ፈልግ

በእናት ማሕጸን ውስጥ የሚገኝ ጽንስ መብት በእናት ማሕጸን ውስጥ የሚገኝ ጽንስ መብት  

የኒዩዚላንድ ብጹዓን ጳጳሳት በእናት ማሕጸን ውስጥ የሚገኝ ጽንስ መብት እንዲጠበቅ አሳሰቡ።

የኒዩዚላንድ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ፣ የአገራቸው መንግሥት ጽንስን በማስወረድ መብት ላይ ያለው ለዘብተኛ አቋም እጅግ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። የኒውዚላንድ መንግሥት ምክር ቤት ካለፉት ወራት ጀምሮ ሲያካሂድ በሰነበተው ጠቅላላ ጉባኤው፣ ጽንስን የማስወረድ ተግባር ተፈጻሚ እንዲሆን የሚያስችል ሕግ በማርቀቅ ላይ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል። ሕጉ ጽንሱ ማደግ ከጀመረ ከሃያ ሳምንታት በፊት ባሉት ጊዜያት፣ በእናት ምርጫ እና ጥያቄ መሠረት ማስወረድ የሚያስችል መሆኑ ታውቋል። ከዚህ በፊት በነበረው ሕግ መሠረት ከሆነ ፣ ከሃያ ሳምንታት በኋላ ፣ በሕክምና ባለሞያ ድጋፍ፣ በእናት የአካል እና የአእምሮ ጤና ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሲባል ጽንስን ማስወረድ የተከለከለ ሆኖ መቆየቱ ታውቋል። የኒይዚላንድ መንግሥት ከዚህ በፊት ከነበረው ሕግ በተለየ፣ በእናት ማሕጸን ውስጥ የሚገኝ ጽንስ የአካል ጤና ይዘት ያልተስተካከለ ሆኖ ሲገኝ እና የእናትም የአካል እና የአእምሮ ጤና ሁኔታ አደጋ ላይ የሚገኝ ከሆነ ጽንስን የማስወረድ መብት ሕጋዊ እንዲሆን የሚያደርግ ሆኖ እንደሚቀርብ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አቋም፣

የኒዩዚላንድ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በድረ ገጹ ይፋ ባደረገው ነባር አቋሙ እንዳስታወቀው ሕጉ የሚጸና ከሆነ፣ ገና በጽንስ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሕጻናት በሕይወት የመቆየት መብታቸውን መገፈፋቸው እንዳሳሰበው ገልጿል። በኒውዚላንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሐምልተን ሀገረ ስብከት ማሕበራዊ ፍትህ ጽሕፈት ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ ሲንቲያ ፒፔር እንዳስታወቁት፣ ገና ሳይወለድ በእናት ማሕጸን ውስጥ የሚገኝ ሕጻን እንደሌላው የቤተሰብ አባል መብቱ የተጠበቀ መሆን አለበት ብለዋል። በእናት ማሕጸን ውስጥ የሚገኝ ሕጻን ሰብዓዊ ማንነቱ የተረጋገጠ መሆኑን ሕግ ሊገነዘብ ይገባል ብለው፣ ባሁኑ ወቅት በኒውዚላንድ የመንግሥት ምክር ቤት ለውይይት የቀረበው የጽንስ ማስወረድ ሕጋዊነት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል።

በፍላግት እና የሚደረግ ውርጃ፣

ከዚህ በፊት በነበረው ሕግ መሠረት ፣ በእናት ፍላጎት እና ምርጫም ቢሆን የሃያ ሳምንታት ዕድሜ ያለውን ጽንስ ፣ በሕክምና ባለሞያ ድጋፍ ማጨናገፍ ይቻላል የሚለውን ሕግ ቤተክርስቲያኒቱ የማትቀበል መሆኑን ወይዘሮ ሲንቲያ ፒፔር አስታውቀዋል። በዚህም መሠረት በአካል ላይ ጉዳት የሚታይበት ጽንስ እንኳ ሳይቀር፣ በሕይወት የመኖር መብቱን አዲስ የሚረቀቅ ሕግ እንዲያስከብርለት ጠይቀዋል። በኒውዚላንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሐምልተን ሀገረ ስብከት ማሕበራዊ ፍትህ ጽሕፈት ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ ሲንቲያ ፒፔር በማከልም በሕክምና ባለሞያዎችም በኩል በጽንስ አካል ላይ የሚደረግ የአካል ምርመራም ትክክል አለመሆኑን አስረድተው አዲሱ ሕግ ሃያ ሳምንት ባልሞላ ጽንስ ላይ የሚደረገውን የአካል ብቃት ምርምርራ ሕጋዊ እንዳያደርግ ጠይቀዋል።

ቤተሰብን የሚያጋጥም ችግር ማስወገድ መሞከር፣

የሐምልተን ሀገረ ስብከት ማሕበራዊ ፍትህ ጽሕፈት ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ ሲንቲያ ፒፔር፣ የኒውዚላንድ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ስጋት በማስረዳት እንደተናገሩት፣ በአገራቸው ውስጥ አንድ ሴት ሳትዘጋጅበት የሚያጋጥማት እርግዝና ማሕበራዊ ውጥረትን እና ቤተሰባዊ ጫናን የሚያስከትል መሆኑን ገልጸው፣ እርጉዝ እናቶች ከመንግሥት በኩል ከፍተኛ ድጋፍ እና እርዳታ የሚደረግላቸው ቢሆን ኖሮ ጽንስን ወደ ማስወረድ ውሳኔ አይደርሱም ነበር ብለዋል። ነገር ግን አዲስ የሚረቀቀው ሕግ ይህን ሕቅ ያልተገነዘበ መሆኑን አስረድተው፣ ሕጉ ሥራ ላይ ውሎ ተፈጻሚነትን የሚያገኝ ከሆነ፣ ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚታይ ውጤት አሉታዊ ፋይዳ ያለው እንደሚሆን እና በርካታ ሴቶችም እርግዝናቸውን ለማቋረጥ የሚገደዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
02 March 2020, 16:30