ፈልግ

አስራ አራቱ የመስቀል መንገድ አስራ አራቱ የመስቀል መንገድ 

አስራ አራቱ የመስቀል መንገድ ማረፊያዎች ከቆዩት የካቶሊክ ቤተሰብ ሃይማኖታዊ ቅርሶችና ልምዶች አንዱ

 

 

ወደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስንገባ በግድግዳዉ ላይ የተሰቀሉ 14 ሥዕሎችን እናገኛለን፤ እነሱም 14ቱ የመስቀል መንገድ ጸሎት ማረፊያዎች ናቸው። እነዚህ 14ቱ ሥዕሎች ክርስቶስ ከጲላጦስ ቤተመንግስት እስከ ሞተበት የጎልጎታ ኮረብታ ድረስ ያሳለፈዉን ሥቃይና መከራ የሚያሳዩ ዋና ዋና ክስተቶችን የያዙ ናቸዉ። እኛ ካቶሊኮች በተለይም በዐርባ ጾም  ወቅት ይህን የመስቀል መንገድ ጸሎት ማድረግ እንወዳለን፣ ይህን በማድረጋችን ክርስቶስን በጎልጎታ ጉዞ እናጅባለን፣ በእርግጥ ህመማችንንና ሥቃያችንን የተጋራው ክርስቶስ ራሱ ነው፤ ሥቃዩ ሥቃያችን ሞቱም ሞታችን ነውና። ይህን ጸሎት ስናደርግ ከክርስቶስ ጋር ከጨለማና ከሞት ወደ ትንሳኤው ብርሃን እንሻገራለን፡፡

አንደኛ ማረፊያ፡ ክርስቶስ ሞት ተፈረደበት

ምናልባት አንዳንድ ጊዜ እኛ በሌሎች በውሸት እንከሰስና ይፈረድብን ይሆናል፤ በእንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ክርስቶስን እናስብ።

ሁለተኛ ማረፊያ፡ ክርስቶስ መስቀሉን ለመሸከም ተቀበለ

ሁላችንም በህይወታችን የምንሸከመው መስቀል፤ህመም፤መከራ፤ችግር አለን፡፡

ሶስተኛ ማረፊያ፡ ክርስቶስ በመስቀሉ ሥር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደቀ

ሁላችንም መስቀላችንንና ችግራችንን ከአቅማችን በላይ ሆኖ የሚሰማን ጊዜ አለ፤ አቅቶን የምንወድቅበትም ጊዜ አለ፤ ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር እንደገና ተነስተን መንገዳችንን እንቀጥላለን፡፡

አራተኛ ማረፊያ፡ ኢየሱስ ከእናቱ ከማርያም ጋር በመንገድ ተገናኘ

ማርያም ሁላችንንም በችግራችንና በሥቃያችን ጊዜ ሁሉ ልትረዳን ዝግጁ ናት፡፡

አምስተኛ ማረፊያ፡ ቀሬናዊው ስምዖን የክርስቶስን መስቀል በመሸከም ረዳ

በዚህ ማረፊያ በችግራችን ጊዜ ስለሚረዱን ሰዎች እግዚአብሔርን እናመሰግናለን።

ስድስተኛ ማረፊያ፡ቬሮንካ የምትባል ሴት ፊቱን ጠረገችለት

የተቸገሩ ሰዎችን በምንረዳበት ወቅት ሁሉ የክርስቶስ ፊት በፊታችን ላይ ይታተማል።

ሰባተኛ ማረፊያ፡ ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ወደቀ

እኛም ደግመን ደጋግመን በተመሳሳይ ኃጢአት ወይም ችግር ላይ እንወድቃለን፤ ነገር ግን ከኢየሱስ ጋር እንደገና ከወደቅንበት ተነስተን መንገዳችንን እንቀጥላለን፡፡

ስምንተኛ ማረፊያ፡ ኢየሱስ የኢየሩሳሌምን ሴቶች አጽናና

በኃጢአታችን፤በመከራችን፤ በችግራችን ላይ ማልቀስ አለብን፤ ነገር ግን ኢየሱስ ሥቃያችንንና ሞታችንን አብሮን ስለሚሸከም ልንጽናና ይገባናል፡፡

ዘጠነኛ መረፊያ፡ ኢየሱስ ለሦስተኛ ጊዜ ወደቀ

አንዳንዴ በሕይወታችን በሚከሰቱ ችግሮች እንደ ህመም፤ሥቃይና፤ ተስፋ መቁረጥ በሚያጋጥመን ጊዜ ባዶነት ይሰማናል ሆኖም ያለ ኢየሱስ የእኛ ሁኔታ ተስፋ የሌለው ነው፤ ነገር ግን ከሱ ጋር ስንሆን መከራችን ምንም ያህል ከባድ ቢሆንም እን£ን መሸከም እንችላለን፡፡

ዐሥረኛ ማረፊያ፡ ኢየሱስ ልብሶቹን ተገፈፈ

አንድ ቀን ምናልባት መልካም ስማችንንና ያለንን ሁሉ ልንገፈፍ እንችላለን፣ ያ ወቅት ግን ከተረሳውና ያለውን ሁሉ ከተገፈፈው ከክርስቶስ ጋር ፍጹም አንድነትን የምንመሥርትበት ወቅት ሊሆን ይገባል፡፡

አሥራ አንደኛ ማረፊያ፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተቸነከረ

በሽታ ወይም ዕድሜ በአልጋ ለይ የሚቸነክረን ወቅት ይመጣል፣ ከክርስቶስ ጋር አንድ ሆነን ግን ፍቅራችንን ለእግዚአብሔር፤ ሕይወታችንን ለወንድሞቻችንና እህቶቻችን አገልገሎት ማቅረብ እንችላለን፡፡

አሥራ ሁለተኛ ማረፊያ፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ሞተ

በሞታችን ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ሆነን “አባት ሆይ! ነፍሴን በእጆችህ አደራ እሰጣለሁ” እያልን እንጮሃለን፡፡

አሥራ ሦስተኛ ማረፊያ፡ ኢየሱስን ከመስቀል አወረዱት

ከሥልጣናችንና ከነበርንበት ደረጃ ሙሉ በሙሉ የምንወርድበት ጊዜ ይመጣል፤ ሕይወት ወደ ፍጻሜ ትመጣለች፣ ስለዚህ ወደ ዘላለማዊ ጥበብ በእግዚአብሔር ዘንድ የማያልቅ ዋጋ ስላለው ነገር እንዲያስተምረን መጸለይ አለብን፣

አሥራ አራተኛ ማረፊያ፡ ኢየሱስ ተቀበረ

መቃብር ለእኛ ለክርስቲያኖች ወደ አዲስ ሕይወት መግቢያ በር ነው፣ በመቃብራችን ውስጥ ለብቻችንን አንቀበርም፤ ክርስቶስ በኋላ ወደ አዲስና የክብር ሕይወት ሊወስደን አብሮ ከእኛ ጋር ወደ መቃብር ይገባና በጎናችን ሆኖ ይቆያል፡፡

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

06 March 2020, 10:26