ፈልግ

የመጋቢት 27/2012 ዓ.ም 5ኛው የዐብይ ጾም ሳምንት እለተ ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

“ሐዘናችንን ሐዘኑ በማድረግ ርህራሄ የሚያሳየውን ኢየሱስ ምሳሌ ልንከተል ይገባል” !

የእለቱ ምንባባት

1.      ሕዝቅኤል 37፡11-14

2.    መዝሙር 129

3.    ሮም. 8፡8-11

4.    ዮሐንስ 11፡1-45

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ማርያምና ከእኅትዋ ከማርታ መንደር ከቢታንያ የሆነ አልዓዛር የሚባል አንድ ሰው ታሞ ነበር። ማርያምም ጌታን ሽቱ የቀባችው እግሩንም በጠጕርዋ ያበሰችው ነበረች፤ ወንድምዋም አልዓዛር ታሞ ነበር። ስለዚህ እኅቶቹ ጌታ ሆይ፥ እነሆ የምትወደው ታሞአል ብለው ወደ እርሱ ላኩ። ኢየሱስም ሰምቶ ይህ ህመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም አለ። ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን አልዓዛርንም ይወድ ነበር። እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያን ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤ ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ አላቸው። ደቀ መዛሙር መምህር ሆይ፥ አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፥ ደግሞም ወደዚያ ትሄዳለህን? አሉት። ኢየሱስም መል ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል አላቸው።  ይህን ተናገረ፤ ከዚህም በኋላ ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ ጌታ ሆይ፥ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል አሉት። ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደ ተናገረ መሰላቸው።
እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ አልዓዛር ሞተ፤ እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ አላቸው። ስለዚህ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርት ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ አለ። ኢየሱስም በመጣ ጊዜ በመቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው።
ቢታንያም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው።
ኢየሱስም ወንድምሽ ይነሣል አላት። ማርታም በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው።ኢየሱስም ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤
ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።
እርስዋም አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው። ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል አለቻት።እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት።
ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር አለችው። ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ ወዴት አኖራችሁት? አለ። እነርሱም ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ አሉት።
ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህ አይሁድ እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ አሉ።
ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ ይህ የዕውሩን ዓይኖች የከፈተ ይህን ደግሞ እንዳይሞት ያደርግ ዘንድ ባልቻለም ነበርን? አሉ።

ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ ድንጋዩን አንሡ አለ። የሞተውም እኅት ማርታ ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል አለችው።
ኢየሱስ ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን? አላት። ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ አለ። ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ።

የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም ፍቱትና ይሂድ ተዉት አላቸው። ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶች እንደምን ከረማችሁ!

በዛሬው (መጋቢት 27/2012 ዓ.ም) በአምስተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት ሰንበት እለተ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ዮሐንስ 11፡1-45) የአልዓዛር ከሞት መነሳት ይገልጻል። አልዓዛር የኢየሱስ ወዳጆች የነበሩት  የማርታ እና የማሪያ ወንድም ነው። ኢየሱስ ወደ ቢታንያ ሲደርስ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀናት ያህል ሞልቶት ነበር፣ ማርታ ጌታን ለመገናኘት ሮጣ በመሄድ “እዚህ ብትኖር ኖሮ ወንድሜ አይሞትም ነበር” (ዮሐንስ 11፡ 21) አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሳል” (ዩሐንስ 11፡23) በማለት መለሰላት። “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል” (ዩሐንስ 11፡25) በማለት አክሎ ይናገራል። ለሙታን እንኳን ሕይወት የመስጠት ችሎታ ያለው መሆኑን እና ኢየሱስ ራሱን የሕይወት ጌታ መሆኑ ይገልጻል። ከዚያም በኋላ ማርያም እና እርሷን ተከትለዋት የመጡት አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚነግረን “ኢየሱስ መንፈሱ በኀዘን ታወከ፣ ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ” (ዮሐንስ 11፡ 33. 35)። ይህንን የሁከት ስሜት በልቡ ውስጥ ይዞ ወደ መቃብሩ ስፍራ ይሄዳል፣ ሁል ጊዜም ቢሆን ጸሎቱን የሚሰማውን አባቱን እያመሰገነ መቃብሩን አስከፍቶ “አልዓዛር ፣ ና ውጣ!” ብሎ በታላቅ ድምጽ ተጣራ (ዮሐንስ 11፡43)። አልዓዛርም “እጅና እግሩ በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ”  (ዮሐንስ 11፡44)።

እዚህ ላይ እግዚአብሄር ሕይወት መሆኑን እና ሕይወት ሰጪ መሆኑን ተጨባጭ በሆነ መልኩ እንመለከታለን። ኢየሱስ ወዳጁ የነበረውን የአልዓዛር ሞት አስቀድሞ ማስቅረት ይችል የነበረ ሲሆን ነገር ግን የምንወዳቸው ሰዎች ከእኛ በሞት በሚለዩበት ወቅት የሚሰማንን ከፍተኛ ሐዘን ኢየሱስ የራሱ ሐዘን አድርጎ በመቁጠር እና ከሁሉም በላይ ደግሞ እግዚአብሔር በሞት ላይ ያለውን ስልጣን ለማሳየት ይፈልጋል። በዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ውስጥ የሰዎች እምነት እና የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚፈልጉ ሁሉ በመጨረሻም እንደሚያገኙት እናያለን። ማርታ እና ማርያም እንዲሁም ሁላችንም “አንተ አዚህ ብትኖር ኖሮ . . . ” ብለን የምናሰማውን ጩኸት እናያለን። የእግዚአብሔር መልስ ግን ወሬ አልነበረም፣በፍጹ እንዲህ አልነበረም! ሞት ላስከተለው ችግር የእግዚአብሔር መልስ ኢየሱስ ነው-“ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ… በእኔ እምነት ይኑራችሁ! ለቅሶ ሲያጋጥማችሁ በእኔ ማመናችሁን ቀጥሉ፣ ሞት አሸናፊ ሆኖ የሚወጣ ቢምስላችሁ እንኳን በእኔ ማመናችሁን ቀጥሉ። ድንጋዩን ከልባችሁ ላይ አስወግዱት! ሞት ወዳለበት ስፍራ እግዚአብሔር ቃል ገብቶ መልስ ይሰጥ ዘንድ ፍቀዱለት”።

ዛሬም ቢሆን ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሱ” በማለት ይናገራል። እግዚአብሔር ለመቃብር አልፈጠረንም፣ እርሱ የፈጠረን ለሕይወ፣ ለውብት እና ለደስታ ነው የፈጠረን። ነገር ግን መጽሐፈ ጥበብ እንደ ሚናገረው “ሞት ወደ ዓለም የገባው በዲያብሎስ ቅናት ነው” (መ. ጥበብ 2፡24) ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከእዚህ ስይፍ ሊያድነን መጣ።

ስለሆነም የሞት ጣዕም ያላቸውን ድንጋዮች ሁሉ እንድናስወገድ ተጠርተናል፣ ለምሳሌ በእምነታችን ውስጥ ያለው ግብዝነት በራሱ ሞት ነው፣ ሌሎችን የሚጎዳ ትችት በራሱ ሞት ነው፣ በደል መፈጸም፣ ስም ማጥፋት ሞት ነው፣ ድሆችን ማግለል ሞት ነው። ጌታ እነዚህን ድንጋዮች ከልባችን እንድናስወግድ ይጠይቀናል፣ ይህንን በምናደርግበት ወቅት ሁሉ ሕይወት አሁንም በዙሪያችን ያብባል።  ክርስቶስ ህያው ነው ፣ እሱን የተቀበለ እና እሱን የሚከተል ሁሉ ከሕይወት ጋር ይገናኛል። ያለ ክርስቶስ ወይም ከክርስቶስ ውጭ በሕይወት የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ አንድ ሰው ወደ ሞት የሚወስደውን መንገድ ይከተላል ማለት ነው።

የአልዓዛር ከሞት መነሳት ደግሞ አማኙ በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት በክርስቶስ የፋሲካ ምስጢር ውስጥ መግባቱን የሚያመለክት የእድሳት ምልክት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ተግባር እና ኃይል ክርስቲያን እንደ አዲስ ፍጥረት በመሆን በሕይወቱ የሚራመድ ሰው ነው - ለሕይወት የተፈጠረ እና ወደ ሕይወት የሚሄድ ሰው ነው።

ሐዘናችንን ሐዘኑ በማድረግ ርህራሄውን የሰጠንን ልጇን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየንን ተምሳሌት በመከተል  ርህሩህ እንድንሆን ድንግል ማርያም እንድትረዳን ልንማጸናት ይገባል። በፈተና እና በመከራ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እያንዳንዳችን ቅርብ እንድሆን ዘንድ፣ ለእነሱ ሞትን የሚያሸንፍ እና ሕይወትን የሚሰጥ የእግዚአብሔር ፍቅር እና ርህራሄ ነፀብራቅ መሆን እንችል ዘንድ እርሷ እንድትረዳን አማላጅነቷን መማጸን ይኖርብናል።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 20/2012 ዓ.ም ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

03 April 2020, 18:32