አዎንታዊ አስተሳሰቦችን ከሚያራምዱ ማኅበራዊ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል!
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ
ክፍል ዘጠኝ
አዎንታዊ አስተሳሰቦችን ከሚያራምዱ ማኅበራዊ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል!
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፣ ባለፈው ዝግጅታችን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ አራት ዋና ዋና የታሪክ ሂደቶችን አልፎ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ መድረሱን መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ከእነዚህ ደረጃዎች መካከል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕዮተ ዓለም (እ.አ.አ 1891-1931) እና አዲስ የክርስቲያን አስተሳሰብ (እ.አ.አ. 1931-1958) የተሰኙትን ሁለቱን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ያለፈባቸውን የታሪክ ሂደቶች በቅደም ተከተል በአጭሩ ከእዚህ ቀደም ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው እለት የክፍል ዘጠኝ ዝግጅታችን ደግሞ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ ያለፈበትን ሦስተኛውን የታሪክ ሂደት እንደ ሚከተለው በአጭሩ እናስቃኛችኋለን፣ እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።
አቅራቢ እና አዘጋጅ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ካለፈባቸው ታሪካዊ ሂደቶች ውስጥ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚጠቀሰው የታሪክ ሂደት ደግሞ የተለያዩ አዎንታዊ አስተሳሰቦችን ከሚያራምዱ ማኅበራዊ አካላት ጋር በተደጋጋሚ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ይሞግት የነበረው የታሪክ ሂደት ይገኝበታል።
ይህ ታሪካዊ ሂደት የተከሰተው እ.አ.አ ከ1958-1978 ዓ.ም ድረስ በነበረው የታሪክ ሂደት ውስጥ በዓለም ዙሪያ በወቅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይንጸባረቅ በነበረው ምዕራባዊያን እና ምስራቃዊያን ብሎ በመፈረጅ በሁለት ጎራ ዓለማችንን ከፋፍሏት የነበረ የታሪክ ሂደት ሲሆን ምዕራቡን የዓለማችንን ክፍል እንደ ባለጸጋ፣ የሰለጠነ፣ ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ብቃት ያለው ተደርጎ የተቆጠረ ሲሆን፤ በአንጻሩ ደግሞ የምስራቁ የዓለማችን ክፍል ድሃ፣ ኋላ ቀር፣ ስልጣኔ የጎደለው፣ ተራማጅ ያልሆነ . . . ወዘተ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። በእነዚህ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰቦች የተነሳ የተለያዩ ጦርነቶች በዓለማችን ዙሪያ ይካሄዱ የነበረ ሲሆን እነዚህን ግጭቶች እና ጦርነቶች ለማስቀረት በማሰብ በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ዮሐንስ 23ኛ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ እንዲካሄድ በመወሰን በወቅቱ በጉባሄው ሽፋን ከተሰጣቸው አርዕስቶች መካከል “ሰላም በምድር ላይ ይሁን” በሚል ጭብጥ ዙሪያ ላይ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳትን ያሳተፈ ጉባሄ እንዲደረግ መወሰናቸው እና በወቅቱ ለነበረው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ በተወሰነ መልኩም ቢሆን እንኳን ማኅበራዊ መግባባት እና መፍትሄ እንዲመጣ ያስቻለ በላቲን ቋንቋ “Pacem in terris” በአማርኛው “ሰላም በምድር ላይ ይሁን” በሚል አርዕስት አንድ ሐዋርያዊ መልእክት ለንባብ ማቅረባቸው ይታወሳል።
በተለይም ደግሞ በወቅቱ ምዕራባዊያን እና ምስራቃዊያን የሚል መጠሪያ ተሰቷቸው በሁለት ጎራ ተከፋፍለው በተፋጠጡ የዓለማችን ሀገራት ሳቢያ ዓለማችን ለከፍተኛ ጦርነት በመጋለጧ፣ አልፎም ተርፎም የቀዝቃዛው ጦርነት በመባል በሚታወቀው ሂደት ውስጥ በተለይም በአሜሪካ እና በራሻ ከፍተኛ የሆነ ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ጅምላ ጨራሽ የሚባሉ የኒውክለር የጦር መሣሪያዎችን ለማምረት በሚሯሯጡበት ወቅት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በላቲን ቋንቋ “Pacem in terris” በአማርኛው “ሰላም በምድር ላይ ይሁን” በሚል አርዕስት ለንባብ ባበቃችሁ ሐዋርያዊ መልዕክት ሁለቱ የዓለማችን ኃያላን የሚባሉ ሀገራት ጅምላ ጨራሽ በሆነ መልኩ የጋራ መኖሪያ የሆነችውን ምድራችንን በጅምላ የሚያጠፋ የጦር መሳሪያዎችን ከማምረት እንዲቆጠቡ እና ከተቻለም እነዚህን ጅምላ ጨራሽ የሆኑ የኒውክለር የጦር መሣሪያዎችን ከምድረ ገጽ ያስወግዱ ዘንድ በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በማቅረብ ሁለቱ ኃያላን የሚባሉ ሀገራት ፍጥጫቸውን አቁመው ወደ ሰላም እንዲመለሱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ አስተዋጾ ማድረጓ ይታወሳል።
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ይህንን የጀመረችውን የሰላም እና ማኅበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን የምታደርገውን እንቅስቃሴ እና አስተዋጾ አጠናክራ በመቀጠል በላቲን ቋንቋ “Mater et magistra፣ Gaudium et spes፣ Populorum Progressi፣ Octogesima adveniens” በሚል አርዕስት በተከታታይ ሐዋርያዊ መልዕክቶችን ለንባብ በማብቃት በምድራችን ላይ ማሕበራዊ ፍትህ እና ሰላም እንዲሰፍን በታሪክ ሂደት ውስጥ ያደርገችው ጥረት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ያለፈበት ሦስተኛ የታሪክ ሂደት ነው።