ፈልግ

የግንቦት 16/2012 ዓ.ም ዘትንሣኤ 6ኛ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ የግንቦት 16/2012 ዓ.ም ዘትንሣኤ 6ኛ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ 

የግንቦት 16/2012 ዓ.ም ዘትንሣኤ 6ኛ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.     ሮሜ 6፡ 1-11

2.     1ኛ ጴጥ 4፡1-11

3.     ግ. ሓዋ. 23፡ 12-22

4.     ዮሓ.21፡ 15-25

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

በልተው ካበቁ በኋላ፣ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፣ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፤ ከእነዚህ አብልጠህ ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው።ኢየሱስም፣ “ጠቦቶቼን መግብ” አለው። ኢየሱስም ለሁለተኛ ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ በእውነት ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም፣ “አዎን፤ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም፣ “በጎቼን ጠብቅ” አለው።

ሦስተኛም ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ ትወደኛለህን?” አለው። ጴጥሮስም ሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስ፣ ‘ትወደኛለህን?’ ብሎ ስለ ጠየቀው ዐዝኖ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድህም ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በጎቼን መግብ። እውነት እልሃለሁ፤ ወጣት ሳለህ ልብስህን ራስህ ለብሰህ ወደ ፈለግህበት ትሄድ ነበር፤ ስትሸመግል ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላም ሰው ልብስህን አስታጥቆህ ልትሄድ ወደማትፈልግበት ይወስድሃል።” ኢየሱስ ይህን ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብረው ለማመልከት ነው። ከዚህ በኋላም፣ “ተከተለኝ” አለው።

ጴጥሮስ ወደ ኋላው ዘወር ሲል፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር ሲከተላቸው አየ፤ ይህም ደቀ መዝሙር ያን ጊዜ ራት ሲበሉ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበር። ጴጥሮስም ባየው ጊዜ፣ “ጌታ ሆይ፤ እርሱስ?” ብሎ ጠየቀ። ኢየሱስም፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ እንኳ አንተን ምን ቸገረህ? አንተ ራስህ ተከተለኝ” አለው። በዚህ ምክንያት ይህ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሰራጨ። ኢየሱስ ግን፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ አንተን ምን ቸገረህ?” አለው እንጂ እንደማይሞት አልነገረውም። ስለ እነዚህ የሚመሰክረውና ይህን የጻፈው ይኸው ደቀ መዝሙር ነው፤ ምስክርነቱም እውነት እንደሆነ እናውቃለን።ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎችም ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሁሉም ነገር ቢጻፍ፣ ለተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ ዓለም በቂ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር የትንሳኤ ስድስተኛ ሰንበትን እናከብራለን።

በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የሕይወታችን መመሪያ የሆነውን ቃሉን ቅድስት ቤተክርስቲያን ለዕለቱ ባዘጋጀችልን ንባባት ኣማካኝነት ወደ እያንዳዳችን ልብ ይልካል። በእርግጥ  ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ቃሉን ወደ እኛ ሲልክ ቃሉን በሙሉ ልብ እንድናዳምጥና እንድናስተውል ቢሆንም የቃሉ መደመጥ ዋነኛ ዓላማውና ግቡ ያዳመጥነውን ቃል በሕይወታችን መተግበር እንድንችል ነው። ለዚህም ነው ሁል ጊዜ የቃሉ ሰሚዎች ብቻ ሳንሆን በተግባር የምናውልበት ብርታትና ጸጋ ስጠን ብለን የምንለምነው።

እንግዲህ በዚህ መልኩ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልዕክት ኣድርጎ ዛሬ ለእኛም እግዚኣብሔር ፍጹም መሓሪ ፍጹም ይቅር ባይ ኣምላክ መሆኑን ይነግረናል።

እኛ ልጆቹ ምን ያሕል ኃጢያተኞች ብንሆንም እንኳን በእርሱ ፊት ለመቆም የተገባንና ሥሙን ለመጥራት በኣነጋገራችን ሆነ በኣካሄዳችን ሆነ በምግባራችን የተገባን ባንሆንም እንኳን የእርሱ ፍቅር የእርሱ ቸርነት የእርሱ ምሕረት እኛ ከምንገምተው በላይ ነውና እጆቹን ዘርግቶ ሊያቅፈን ሊያበረታታን እውነተኛ ኣባትነቱን ሊያሳየን ዘወትር ወደ እኛ ይመጣል ከኃጢኣታችንም ይፈታናል በፍቅሩና በጸጋውም ይሞላናል።

ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በዚሁ መልዕክቱ በቁጥር 2 ላይ እንደሚጠቅሰው እኛ ለኃጢኣት ሞተናል ይላል። ለኃጢኣት መሞት ማለት በእግዚኣብሔር ጸጋ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ በመሳተፍ ድሮ ከነበርንበት ኣሮጌ እኛነት በመውጣት በኣንድያ የእግዚኣብሔር ልጅ የተጎናጸፍነውን ኣዲሱን ከኃጢኣት ነፃ የወጣውን ሰውነት ይዘን ወደ ቅድስና ጉዞ መጀመር ማለት ነው። ለኃጢኣት መሞት ማለት ማንነታችንን ሙሉ በሙሉ ለእግዚኣብሔር ፈቃድ ማስገዛት ማለት ነው።  ለኃጢኣት መሞት ማለት ለራሳችን ፍላጎትና ስሜት ብቻ መገዛት ሳይሆን እግዚኣብሔር በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በመንፈስ ቅዱስ ኣጋዢነት ለሚሰጠን መመሪያ ተገዢ መሆን ማለት ነው። ለኃጢኣት መሞት ማለት ሰይጣንንና ከእርሱ የሚመነጨውን ማንኛውንም ዓይነት ክፉ ሓሳብና ምኞት መካድ ማለት ነው። ለኃጢኣት መሞት ማለት ከማንኛውም ዓይነት ኃጢኣት ነፃ በመሆን በእግዚኣብሔር ጸጋ ውስጥ መመላለስ ማለት ነው።

ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ እንደሚለው በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ተጠምቀናል ስንል ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ኣብረን ሞተናል ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣብረን ወደ መቃብር ወረደናል እዛም በኃጢኣት የበሰበሰውን ኣሮጌውን ሰውነት በመተው ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ኣብረን በኣዲስ ሰውነት በኣዲስ መንፈስ በኣዲስ ኃይል ተነስተናል ማለታችን ነው በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣዲስ ፍጥረት ሆነናል ማለታችን ነው።

ይህ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነውን ኣዲስ ሕይወት በተለያዩ መንፈሳዊ እሴቶች ልንጠብቀው ልንንከባከበው ይገባል። በተለይም የእምነታችን መሠረትና የጸጋዎች ሁሉ ምንጭ በሆነው በመሥዋተ ቅዳሴ በመሳተፍ የምስጢራትና የጸጋዎች ሁሉ ባለቤት የሆነውን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በሥጋ ወደሙ መልክ በመቀበልና ከእርሱም በምናገኘው ኃይል በየትኛውም መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተካፋይ በመሆን ልናሳድገው ይገባል።

ይህ የተቀበልነው ኣዲስ ሰውነት በዚህ መልኩ በየጊዜው እየታደሰ የማይሄድ ከሆነ የተቀበልነው ጸጋ ቀስ በቀስ ከውስጣችን በመውጣት ተመልሰን ወደ ድሮው ኃጢያተኛ እኛነታችን በማዘንበል እንደ ቀድሞው የሰይጣንና የእርሱ ሥራ ብቻ ተካፋዮች እንሆናለን። ኣንድ ተክል ተተክሎ ኣስፈላጊው እንክብካቤ ካልተደረገለት በምንም መልኩ ሊያድግ ኣይችልም። ማለትም ውኃ ማጠጣት መኮትኮት ኣረሙን ማስወገድ በዙሪያው ማዳበሪያ መጨመርና የመሳሰሉትን ከተነፈገ ኣድጎ ፍሬ ማፍራት ኣይደለም ማደጉ ራሱ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል ቀስ በቀስ ይጠወልጋል ይደርቃል በስትመጨረሻም ይሞታል። እኛም በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንደዚህ ነን ኣስፈላጊው መንፈሳዊ እንክብካቤ ከሌለ ቀስ በቀስ አንጠወልጋለን እንደርቃለን በስተመጨረሻም እንሞታለን።

ቅዱስ ሓዋርያው ጴጥሮስም በሁለተኛ መልዕክቱ የሚደግምልን ተመሳሳይ ሓሳብ ነው። ለኃጢያት ሞተናልና ከእንግዲህ ወዲህ የሥጋን ክፉ ምኞት በማድረግ ሳይሆን የእግዚኣብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም መኖር ኣለብን ይለናል።

ቅዱስ ሓዋርያው ጴጥሮስ ሌላ የሚያካፍለን ሓሳብ ሁልጊዜ የዓለም መጨረሻ ነገ እንደሆነ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ መምጫ ነገ እንደሆነ ኣድርገን መኖር እንዳለብን ይነግረናል። ይህም ማለት ዘወትር ከኃጢኣት ፀድተን በእግዚኣብሔር ጸጋ እየተመላለስን እንድንኖር በትንሣኤው ኣማካኝነት ያገኘነውን ኣዲስ ሕይወት ጠብቀን ይዘን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንድንሻገር መልዕክቱን ያስተላልፍልናል። ቅዱስ ሓዋርያው ጴጥሮስ በመቀጠል እንደ ባለኣእምሮ ኣስቡ ጸሎትን ለማድረግ ይረዳችሁ ዘንድ በመጠን ኑሩ ከሁሉ በላይ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ፍቅር ይኑራችሁ እግዚኣብሔር በሰጣችሁም ስጦታ ተጠቅማችሁ ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን በሚገባ ኣገልግሉ ይለናል። ይህንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው በሰጠን ኣዲስ ሕይወት ውስጥ እይኖርን ነን ብለን መናገር የምንችለው። ይህንን መተኪያ የሌለው ቀጥተኛ መንገድ መከተል ስንችል ብቻ ነው የመንግሥተ ሰማይ እጩዎች የእግዚኣብሔርም ቃል ፈፃሚዎች ነን ብለን በሙላት መናገር የምንችለው። በዛሬው በዮሓንስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ላይ ሲነበብ እንደሰማነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ያደረገውን ውይይትና ስለሰጠውም ኃላፊነት ይናገራል። ይህ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠው ኃላፊነት ገና ከጅምሩ ጴጥሮስ ሲጠራ ዓሣ ኣጥማጅ ነበርክ ኣሁን ግን የሰዎች ኣጥማጅ ትሆናለህ ብሎ የተናገረው የክርስቶስ ቃል ተፈፀመ፣ ምክንያቱም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሦስት ጊዜ የዮና ልጅ ስምኦን ሆይ ከነዚህ ይልቅ ኣብልጠህ ትወደኛለህን? ብሎ ከጠየቀው በኋላ ግልገሎቼን ኣሰማራ ጠቦቶቼን ጠብቅ በጎቼን ኣሰማራ ብሎ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቶታል። ስለዚህ በዚህ መልኩ የክርስቶስ የሆኑት ክርስቶስ በየስማቸው ይጠራቸው የነበሩት ከፊት ከፊትም በመሄድ ይመራቸው የነበሩት ስለእነሱም ሲል ሕይወቱን ኣሳልፎ የሚሰጥላቸው የበጎቹ ጠባቂ ኣደረገው፣ እኛም የክርስቶስ በጎች የሆንን ይህንን የክርስቶስን ቃል ሰምተን በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ኣማካኝነት ወደ ዘለዓለም ሕይወት እንሻገራለን። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በጎቹን በለመለመ መሥክ እንደሚመራ ሁሉ ቅዱስ ጴጥሮስም በተቀበለው ኃላፊነት መሠረት በጎቹንም ሆነ ጠቦቶቹን በለመለመ መሥክ ይመራል፣ በዚህም መንጋ ውስጥ የተካተተ ሁሉ የኋላ ኋላ በክርስቶስ ጥላ ውስጥ ይኖራል ምክንያቱም ቅዱስ ጴጥሮስም በጎቹን እንዲያሰማራ ኃላፊነቱን ይውሰድ እንጂ በጎቹም ሆኑ ጠቦቶቹ ሁል ጊዜም ቢሆን የክርስቶስ ናቸው።

እንድ ኣንድ የቤተክርስቲያን ኣባቶች ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሓዋርያው ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ የዮና ልጅ ስምኦን ሆይ ከነዚህ ይልቅ ኣብልጠህ ትወደኛለህን? ብሎ የጠየቀው ከዚህ በፊት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ በተሰጠበት ጊዜ ሓዋርያው ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በመካዱ ይህንን የክህደቱን ቃል መሰረዣና እንደ ንስሃም የሚቆጠር ነው ይላሉ። ስለዚህ እኛም በሰራናቸው ኃጢኣቶች በመፀፀትና እውነተኛ ንስሃ በመግባት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ባሳየን መንገድ ባስተማረን ትምህርት በሰጠን ጸጋ መመላለስ እንድንችል ዘወትር ከልጇ ኣጠገብ የማትለይው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእኛም ኣጠገብ ሆና የኣንድያ ልጇን ጸጋና በረከት ለእያንዳዳችን ታሰጠን እጃችንንም ይዛ  ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በሚገኝበት በለመለመው መስክ ትምራን። በተለይም ይህ የግንቦት ወር ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተለየ ወር ነውና በዚህ ጊዜ የእርሷን ትሕትና የእንሷን ታዛዢነት የእርሷን ቅድስና በመመልከት እኛም በተቻለን ኣቅም ሁሉ ትሑቶች ታዛዦቻ ቅዱሳኖች ለመሆን ጥረት እንድናደርግና ልክ እንደ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቅድስናን መንገድ መከተል እንድንችል እሷ ራሷ እጃችንን ይዛ ትምራን እርሷ ወደ ደረሰችበትም ቦታ ታድርሰን።

ምንጭ፡ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛ ክፍል

23 May 2020, 14:38