ፈልግ

በኮሎምቢያ ምዕመናን በስቅለተ ዓርብ ጸሎት ላይ ሆነው፣ በኮሎምቢያ ምዕመናን በስቅለተ ዓርብ ጸሎት ላይ ሆነው፣  

በኮሎምቢያ ቤተክርስቲያን በኮሮና ቫይረስ እና በድህነት የሚሰቃዩትን በመርዳት ላይ ትገኛለች።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያስከተለ ካለው ስቃይ መውጣት የሚቻለ እርስ በእርስ በመተጋገዝ መሆኑን በላቲን አሜሪካ የኮሎምቢያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ፋቢዮ ጋቪሪያ አስታወቁ። ብጹዕ አቡነ ሄክቶር አገራቸው ከኮሮና ቫይረስ ውረርሽኝ በተጨማሪ በአመጽ እና ስር በሰደደ ድህነት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኮሎምቢያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ሥራ አስተባባሪ ጽ/ቤት እንዳስታወቀው፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለሚሰቃይ የኮሎምቢያ ሕዝብ የሕክምና ድጋፍ እንዳይደረግ ከፍተኛ የሕክምና መገልገያ መሣሪያ እጥረት እንዳለ የገለጸው ጽ/ቤቱ እርዳታን ለማሰባሰብ በተመቻቸው የቤተክርስቲያኒቱ ድረ ገጽ አማካይነት ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከላቲን አሜሪካ እና ከዓለም ዙሪያ ዕርዳታን ለማሰባሰብ የተጀመረ መሆኑ ታውቋል። ቤተክርስቲያኒቱ ከሰባሰባቸው ዕርዳታዎች መካከል አብዛኛው በብርሃነ ትንሳኤው ዕለት የተገኘ መሆኑን ጽ/ቤቱ አስታውቋል። ከተገኘው እርዳታ ውስጥ አብዛኛው የሚውለው አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው እጅግ ድሃ ለሆኑ ቤተሰውቦች፣ ለአረጋዊያን፣ ረዳት ለሌላቸው፣ መጠለያ እና ሥራ ለሌላቸው የሚሰጥ መሆኑን የሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ ሥራ አስተባባሪ ጽ/ቤት አስታውቋል። “ክርስቲያናዊ የጋራ ሃብት” በሚል መጠሪያ ዘንድሮ ለ39ኛ ጊዜ የተካሄደው የዕርዳታ ማሰባሰብ ተግባር፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የደረሰውን ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለል መሆኑ ታውቋል። የኮሎምቢያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ፋቢዮ ለመላው የአገሩ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት በልዩነት ከመከፋፈል ይልቅ ሕብረትን በመፍጠር አሁን በምንገኝበት ጊዜ ለችግር እና ለመከራ እጅ መስጠት እንደማይገባ አሳስበዋል።

የኮሎምቢያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዜጎች በመካከላቸው አንድነት እና መረዳዳት በማሳየት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በድህነት ምክንያት በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ድሃ ቤተሰቦችን ለመርዳት ጥሪ ማድረጓ ታውቋል። የዕርዳታ ተግባሯን ውጤታማ ለማድረግ ይችል ዘንድ በሃገሪቱ የሚገኙት ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች እንደ አስፈላጊነቱ አራት የተግባር መዋቅሮች መዘርጋታቸውን ያስታወቀው የሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ ሥራ አስተባባሪ ጽ/ቤቱ፣ የመጀመሪያው እና አስቸኳይ እርዳታ ማቅረብን የሚጠይቀው በረሃብ ለተጎዱት ቤተሰቦች ምግብን ወደ ቤታቸው ድረስ ማድረስ ሲሆን ሁለተኛው ዓይነት የተግባር መርሃ ግብር በከተሞች ውስጥ ለሚገኙ እና ለቫይረሱ እጅግ ለተጋለጡ እና ጥቃት ለሚደርስባቸው የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች መጠለያን እና ምግብ ማቅረብ መሆኑን ጽ/ ቤት ገልጾ ከዚህም በተጨማሪ ውስጣዊ ችግር ላለባቸ ቤተሰቦች የሥነ ልቦና እና ማህበራዊ ቅርበት በማድረግ ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት መሆኑ ታውቋል። 

ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ፋቢዮ እንደገለጹት ትልቁ እና ዋናው ጭንቀታቸው በዙሪያቸው ምንም ዓይነት ማሕበራዊ ዝምድና የሌላቸው ሰዎች ሁኔታ እንደሆነ ገልጸው እነዚህ ሰዎች በቅርብ ሆኖ የሚከታተላቸው ወይም የሚጠይቃቸው ሰው ከሌለ ራሳቸውን ከሕብረተሰቡ እንደተገለሉ ወይም እንደተረሱ አድርገው ይቆጥራሉ ብለው በተለይም አረጋዊያኑ የገንዘብ አቅም ማነስ የሚታይባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ አማጺ ብድን እና የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን ከመንግሥት ማኅበራዊ መሪ ጋር ከፍተኛ ቅራኔ መኖሩን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ፋቢዮ ከግጭት እና ከዓመፅ ጋር የተገናኘው የሰብአዊ ቀውስ ከረጅም ጊዜ ወዲህ የአገራቸው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ የቆየ መሆኑን አስረድተዋል። ሀገራቸው ኮሎምቢያ ባሁኑ ጊዜ በሁለት ማሕበራዊ ቀውሶች ውስጥ ትገኛለች ያሉት ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ፋቢዮ አንደኛው የእርስ በእርስ አምጽ ሲሆን ሁለተኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው አደጋ ነው ብለዋል። ዘንድሮ የተከበረውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ በዓል ብዙዎቹ በመከራ መካከል ማሳለፋቸውን ያስታወቁት ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ፋቢዮ የትንሳኤውን ምስጢር በማግኘት ከሞት የተነሳውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያገኙታል ብለዋል።

ይህን ዜና በድምጽ ማድመጥ ከፈለጉ የተጫወት ምልክትን ይጫኑ፣

 

16 April 2020, 09:47