ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ በሕማማት ሳምንት ያሳዩት የትህትና ምሳሌ፣ ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ በሕማማት ሳምንት ያሳዩት የትህትና ምሳሌ፣ 

“እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር ድንበር የላቸውም”!

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ እና ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ እንደ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር ድንበር የሌላቸው መሆኑን አስታወቁ። ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ይህን ካሉ በኋላ ምዕመናን በሙሉ የኮሮና ቫይረስን በእምነት በተስፋ እና በፍቅር ማሸነፍ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ዘንድ ሚያዚያ 04/2012 ዓ.ም ተከብሮ የዋለውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በጽሕፈት ቤታቸው ድረ ገጽ በኩል ባስተላለፉት መልዕክት የብርሃነ ትንሳኤውን በዓል አጋጣሚ በመጠቀም እያንዳንዳችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስጋ ምን እንደሆነ በጥልቀት ማሰላሰል ይስፈልጋል ብለዋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ሲባል የዘንድሮን ብርሃነ ትንሳኤን በዓል ምዕመናን በቤታችን ሆነው እንዲያከብሩት ተገደዋል ብለው ይህም ምዕመናን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስጋው እና ከብር ደሙን በአካል ተገኝተው እንዳይቀበሉ ማድረጉን በመልዕክታቸው አስታውሰዋል።

በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ መረጋጋትን ለማግኘት መጸለይ ያስፈልጋል በማለት ለምዕመናን የማበረታቻ ምክራቸውን የሰጡት  ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ ከአቅማችን በላይ የሆነው በትዕግስት መቀበል እንዳለብን፣ መለወጥ የምንችለውን ለማከናስወን ድፍረት እንዲኖረን እና ልዩነትን ለይተን ለማወቅ ጥበብ እንዲኖረን፣ እምነታችንን እና የትንሳኤውን ምስጢር በሚገባ ለማወቅ የሚያስችለን የአስቸጋሪ ጊዜ ምንነት በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል።        

በብርሃነ ትንሳኤው በዓል መልዕክታቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተይዘው የሚሰቃዩትን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ ወረርሽኙ ባሁኑ ሰዓት ብዙዎችን ለከፍተኛ ስቃይ መዳረጉን ገልጸው፣ ስለዚህም የየአገራቱ መንግሥታት ለዜጎች በሙሉ የተሟላ የጤና እንክብካቤን እና የመከላከያ መንገዶችን እንዲያመቻችላቸው አደራ ብለው የመንግሥት መሪዎች የወረርሽኙን አስከፊነት በመገንዘብ አንድነትን በመፍጠር የጋራ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ አክለውም መሪዎቻችን በሕዝቦች መካከል አንድነት እንዳይኖር በሚያደርጉበት ጊዜ የሚፈጽሙትን ስህተት ይረዱታል ወይ በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

ቤተሰብዓዊ አንድነት ከምን ጊዜም ጎልቶ በሚታይበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ያሉት ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዓለማችን ላይ የደረሰው ስቃይ አንዳችን ለአንዳችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆንን ለማወቅ አስችሎናል ብለዋል። በሌላ ወገን ከሦስት ወራት በፊት ያላሰብነው ለውጥ እየታየ መጥቷል ያሉት ካርዲናል ሉዊስ ታግለ፣ የተገኘው ለውጥም የከባቢ አየር ብክለት መቀነሱን እና የምንተነፍሰው አየር ጥራት መጨመሩን አስታውሰው ከዚህም በተጨማሪ በጦርነት እና በመጽ መካከል የቆዩ አንዳንድ አገሮች ወደ ተኩስ አቁም ስምምንተ መድረሳቸውን አብስረዋል። ምንም እንኳን እነዚህ ለውጦች ለጊዜው ቢሆንም ዞሮ ዞሮ የማይቃለሉ የሚመስል የሰው ልጅ ችግር ጊዜያዊ እንጂ ዘለዓለማዊ እንዳልሆነ መረዳት ችለናል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስም ከትንሳኤው በፊት ለጥቂት ቀናት ብቻ በመቃብር ውስጥ ቆይቷል ብለው ተስፋ ካለ ሞት የመጨረሻ ውሳኔን አለመሆኑን ለመረዳት ችለናል ብለዋል።

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ እና ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ዘንድ በሚያዚያ 04/2012 ዓ.ም ተከብሮ የዋለውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት ከማጠቃለላቸው በፊት፣ በጎ አድራጊ ድርጅታቸውን በሚችሉት መንገድ ሁሉ ድጋፋቸውን የሚያያቀረቡትን ለጋሽ ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን፣ የድርጅታቸው ሰራተኞችን፣ ለታመሙት የሕክምና እርዳታን በማድረግ ላይ የሚገኙ በጎ ፈቃደኞችን በሙሉ አመስግነዋቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው ሁለተኛ ምልዕክቱ ምዕ. 5: 14 ላይ የክርስቶስ ፍቅር ለሥራ ይገፋፋናል ያለውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ አነሰም በዛ በፍቅር ተነሳስተን የምናሳየው ተስፋ በመካከላችን አንድነትን በማሳደግ ወደ አዲስ የሕይወት ጎዳና እንደሚያሸጋግረን ገልጸው እንደ ኮሮና ቫይረስ እምነት ተስፋ እና ፍቅር ድንበር የሌላቸው መሆኑ አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ከዚህ በፊት ባስተላለፉት መልዕክት ወረርሽኙ ሕይወትን ማጥፋት ሲጀምር በመጀመሪያ የግል ሕይወትን ቀጥሎም ስለ ቤተሰባችን ሕይወት ቀጥሎ በቅርብ ስለምናውቃቸው ሰዎች እንድንጨነቅ ማድረጉ ተፈጥሯዊ ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ የራሳችንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት ለማዳን ብለን የተቻለንን ሁሉ ማድረግ መልካም ተግባር ነው ብለው የሌሎችን ስቃይ እንደራሳችን አድርገን መቁጠር ያስፈልጋል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ በማከልም ምናልባት በጣም በምንጨነቅበት ጊዜ ለሌሎች ማሰብን አቁመን ለራሳችን  ብቻ እናስብ ይሆናል ብለው አሁን በምንገኝበት አስጨናቂ ጊዜ ግን አደጋው ሁላችንንም የሚያጠቃ በመሆኑ አንዱ ለሌላው ፍቅርን እና ርህራሄን በተግባር መግለጽ ያስፈልጋል ብለዋል። በድንገት የተከሰተ አደጋ በመሆኑ መዋጋትም የምንችለው ተመጣጣኝ የሆነ ድንገተኛ ተስፋን በመሰነቅ ነው ብለው ድንገተኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ ድንገተኛ በጎ ተግባራት እንድናከናውን አድርጎናል ማለታቸው ይታወሳል።

14 April 2020, 20:56