ፈልግ

የመጋቢት 20/2011 ዓ.ም ዘገብር ኄር እለተ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.     2ጢሞ 2፣1-15

2.     1ጴጥ 5፣1-11

3.     ሐዋ ሥራ 1፣6-8

4.      ማቴ 25፣14-30

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የሰነፉ አገልጋይ ምሳሌ

 “የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጒዞውን ቀጠለ። አምስት ታላንት የተቀበለው ሰውዬ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት ታላንት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ።

“የአገልጋዮቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ። አምስት ታላንት የተቀበለውም፣ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ! አምስት ታላንት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ አምስት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው። “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።

“እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው። “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “አንድ ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ ታላንትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው።

“ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ አገልጋይ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሮአል? ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር።

“ ‘በሉ እንግዲህ ታላንቱን ወስዳችሁ ዐሥር ታላንት ላለው ስጡ፤ ላለው ይጨመርለታል፤ የተትረፈረፈም ይኖረዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።ይህን የማይረባ አገልጋይ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት’ አለ።

የእለት አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘገብር ኄር የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን ፡፡ በዚህም ሰንበት እግዚአብሔር ስላደረገልን ነገር ስለሰጠን ስጦታ የምናስብበትና እርሱንም የምናመሰግንበት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰው አድርጎ ስለፈጠረን ብቻ ሳይሆን ከውልደት አንስቶ እስከ ዳግም ውልደት ከእኛ ጋር በመሆን በሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ከጎናችን በመቆም ልክ እንደ ኣባትና እናት ሆኖ ስለሚከባከበን ነው።

በዛሬው የመጀመሪያ ንባብ ማለትም 2ጢሞ 2፣ 1-15 ባለው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “በርታ” በማለት የምክር ቃሉን ሲለግሰው እናያለን። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በርታ የሚለው በራስህ ኃይል በራስህ ጉልበት የነቃህ ወይም የበረታህ ሁን ለማለት ሳይሆን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው ጸጋ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው ኃይል በርታ ማለቱ ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዋርያት ሥራ ም 1፣8 ላይ ለሐዋርያቱ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን እንደሚቀበሉ ብርታትን እንደሚቀበሉ ነግሮአቸዋል ስለዚህ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በርታ ሲለው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው ጸጋና ከመንፈስ ቅዱስ በሚገኘው ኃይል  ተንቀሳቀስ ማለቱ ነው፡፡ ይህ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር ዛሬ ለእኔና ለእናንተም ያገለግላል የእኔ ማንነት ዕውቀቴም ይሁን ጥንካሬዬ ሁሉ የመጣው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሚመነጭ ነፃ የጸጋ ስጦታ መሆኑን በመገንዘብ ዘወትር ለሱ ምስጋናና ውዳሴ ልናቀርብለት ይገባል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠውን ምክር ለራሱ ብቻ አንዲይዘው ሳይሆን ይህንን ምክር ለሌሎችም አንዲያስተላልፍ ኣደራ ብሎታል፡፡ ይህም የሚያስገነዝበን እያንዳዳችን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምንቀበለው ጸጋ ለግላችን ጥቅም ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የዚህ ጸጋ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ውስጣችንን ክፍት ማድረግ ይጠበቅብናል ይህ የምንቀበለውን ጸጋ ለሌሎች የማካፍል ለሌሎች የማስተላለፍ ግዴታ ይኖረናል በዚህ ኣኳሃን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከኣንዱ ወደ ኣንዱ በቀላሉ ይተላለፋል ማለት ነው ፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በአኛው ጢሞቴዎስ 2፡3-4 ላይ እንደጠቀሰው ቁርጠኛ ወታደር በመሆን መከራን ሁሉ በትዕግሥት አንዲያሳልፍ አንደመከረው እኛም ሁላችን በተቀበልነው ምስጢረ ሜሮን ኣምካኝነት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወታደሮች ሆነናልና አንደ ታማኝ ወታደር ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ትገዢዎች በመሆን ስለ ክርስቶስ ፍቅር ስንል በነገሮች ሁሉ ትዕግሥት በማድረግና የዓለምን ምኞት ሁሉ ወደኃላ በመተው መኖር ይገባናል፡፡ በዚህ መልኩ የምንኖርና የምንንቀሳቅስ ከሆነ ልክ ለዓላማውና ለስልጠናው ታማኝ እንደሆነ እንደ ትጉ እስፖርተኛ የድል ኣክሊል ተቋዳሾች እንደ ትጉ ገበሬም የመጀመሪያ የፍሬው ተካፋዮች እንሆናለን፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንድሚለው ምን ኣልባት እውነትን በመናገራችን እውነትና የእውነት መንገድ የሆነውን ክርስቶስ በመስበካችን ብዙ በደልና እንግልት ሊደርስብን ይችል ይሆናል ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንደሚነግረን የእርሱ መከራ የእርሱ ስቃይ የእርሱ በደል ውስጥ ተካፋይ ሆነናልና እንዲሁ ደግሞ ኣብረን የእርሱ ነፃነት የእርሱ ደስታ የእርሱ ትንሳኤ ተካፋዮች የዘለዓለም ሕይወትም ተቋዳሾች እንሆናለን፡፡ በሮሜ 6፡3-5 እንዲህ ይላል ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ተንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን እንግዲህ ክርስቶስ በኣብ ክብር ከሙታን እነደተነሳ እንዲሁ እኛም በኣዲስ ሕይወት አንድንመላለስ ከሞቱ ጋር ኣንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን ይላል፡፡

በመጀመሪያው መልእክት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በርታ በማለት የምክር ቃሉን እንደለገሰው ሁሉ በዚህ በሁለተኛ መልእክት ሲነበብ እንደሰማነው ደግሞ ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ለቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ምክሩን ሲለግሳቸዋል እናያለን፡፡  በዮሐንስ ወንጌል 21፡15-17 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኃላ ለሐዋርያው ጴጥሮስ 3 ጊዜ በጎቹን እንዲጠብቅ በጎቹን እነዲያሰማራ ግልገሎቹን እንዲጠብቅ ትእዛዝ ሰጥቶት በነበረው መሰረት  ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በተለይም የቤተክርስቲያን መሪዎችና ሽማግሌዎች ይህንን ኃላፊነት ጠንከር ኣድርገው አንዲይዙ ለየት ባለ መልኩ ደግሞ ለምዕመናን ግንባር ቀደም ምሳሌ በመሆን ዓይነተኛ ሚና እንዲጫወቱ ምክሩን ይለግሳል፡፡

እረኛው በቃሉም በምግባሩም መልካም ከሆነ በጎቹ ሁልጊዜ ሊከተሉት ዝግጁዎች ናቸው ምክንያቱም በቃሉ የሚናገረውን በሕይወቱ እየኖረ ያሳያቸዋል እነርሱም በእርሱ ላይ የሚኖራቸው መተማመን ይጨምራል የእርሱንም ኣብነት ለመከተል ውስጣቸው ይነሳሳል፡፡

በመቀጠልም ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ወጣቶቸ እንዲሁም ጎልማሶች ለሽማግሌዎች አንዲታዘዙ ሁልጊዜም በትሕትና እንዲጓዙ ምክሩን ይለግሳል ምክንያቱም ትሑት የሆነ ሰው ኣለኝ የሚለው ወይም የሚመካው በ1ኛቆሮ 15፡ 10 ላይ እንደምናገኘው በራሱ ጉልበትና ኣቅም ላይ ሳይሆን በእግዚኣብሄር ጸጋና ከእርሱ ከሚያገኘው ኃይል ነው፡፡ ትሕትና ዋናው የሰይጣንን ባሕሪ ትዕቢትን ኣሽቀንጥሮ ለመጣል የሚያገለግል ዓይነተኛ መሳሪያችን ነው፡፡ በትሕትና የተሞላ ሰው ምንጊዜም ቢሆን ራሱን ዝቅ ለማድረግ ኣይከብደውም ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሰው እግዚኣብሄርን ከፍ ያደርጋል ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሰው ደግሞ እግዚኣብሄርን ዝቅ ያደርጋል በዚህም ምክንያት በመጽሐፈ ምሳሌ 3፡34 ላይ እንደተጻፈው ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሰው ካለበት ከፍታ ላይ እግዚኣብሄር ራሱ ዝቅ ያደርገዋል ይላል፡፡ ሰይጣን ከነበረበት ከከፍተኛ የመላእክት ማዕረግ የወረደው በትዕቢቱ ራሱን ከእግዚኣብሄር ጋር ማስተካከል በመፈለጉ ነው ኣዳምና ሔዋንም ዋናው ኃጢኣታቸው በትዕቢት እንደ እግዚኣብሄር መሆን መፈለጋቸው ነው፡፡

ሌላው ትዕቢትን ማስወገጃ መሳሪያቸን በመጠን መኖር ነው በመጠን የሚኖር ሰው ራሱን በብዙ መልኩ ስለሚቆጣጠር ሰይጣን ወደ ውስጡ እንዲገባ ክፍተት ኣይፈጥርም በዚህ ሁኔታ ራሱን ከኃጢኣት ምክንያት ሁሉ ያርቃል ማለት ነው፡፡ ሰይጣንን ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል በምናደርገው ጾምና ጸሎት በምናደርገው ተጋድሎ ወደ ዘለዓለማዊ ክብሩ የጠራን ኣምላክ ራሱ ጸጋ ይሰጠናል ፍጹሞች ያደርገናል ያጸናናል ያበረታንማል፡፡

በዛሬው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ላይ እንዳዳመጥነው እግዚኣብሄር ለእያንዳዳችን እንደየኣቅማችንና እንደየችሎታችን የተለያየ ስጦታ ይሰጠናል ነገር ግን በሰጠን ስጦታ ላይ በስተመጨረሻ ምን ያህል ሰርተን አንዳተረፍን ሒሳብ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ በተሰጠን ጥቂት ነገር ሰርተን ማትረፍ ከቻልን እግዚኣብሄር ኣንተ ታማኝ እና ደግ ኣገልጋይ በጥቂት ነገር ላይ ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃልና በትልቅ ነገር ላይ እሾምሃለው ይለናል። ነገር ግን በዚች በትንሿ ነገር ላይ ታማኝ ሳንሆን ብዙ ነገር ቢሰጠንም ይህንን ብዙ ስጦታ በከንቱ እንደምናባክነው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚኣብሄር በሰጠን በማንኛውም ስጦታ ደስተኞች በመሆን ያንን የተሰጠንን ስጦታ ለማሳደግና ውጤታማ ለመሆን የተቻለንን ጥረት አናድርግ፡፡

እግዚኣብሄር በሰጠን በትንሿ ስጦታ ሳንጠቀም ሳንሰራበት ቆይተን መልሰን እርሱን ብናማርር ልክ ኣንድ መክሊት እንደተቀበለው ወስዶም እንደቀበረው ኣገልጋይ ከውርደትና ወደውጭ ከመጣል ኣንተርፍም፡፡ ስለዚህ ይህ ሁሉ ከመምጣቱ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ ስጦታችን ምን መሆኑን በሚገባ እንለይ ካዛ በኃላ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን በእግዚኣብሄር ጸጋ እየታገዝን እንስራበት ካልሰራንበት ከእኛ ተወስዶ ለሌሎች ይሰጣል እኛም እንደማይረባ ቆሻሻ ወደዉጭ እንጣላለን በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፏጨት ይሆናል፡፡

ከእንዲህ ዓይነቱ ሃዘን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትታደገን ስጦታችንን በሚገባ ለማሳደግ እንድንችል ዘወትር በልጇ ፊት ታማልደን በውድቀታችንና በድካማችን ሁሉ በእግዚኣብሄር ፊት ጠበቃ ሁና ትቁምልን፡፡

ምንጭ፡ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ሀ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

27 March 2020, 14:19