ፈልግ

በሶርያ ከሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ስፍራዎች ማካከል አንዱ፣ በሶርያ ከሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ስፍራዎች ማካከል አንዱ፣ 

በሶርያ ውስጥ የሚካሄዱ ግጭቶች እንዲቆሙ ጥሪ ቀረበ።

በሶርያ ውስጥ ለስደተኞች ዕርዳታን በማዳረስ ላይ የሚገኝ የኢየሱሳዊያን ማሕበር በሶርያ ውስጥ ያሉ የእርስ በእርስ ግጭቶች እና ጦርነቶች እንዲያበቁ በማለት ጥሪ አቀረበ። የኢየሱሳዊያን ማኅበር የስደተኞች መርጃ ተቋም፣ በሶርያ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ዘጠነኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፈው ጥሪ፣ የበርካታ ሰዎች ሕይወት የጠፋበት፣ በርካቶችም አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እና ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ የተገደዱበት አስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያበቃ ጥሪ አቅርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኢየሱሳዊያን ማኅበር የስደተኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል እንደ ጎርግሮሳዊያኑ አቆጣጠር ከ2011 ዓ. ም. ጀምሮ በሶርያ እና አካባቢው አገሮች ለሚገኙት ስደተኞች እና ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ዕርዳታን ሲያቀርብ መቆየቱ እና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሚደርሰውን መፈናቀል፣ ስደተት እና ስቃይ ሲያሳውቅ መቆየቱ ታውቋል።

እጅግ የሚያሳዝን ነው፣

አገልግሎት መስጫ ተቋሙ እሑድ መጋቢት 6/2012 ዓ. ም. የሶርያን ጦርነት ዘጠነኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ በድረ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፉ፣ በሶርያ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ባለው ስቃይ እጅግ ማዘኑን ገልጾ፣ ለሰላማዊ ዘጎች፣ ሕጻናት እና እናቶች ከለላ እንዲደረግላቸው ጠይቆ፣ የእርስ በእርስ ግጭትም በአስቸኳይ እንዲቆም በማለት ጥሪውን አስተላልፏል።

የመፍትሄ ሃሳብ፣

የኢየሱሳዊያን ማኅበር የስደተኞች አገልግሎት መስጫ ተቋም በጽሑፉ ፣ በግጭት እና ጦርነት ምክንያት በሶርያ እና አካባቢው አገሮች ለተፈናቀሉት እርዳታን ማዳረስ የተልዕኳቸው ቀዳሚ ዓላማ መሆኑን ገልጾ፣ ለተፈናቃዮች የትምህርት፣ የስነ ልቦና ድጋፍ፣ የስልጠና እና የአደጋ ጊዜ እርዳታን መስጠት እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የወቅቱ ስጋት፣

በሶርያ እና በአካባቢው የተቀሰቀሱት አዳዲስ ግጭቶች እና ጦርነቶች እጅግ እንዳሰጋው የገለጸው ተቋሙ፣ በሰዎች ላይ ሊደርስ የሚችለው አደጋ ከፍተኛ እንደሚሆን አስታውቆ፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት “በሕዝቡ ላይ ከረጅም ጊዜ አንስቶ የወደቁ መከራዎች የሚያደርሱትን ተፅእኖ እንዲያስቡ ጥሪ አቅርቧል። በሶርያ ውስጥ ከቅርብ ወራት ጀምሮ የተቀሰቀሱት አዳዲስ ግጭቶች የሰው ሕይወት ከማጥፋት እና መፈናቀልን ከማስከተል ሌላ ለሶርያ እና ለአካባቢው ሕዝብ ምንም የሚፈይዱት ነገር የለም ብለዋል።

የኢየሱሳዊያን ማኅበር የስደተኞች መርጃ ተቋም፣ የሶርያ ጦርነት ዘጠነኛ ዓመት መታሰቢያ የሰላም ጥሪ መልዕክት ሲያጠቃልል፣ በጎ ፈቃድ ያላቸው ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች በሙሉ፣ ተቋሙ በሶርያ ውስጥ ለሚያበረክተው የሰብዓዊ ዕርዳታ አገልግሎት፣ የሰላም እና የዕርቅ ተግባር ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ አደራ ብሏል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
17 March 2020, 16:41