ፈልግ

ምዕመናን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በጸሎት ላይ፣ ምዕመናን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በጸሎት ላይ፣ 

“ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከኮሮና ወረርሽኝ ራስን ለመከላከል የሚያግዝ ምክር አስተላልፈዋል”።

የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምክትል ዋና ጸሐፊ፣ ክቡር አባ ኢቫን ማፌይስ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን በመወከል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 20/2012 ዓ. ም. ባቀረቡት ስብከት “የእግዚአብሔር ሕዝብ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ፣ ከመንግሥት በኩል የሚወጡትን ደንቦች አሁንም በታማኝነት ማክበር ያስፈልጋል” በማለት ያቀረቡት ምክር ከኮሮና ወረርሽኝ ራስን ለመከላከል የሚያግዝ ወሳኝ ምክር መሆኑን አስታውቀዋል። የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት፣ ሕዝቡ እስካሁን የደረጋቸው መስዋዕትነት ከንቱ እንዳይሆንና እያንዳንዱ ግለሰብ ለሰው ልጅ ሕይወት ከፍተኛ ዋጋን በመስጠት ሃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያሳስብ መልዕክት መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የጣሊያን መንግሥት ያወጣውን ሁለተኛ ዙር የጥንቃቄ ደንቦች ተግባራዊ በማድረግ፣ ወረርሽኙ ተመልሶ እንዳይስፋፋ ለማድረግ ቤተክርስቲያን የበኩሏን ተከታታይ ጥረት የምታደርግ መሆኑን፣ የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምክትል ዋና ጸሐፊ፣ ክቡር አባ ኢቫን ማፌይስ፣ ቅዱስነታቸው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያስተላለፉትን ምክር ዋቢ በማድረግ አስታውቀዋል። ክቡር አባ ኢቫን ማፌይስ በማከልም የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ ምኞት እና ፈቃድ መንግሥት ያወጣቸውን ደንቦች በማክበር ወረርሽኙ ቀንሶ ከሚገኝበት ደረጃ ተመልሶ እንዳይስፋፋ ለማድረግ ገንቢ ውይይቶችን እያደረጉ ወደ ፊት ለመጓዝ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

“የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምክር አባታዊ ምክር ነው” ያሉት ክቡር አባ ኢቫን ማፌይስ፣ ቅዱስነታቸው ሕዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ብለው ያስተላለፉት ምክር ወሳኝ እና ወቅታዊ ነው ብለዋል። ጤናችን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት ክቡር አባ ኢቫን ማፌይስ፣ ከወረርሽኙ ራሱን ለመከላከል ሕዝቡ እስካሁን የከፈለው መስውዕትነት እና የሀገሪቱ ስቃይ ባክኖ እንዳይቀር፣ በጤና ባለሞያዎች እና በካህናት የተከፈለው የሕይወት መስዋዕትነት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚሰቃዩትን ለመርዳት በግለሰቦች የተደረገ እርዳታ እና ጥረት መዘንጋት የለበትም ብለው፣ ይህን መዘንጋት ትልቅ ሃላፊነት መዘንጋት ነው ብለዋል።

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አልተላቀቅንም ያሉት የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምክትል ዋና ጸሐፊ ክቡር አባ ኢቫን ማፌይስ፣ ወደ ፊት በሚጠብቁን ሳምንታትም ከመንግሥት የተሰጡንን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ የተጣለብንን ሃላፊነት በብቃት መወጣት ያስፈልጋል ብለዋል። ወደ መደበኛው የቤተክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓታችን እና ዕለታዊ ተግባሮቻችን ቀስ በቀስ እስክንመለስ ድረስ የተጣለብንን አደራ ተግባራዊ ማድረግ አለብን ብለዋል።

ይህን ዜና በድምጽ ማድመጥ ከፈለጉ የተጫወት ምልክትን ይጫኑ፣
29 April 2020, 17:14