ፈልግ

በዐብይ ጾም ወቅት በእለተ አርብ እለት የክርስቶስ ሕማም በማስታወስ የመስቀል መንገድ ጸሎት ይደረጋል በዐብይ ጾም ወቅት በእለተ አርብ እለት የክርስቶስ ሕማም በማስታወስ የመስቀል መንገድ ጸሎት ይደረጋል  

በስቅለተ ዓርብ የክርስቶስን መስቀል በልዩ ሁኔታ እናከብራለን፤ ለሱ ያለንን ፍቅርና አክብሮት እንገልጻለን

በመሰቀል ላይ የተሰቀለውንና የቆሰለውን ክርስቶስ ማስታወስ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ እና ተስፋ በሌለው ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሰዎች ትልቅ ተስፋና ማጽናኛ ነው።

በሥቅለተ ዓርብ ዕለት ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ለይ ተሰቅሎ መሞቱን እናስባለን፣ በዚህ ዕለት እኛ ካቶሊኮች መስቀልን በልዩ ሁኔታ የምናከብረው፣ አከባበሩም የሚፈጸመው በሚከተለው ዓይነት ነው።

-   ትልቅ መስቀል የወይን ጠጅ ቀለም ባለው ጨርቅ ተሸፍኖ ካህኑ ከፍ አድርጎ ተሸክሞት ወደ ቤተክርስቲያን ይገባል።

-   ካህኑ መሸፈኛ ጨርቁን እያነሳ ሶስት ጊዜ “እነሆ ዓለምን የሚያድን ጌታ የተሰቀለበት የእንጨት መስቀል” እያለ ይዘምራል፤እንዲህ እየዘመረ ቤተክርስቲያኑን አቋርጦ ያልፋል።

-   ምዕመናኑ ደግሞ በጉልበታቸው ተንበርክከው «ኑ ለእርሱ እንስገድለት» እያሉ ይመልሳሉ።

-   መሸፈኛ ጨርቁ ሙሉ በሙሉ ከተነሳ በኋላ ምዕመናኑ አንድ በአንድ ወደፊት እየመጡ በመስቀሉ አጠገብ በመንበረከክ፤ በእጃቸዉ በመንካት ወይም በመሳም መስቀሉን ይሳለማሉ።

አንዳንድ ሰዎች ምናልባት መስቀሉን እንዲህ ባለ ሁኔታ በማክበራችን የእንጨት  መስቀልን በመንበርከክና በመሳምም ጭምር ታመልካላችሁ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፣ ለእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች በአክብሮት እንዲህ እያልን እንመልሳለን። “እኛ ካቶሊኮች የእንጨት መስቀልን አናመልከም፤ እኛ የምናመልከው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእኛ መካከል የሚኖረውንና ህያው የሆነውን ክርስቶስን ነው፣ ስለሆነም “ኑ ለእንጨት መስቀል እንስገድለት” አንልም፡ ይልቁንም “ ለርሱ (ለክርስቶስ) እንስገድለት” ነው የምንለው፤ በመካከላችን ለሚገኘው ለክርስቶስ እንስገድለት ማለታችን ነው፣ መስቀል ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ለእኛ ያሳየውን ትልቅ ፍቅር ያስታውሰናል። ልባችንንና አእምሮአችንን ወደዚህ ሀሳብ ያነሳሳናል፣ ክርስቶስን በልባችንና በአእምሮአችን በመያዝ ለእርሱ ሰግደን እሱን እናመልካለን እንጂ እፊት ለፊታችን የሚታየውን መስቀሉ የተሠራበትን የሞተ እንጨት አይደለም፣ በየዕለት ሕይወታችን የሚሆኑ ነገሮች እዚህ ላይ ማሰብ እንችላለን፡ ለምሳሌ አንዲት ሙሽሪት በድንገተኛ አደጋ የሞተባትን የባሉዋን ፎቶ ልትስም ትችላለች፤ ታድያ በዚህ ሰዓት ይህች ሴት የምትስመውና የምትወደዉ ፎቶው የታተመበት ወረቀትን ሳይሆን ያንን ውድ ባሉዋን ነው፤ ፎቶው ያንን ወድ ባሏን እንድታስተውስ እንድትስመውና እንድትወደው የሚረዳት መሣሪያ ብቻ ነው።

ሰዎች የተሰቃየውንና የተሰቀለውን የክርስቶስን አካል ምስል በመስቀል ላይ የሚያኖሩት ለምንድነው?

ክርስቶስ ከሞተ እስከ ብዙ መቶ ዓመታት ድረስ ክርስቲያኖች መስቀልን ያከብሩት የነበረው የተሰቀለው ክርስቶስ የሌለበትን ሌጣውን መስቀል ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሌጣውን መስቀል በተለያዩ ውብ ድንጋዮች ያጌጡ ነበር፣ ይህም ክርስቶስ ከሙታን መነሳቱንና ሕያውነቱን ለመግለጽ ነው፣ ነገር ግን  በ11ኛው ክፍለ ዘመን “ጥቁር ሞት” እየተባለ የሚጠራው አደገኛና ገዳይ ወረርሽኝ በአውሮፓ አህጉር በገባ ጊዜ ሰዎች በዚያ በገዳይ ቁስሎች ተከበው ክርስቶስን በመስቀል ላይ ከነቁስሉና ከነስቃዩ ያስታውሱት ነበር። በመስቀል ላይ እንዲህ የቆሰለውና የተሰቃየው ክርስቶስ በጎናቸው እንዳለ ከእርሱ ጋር አብሮ እንደሚሰቃይና እንደሚሞት ይሰማቸው ነበር፣ በዚህ ምክንያት ነው የቆስለውንና የተሰቃየውን የክርስቶስ አካል ምስል በመስቀል ለይ ማኖር የተጀመረው።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

06 March 2020, 10:48