ፈልግ

ምዕመናን ተሰብስበው በጸሎት ሲተባበሩ ፣ ምዕመናን ተሰብስበው በጸሎት ሲተባበሩ ፣ 

“የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሐይማኖት ተቋማት መተባበር ያስፈልጋል”።

“ሐይማኖቶች ለሰላም” በሚል ርዕሥ የልዩ ልዩ ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የተገናኙበት መንፈሳዊ ጉባኤ የተካፈሉት በናይጄሪያ የአቡጃ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦሎሩንፈሚ ኦናይየካን ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ጥረት እንዲያድረጉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመላው ዓለም የሚገኝ የሰው ልጅ የኮሮና ቫይረስን በመዋጋት ጤናን ፣ ርህራሄን እና ጥንካሬን ማግኘት ይችል ዘንድ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ጥረት እንዲያደርጉ በማለት “ሐይማኖቶች ለሰላም” በሚል  ርዕሥ ዛሬ መጋቢት 23/2012 ዓ. ም. ከ900 በላይ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ዓለም አቀፍ መንፈሳዊ ጉባኤን ባሉበት ሆነው ማካሄዳቸው ታውቋል። ዛሬ በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር በአሥር ሰዓት ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት በተጀመረው ጉባኤ ላይ ከሊማ፣ ከኒዩ ዮርክ፣ ከሎንደን፣ ከቤይሩት፣ ከቶኪያ እና ከኦስሎ ከተሞች የተወጣጡ የክርስትና፣ የእስልምና፣ የአይሁድ፣ የቡዳ እና የዞራስት እምነት ተወካዮች ከመኖሪያቸው ሆነው የተካፈሉ መሆኑ ታውቋል።           

ዓለም አቀፍ አባልነት፣

ይህን የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ዓለም አቀፍ ጉባኤን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በመወከል የተገኙት በናይጄሪያ የአቡጃ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦሎሩንፈሚ ኦናይየካን “ሐይማኖቶች ለሰላም” የሚል መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ፕሬዚደንት መሆናቸው ታውቋል። በተጨማሪም ጉባኤውን በድረ ገጽ ከተካፈሉት መካካል ከግሪክ፣ ከዩጋንዳ፣ ከሰሜን አመሪካ የተወጣጡ የልዩ ልዩ ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች እና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች መካፈላቸው ታውቋል።        

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶችን በማስመልከት ቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ  ያደረጉት በናይጄሪያ የአቡጃ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦናይየካን ለዜና ማዕከሉ እንደገለጹት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት እንደጠየቁን በሕብረት በመሰባሰብ ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን ለመቋቋም የጋራ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በተመለከተ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክት ግልጽ ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦናይየካን ሃይማኖታዊ ቡድኖች በድንበሮች ሳይወሰኑ የጋራ ጥረትን በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል። የሐይማኖት ፣ የአገር እና የቆዳ ቀለም ሳይገድበን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመዋጋት በጋራ መቆማቸውን ገልጸዋል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪ መሠረት የዓለም የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች በመተባበር ጸሎት በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ጆን “ሐይማኖቶች ለሰላም” በሚል መንፈሳዊ እንቅስቃሴ አማካይነት እግዚአብሔር ከዚህ ታላቅ መከራ ነፃ እንዲያወጣን በማለት የሰው ልጆች በሙሉ ጸሎታችንን ወደ እግዚአብሔር እናቀርባለን ብለዋል።       

ይህን ጉባኤ በአካል ተገናኝተን ለማካሄድ ዕድል ባናገኝም በዓለም ዙሪያ የምንገኝ በሙሉ እንደየ ባሕላችን በመተባብር  ልባችንን ለእግዚአብሔር በመክፈት በአጭር ደቂቃዎች ውስጥ ለመገናኘት ችለናል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦናይየካን ይህን ግንኙነት ለማድረግ የዘመኑ ቲክኖሎጂ ጥሩ ዕድል የከፈተ በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸሎት ጥሪ ዓለማችን አስፈላጊ እንደ ጤና ባለሞያዎች እኛም በበኩላችን ውጤታማ እርምጃዎችን፣ ጥንቃቄዎችን እና አዳዲስ ጥናቶችን ማካሄድ እንዳለብን ያሳስበናል ብለው በማከልም ከሁሉም በላይ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቀርበን ምሕረትን መለመን ያስፈልጋል ብለዋል። ከወረርሽኙ ለመውጣት የእያንዳንዱ ሰው የጋራ ጥረት ሊታከልበት ያስፈልጋል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦናይየካን በናይጄሪያ የሚታየው ዝቅተኛ ጥረት ተስፋን በማጨለም ወደ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ሊመራ ይችላል ብለዋል።

በናይጄሪያ ውስጥ በመቶች የሚቆጠሩ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መመዝገባቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦናይየካን ጥናቃቄ ካልታከለበት እንደ ሌሎች አገሮች ከፍተኛ የሰው ሕይወት መጥፋትን ሊያስከትል ይችላል ብለዋል። በአገራቸው ከፍተኛ የሕክምና መገልገያ መሣሪያ እጥረት አለ ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦናይየካን ይህም ለቫይረሱ መዛመት ዕድል ይከፍታል ካሉ በኋላ በዚህ ሁኔታ ላይ ለሚገኝ ሕዝብ የእግዚአብሔር ዕርዳታ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው የብርሃነ ትንሳኤው ተስፋ ከሞት ወደ ሕይወት ያሸጋግረናል ብለዋል።     

01 April 2020, 17:30