ያጠናክራቸዋል፣ በዚህም እያንዳንዱ ሰው በሕይወቱ ውስጥም ቢሆን ፣ በመከራም እና በችግር ፣ በደስታ እና በሐዘን ውስጥ ፣ በእየሱስ መንገድ ላይ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል። ይህ እንዲፈጸም ለማድረግ ለመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ተገዢ መሆን መጽናናትን ብቻ ሳይሆን የሚያስገኝልን፣ ነገር ግን የልብ መለወጥ፣ ወደ እውነት እና ፍቅር እንድናመራ ሊያደርገን ይችላል።
ሁላችንም የምንሠራውን የስህተት እና የኃጢአት ልምምድ ተገንዝቦ ፣ መንፈስ ቅዱስ እንዳንሸነፍ ይረዳናል እናም የኢየሱስን ቃላት ትርጉም እንድንገነዘብ እና እንድንኖር ያደርገናል “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ” (ዮሐንስ 14፡5) ይለናልና። ትእዛዛቶቹ እንደ አንድ መስታወት የእኛን ስህተቶች እና ክፉ ተግባራት ፍንትው አድርገው በማሳየት እንዲያንጸባርቁ ታስበው የተሰጡን አይደለም። እንዲ በፍጹም አይደለም! የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሕይወት ቃል ሆኖ ተሰጠን፣ እሱም ይለወጣል ፣ ያድሳል ፣ አይፈረድም ነገር ግን የሚፈውስ እና ዋና ዓላማው ይቅርታን ማድረግ ነው። ለእግራችን የሚያበራ ቃል ነው። እናም ይህ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው! እሱ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ፣ ነፃ ሰዎች እንድንሆን የሚረዳን ፣ እሱ ራሱ እግዚአብሔር ነው፣ መውደድ እና መወደድ የምንፈልግ ሰዎች እንድንሆን፣ ሕይወት በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ ጌታ ያደረገውን ድንቅ ሥራዎች የማወጅ ተልእኮ መሆኑን የተገነዘብን ሰዎች እንድንሆን ያደርገናል።
የእግዚአብሔርን ቃል እንዴት ማዳመጥ እንደ ሚገባት ያወቀች እና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ የተቀበለች የቤተክርስቲያን እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቅዱስ ወንጌል በደስታ እንድንኖር ፣ ልብን የሚያሞቅ እና አካሄዳችንን የሚያበራል መለኮታዊ እሳት የሆነውን መንፈስ ቅዱስ እንድንቀበል እንድትረዳን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።
ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 09/2012 ዓ.ም በቫቲካን ካደረጉት አስተንትኖ የተወሰደ።