ፈልግ

የአውሮፓ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምክር ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ፣ ክቡር አባ ብሪዎስ ፕሪዬቶ፣ የአውሮፓ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምክር ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ፣ ክቡር አባ ብሪዎስ ፕሪዬቶ፣ 

በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ ለሚገኙት ስደተኞች ዋስትና ያለው ጥገኝነት እንዲሰጣቸው ጥሪ ቀረበ።

የኮሮና ቭይረስ ወረርሽኝ ዓለማችንን እያሰቃየ ባለበት ባሁኑ ወቅት በሜዲቲራኒያን ባሕር በሊቢያ ወደቦች የሚገኙ ስደተኞች ሁኔታ የተመለከቱት የአውሮፓ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የአውሮፓ ሕብረት አገሮች በመተባባር ለስደተኞች አስቸኳይ የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረውጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ ምክር ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ፣ ክቡር አባ ብሪዎስ ፕሪዬቶ እንደተናገሩት ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በማድረግ በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ አሳልፎ መስጠት ትክክል አይደለም ብለዋል። ካለፉት ቀናት ወዲህ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ለአውሮፓ በሚቀርቡ የባሕር ወደቦች ተጠግተው መኖራቸው ተመልክተው እነዚህ ስደተኞች ከሚገኙበት የባሕር ላይ ስቃይ ወጥተው ወደ አውሮፓ ክልል እንዲገቡ እና የአውሮፓ አገራት መንግሥታትም በሕብረት ተጋግዘው እርዳታ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

በአንድ ነፍስ አድን የግል መርከብ ውስጥ ለቀናት ያህል በባሕር ላይ እንዲቆዩ በተደረጉት 47 ስደተኞች ሁኔታ የማልታ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከፍተኛ ጭንቀት የሚጋራው የአውሮጳ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ ይህን የስደተኞች ስቃይ እንዲያቃልል ሃላፊነት የተሰጠው የማልታ መንግሥት ስደተኞችን ወደ መጡበት ወደ ሊቢያ መመለሱንም የጳጳሳቱ ጉባኤ ምክር ቤት አስታውሷል።

የአውሮፓ ሕብረት፣ መንግሥታቱን በመርዳት የስደተኞቹን የጥገኝነት ጥያቄ ተቀብለው፣ ስደተኞቹ ተጠግተው በሚገኙበት ወደብ አገሮች አስፈላጊውን ዕርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባ ነበር በማለት የጳጳሳቱ ጉባኤ ምክር ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አባ ብሪዎስ ፕሪዬቶ ተናግረው የሊቢያ የባሕር ወደቦች ምን ጊዜም አስተማማኝ ሊሆኑ አይችሉም ብለዋል። ዓለም አቀፍ የባህር ክልል ጥበቃ ውል፣ በአንቀጽ 167/78 ላይ ተግባራዊ እንዲሆን በሚጠይቀው ደንብ መሠረት ባሕር ላይ የሚገኙ ስደተኞችም ሆነ ተጓዦች ከለላ ሊሰጣቸው የሚችለው አስተማማኝ የባሕር ወደብ በሚገኙባቸው አገራት እንደሆነ ክቡር አባ ብሪዎስ አስታውሰዋል። አባ ብሪዎስ አክለው እንዳስተወቁት ወደ መጡበት አገር እንዲመለሱ በሚደረጉበት ጊዜ ከፍተኛ ስቃይ እንደሚደርስባቸው እና ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጸምባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የሜዲቴራኒያን ባሕር ወደ መቃብር እንዳይለወጥ ከተፈለገ ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና አባል አገራት በሕብረት በመሥራት፣ የሚደርስባቸውን በደል እና ስቃይ ለመሸሽ የሚሰደዱትን እናቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶች ተቀብለው ለችግሩ የጋራ ምላሽ መስጠት አለባቸው በማለት የአውሮፓ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አሳስቧል። የጳጳሳት ጉባኤው በማከልም ስደተኞች ከሚገኙበት የባሕር ላይ ስቃይ ወጥተው ወደ አውሮፓ ክልል እንዲገቡ እና የአውሮፓ አገራት መንግሥታትም በሕብረት ተጋግዘው በባሕር ላይ ችግር ላጋጠማቸው ስደተኞች አስቸኳይ እርዳታ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሁሉም የአውሮፓ ሕብረት አገሮች መንግሥታት ችግር ውስጥ መሆናቸው የሚታወቅም ቢሆንም ሰብአዊ መርሆዎች ሁል ጊዜ በማሸነፍ ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው የአውሮፓ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አሳስቧል። ለቀናት ያህል በባሕር ላይ በችግር ውስጥ የሚገኙትን ስደተኞች ጨምሮ ማንም ሰብዓዊ ፍጡር ተዘንግቶ ወደ ጎን መባል የለበትም በማለት፣ የአውሮፓ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምክር ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ፣ ክቡር አባ ብሪዎስ ፕሪዬቶ ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. ፣ ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገርኝነት ጠያቂዎች ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ስደተኞች ብቻ ሳይሆን ማንም ሰው ተረስቶ ወይም ልዩነት ተደረጎበት ወደ ጎን መደረግ የለበትም ማለታቸውን ክቡር አባ ብሪዎስ ፕሪዬቶ አስታውሰዋል።

የአውሮፓ ሕብረት አገሮች ለእሴቶች እና መርሆዎች የጋራ ግንዛቤ ኖሯቸው፣ የሰው ልጆች በሙሉ እኩል ሰብዓዊ ክብር እንዳላችው፣ በተለይም በከፍተኛ ችግር ውስጥ በሚገኙበት ጊዜ መብታቸውን ማስጠበቅን የሚያውቅ ማኅበረሰብ መሆኑን የአውሮፓ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አስታውቋል።

26 April 2020, 13:08