ፈልግ

ሐኪሞች የሕክምና ዕርዳታ በማድረግ ላይ፣ ሐኪሞች የሕክምና ዕርዳታ በማድረግ ላይ፣ 

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቫሌንቲነቲ ለጣሊያን ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ምስጋናቸውን አቀረቡ።

የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተጎዱትን ለመርዳት የሚያስችል የሁለት ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ ዩሮ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማበርከቱ ታውቋል። የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤው ይህን ዕርዳታ ያሰባሰበው ከዜጎች ደመወዝ ተቆርጦ ለቤተክርስቲያን ከሚሰጥ ከሺህ ስምንት እጅ፣ በሃገሩ ከሚገኙ አምስት ሆስፒታሎች ከሚገኝ ገቢ እና ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ፋውንዴሽን የተገኘ መሆኑን በጣሊያን የፔስካራ-ፔኔ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ቶማሶ ቫሌንቲነቲ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ይህን ዕርዳታ መለገሱ ለጳጳሳቱ ትልቅ እውቅናን ያስገኛል ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቶማሶ ቫሌንቲነቲ ከዚህም በተጨማሪ ፋውንዴሽኑ በየክፍላተ ሃገራቱ ለሚያበረክተው ጥራት ያለው አገልግሎት ማስረጃ ይሆናል ብለው ከዚህ በፊትም ለሚያበረክተው የሕክምና አገልግሎት ከታካሚዎች ከፍተኛ አድናቆት ማትረፉን ብጹዕ አቡነ ቶማሶ ቫሌንቲነቲ ገልጸዋል። እርሳቸው በፕሬዚደነት የሚመሩትን በፔስካራ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ፋውንዴሽን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሆስፒታሉን ለዕርዳታ ማሰባሰብ ተልዕኮ መምረጡ ትክክል ነው ብለው፣ ሆስፒታሉ በእርግጥ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርን ለማገዝ አቅም ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

በማዕከላዊ ጣሊያን፣ በፔስካራ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1977 ዓ. ም. የተቋቋመው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ፋውንዴሽን አገልግሎቱን በዋናነት የሚያበረክተው በህክምና ዘርፍ መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቫሌንቲነቲ፣ ባሁኑ ጊዜ በውስጡ 380 ሠራተኞች ያሉት መሆኑን አስረድተዋል። ከጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የተገኘው ዕርዳታ በሦስት የህክምና ማዕከላት ውስጥ ለሚገኙት ሕሙማን አስፈላጊውን ሕክምና ለመስጠት እንደሚያግዝ ብጹዕ አቡነ ቫሌንቲነቲ ገልጸው፣ እርሳቸው በፕሬዚደንትነት የሚመሩት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ባሁኑ ጊዜ በተወሰኑ ክፍሎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ለሚያሻቸው ሕሙማን ብቻ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን እና በቁጥር የተወሰኑ የጤና ባለሞያዎች ብቻ ገብተው የሕክምና እርዳታን እንዲሰጡ መደረጉን አስረድተዋል።

ከጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በተገኘ ዕርዳታ ጠቅላላ የአካባቢ ጽዳትና ንፅህና ለመጨመር የሚያግዝ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቫሌንቲነቲ ገልጸው፣ ከዚህም በተጨማሪ ለጤና ባለሞያዎች የሚያገለግል ቁሳቁስ መግዣ የሚውል መሆኑን አስረድተዋል። ከፍተኛ ጥንቃቄ እና የህክምና እገዛ የሚያስፈልጋቸው ወጣት የአዕምሮ ሕሙማን በሆስፒታላቸው እንደሚገኙ ያስታወቁት ብጹዕ አቡነ ቫሌንቲነሊ ለእነዚህ ወጣቶች ከዚህ በፊት የተጀመረው የሕክምና ክትትል እንዳይቋረጥ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያመቻቹላቸው ገልጸዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያስጨነቀ ባለባት ባሁኑ ጊዜ በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ የሚገኙ ሁለት አካባቢዎች በጥበቃ እንደሚገኙ ገልጸው በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ቤተሰቦች ከቤት እንዳይወጡ መታዘዛቸውን ተናግረዋል። የቁምስና መሪ ካህናት ለቤተሰቦች ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ መሆናቸውን አስረድተው በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ካሪታስ በጎ አድራጊ ድርጅት እና ሌሎች ድርጅቶች የምግብ እና የመጠለያ አገልግሎት በማቅረብ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ተሰማርተው የሕክምና አገልግሎታቸውን በማበትከት ላይ ለሚገኙ የጤና ባለሞያዎች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ “ጊዜው አስጨናቂ ቢሆንም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር በመሆኑ ፍራቻን ማስወገድ አለብን” በማለት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቫሌንቲነቲ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።    

23 April 2020, 22:48