ፈልግ

የመጋቢት 13/2012 ዓ.ም ሦስተኛ የዐብይ ጾም ሳምንት ሰንበት (ደብረ ዘይት) አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.      ዘጸዐት 17፡3-7

2.    መዝሙር 94

3.    ሮም 5፡1-2፣ 5-8

4.    ዮሐንስ 4፡5-42

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ስለዚህ በሰማርያ፣ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ወደ ነበረች፣ ሲካር ወደምትባል ከተማ መጣ። በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጒድጓድ ነበረ፤ ኢየሱስም ከጒዞው የተነሣ ደክሞት ስለ ነበር በውሃው ጒድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ነበር። አንዲት ሳምራዊት ሴት ውሃ ለመቅዳት ስትመጣ ኢየሱስ፣ “እባክሽ የምጠጣው ስጪኝ” አላት፤ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ለመግዛት ወደ ከተማ ሄደው ነበር።

ሳምራዊቷም፣ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ፣ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት ውሃ አጠጪኝ ትላለህ?” አለችው፤ ይህን ማለቷ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር ስለማይተባበሩ ነው። ኢየሱስም፣ “የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ፣ አንቺው በጠየቅሽው፣ እርሱም የሕይወትን ውሃ በሰጠሽ ነበር” ሲል መለሰላት።

ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ መቅጃ የለህም፤ ጒድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ ይህን የሕይወት ውሃ ከየት ታገኛለህ? ለመሆኑ አንተ፣ ይህን ጒድጓድ ከሰጠን፣ ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱ ራሱና ልጆቹ፣ እንስሳቱም ከዚሁ ጒድጓድ ጠጥተዋል።” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።”

ሴትዮዋም፣ “ጌታዬ፤ እንዳልጠማና ውሃ ለመቅዳት እንዳልመላለስ፣ እባክህ ይህን ውሃ ስጠኝ” አለችው።እርሱም፣ “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ተመለሽ” አላት። ሴትዮዋም፣ “ባል የለኝም” ብላ መለሰች። ኢየሱስም፣ እንዲህ አላት፤ “ባል የለኝም ማለትሽ ትክክል ነው፤ በርግጥ አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁን ከአንቺ ጋር ያለውም ባልሽ ስላልሆነ፣ የተናገርሽው እውነት ነው።” ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ አንተ ነቢይ እንደሆንህ አያለሁ፤ አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፤ እናንተ አይሁድ ግን ሰው መስገድ ያለበት በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ” አለችው።

ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “አንቺ ሴት፤ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ እንደሚመጣ እመኚኝ። እናንተ ሳምራውያን ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ግን ድነት ከአይሁድ ስለ ሆነ ለምናውቀው እንሰግዳለን። በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቶአል፤ አብም እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።”

ሴትዮዋም፣ “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ነገር ይነግረናል” አለችው።ኢየሱስም፣ “የማነጋግርሽ እኮ እኔ እርሱ ነኝ” ሲል ገልጦ ነገራት።

ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው መጡ

በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው መጡ፤ ከሴት ጋር ሲነጋገር በማግኘታቸው ተደነቁ፤ ሆኖም ግን፤ “ምን ፈለግህ?” ወይም፣ “ከእርሷ ጋር የምትነጋገረው ለምንድን ነው?” ብሎ የጠየቀው ማንም አልነበረም።

ሴትዮዋም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ተመለሰች፤ ለሕዝቡም፣ “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እርሱ ክርስቶስ ይሆን እንዴ?” አለች፤ እነርሱም ከከተማ ወጥተው እርሱ ወዳለበት አመሩ። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፣ “ረቢ፣ እህል ቅመስ እንጂ” አሉት።

እርሱ ግን፣ “እናንተ የማታውቁት፣ የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሰው ምግብ አምጥቶለት ይሆን እንዴ?” ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው፤ እናንተ፣ ‘ከአራት ወር በኋላ መከር ይደርሳል’ ትሉ የለምን? እነሆ፣ አዝመራው ለመከር እንደ ደረሰ ቀና ብላችሁ ማሳውን ተመልከቱ እላችኋለሁ። አጫጁ አሁንም ቢሆን እንኳ ደመወዙን እየተቀበለ ነው፤ ለዘላለም ሕይወት ይሆን ዘንድ አዝመራውን ይሰበስባል፤ ይህም ዘሪውና አጫጁ በጋራ ደስ እንዲላቸው ነው። ስለዚህ፣ ‘አንዱ ይዘራል፤ ሌላውም ያጭዳል’ የተባለው ምሳሌ እውነት ነው። ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ አድካሚውን ሥራ ሌሎች ሠሩ፤ እናንተም የድካማቸውን ፍሬ ሰበሰባችሁ።”

ብዙ ሳምራውያን አመኑ

ሴትዮዋ፣ “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ” ብላ ስለ መሰከረች፣ ከዚያች ከተማ ብዙ ሳምራውያን በእርሱ አመኑ። ስለዚህ፣ ሳምራውያኑ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ አብሮአቸው እንዲቈይ አጥብቀው ለመኑት፤ እዚያም ሁለት ቀን ቈየ። ከቃሉም የተነሣ ሌሎች ብዙዎች አመኑ። ሴትዮዋንም፣ “ከእንግዲህ የምናምነው አንቺ ስለ ነገርሽን ብቻ አይደለም፤ እኛ ራሳችን ሰምተነዋል፤ ይህ ሰው በእውነት የዓለም አዳኝ እንደሆነ እናውቃለን” አሏት።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በእዚህ አሁን በምንገኝበት ሦስተኛው ሳምንት የዐብይ ጾም ሰንበት ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ ከአንዲት ሳምራዊ ከሆነች ሴት ጋር ስላደረገው ቆይታ ይናገራል (የሐንስ 4፡5-42)። እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እየሄደ ሳለ በሰማርያ አከባቢ በሚገኘው አንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ሲደርስ እዚያው ትንሽ እረፍት ለማድረግ ቆሙ። ሳምራውያን በአይሁዳዊያን ዘንድ እንደ መናፍቃን ተደርገው ይቆጠሩ ነበር፣ እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ሆነው ይታዩ ነበር፣ በጣም የተናቁ ሰዎችም ነበሩ። በወቅቱ ኢየሱስ ደክሞት ነበር፣ ውሃም ጠምቶት ነበር። አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ በመጣች ጊዜ እርሱ “ውሃ አጠጪኝ” ብሎ ጠየቃት (የሐንስ 4፡7)። ስለዚህ እርሱ እያንዳንዱን መሰናክል በመስበር ለዚያች ሴት ሕያው የሆነ ውሃ እንደ ሚሰጣት በመግለጽ  የሕይወት ምስጢር ማለትም የእግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ የሆነውን የመንፈስ ቅዱስ ምስጢር ለሴትዮዋ ይገልጻል። በእውነቱ ለሴቲየዋ አስገራሚ ምላሽ በመስጠት ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፣ “የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ፣ አንቺው በጠየቅሽው፣ እርሱም የሕይወትን ውሃ በሰጠሽ ነበር” ሲል መለሰላት” (የሐንስ 4፡10)

የእዚህ ውይይት ዋና ነጥብ ውሃ ነው። በአንድ በኩል ውሃ በሕይወት ለመኖር መሰረታዊ የሆነ ነገር ሲሆን እሱም የአካልን ጥማት የሚያረካ እና ህይወትን የሚደግፍ ነው። በሌላ በኩል ውሃ የዘላለም ሕይወትን የሚሰጥ መለኮታዊ ጸጋ ምልክት ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በነቢያት እንደተገለፀው ሕያው የሆነ ውሃ ምንጭ እግዚአብሔር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ባህል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው፣ በተለይም ደግሞ በመዝሙረ ዳዊት እና በነቢያት መጽሐፍ ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ሕያው የሆነ የውሃ ምንጭ እግዚአብሄር ነው፣ ከእርሱ ሕያው የሆነ የውሃ ምንጭ ከሆነው እግዚአብሔር እና ከእርሱ ሕግጋት መራቅ እጅግ የከፋ ድርቀትን ያስከትላል ይሉናል። ይህ በምድረ በዳ የእስራኤል ሕዝብ ገጥሞት የነበረው ተሞክሮ ነው። ወደ ነፃነት ጎዳና በሚወስደው ረዥም መንገድ ላይ ውሃ ስለሌለ በሙሴ እና በእግዚአብሄር ላይ ማጉረምረም ጀምረው ነበር። ከዚያም በእግዚአብሔር ትእዛዝ  ሙሴ ከድንጋይ ውስጥ ውሃ እንዲፈልቅ አደረገ፣ ይህም ከህዝቡ ጋር አብሮ በመሆን ህይወትን ለሕዝቡ እንደሚሰጥ እግዚአብሔር የገለጸበት መለኮታዊ ምልክት ነው (ዘፀ 17፡ 17-7)።

ሐዋርያው ​​ጳውሎስም ያንን ዐለት እንደ ክርስቶስ ምልክት አድርጎ ተርጉሟል። በዚህ መንገድ እንዲህ ይላል: - “ዐለቱም ክርስቶስ ነው” (1 ቆሮ 10 4) በማለት ይናገራል። በርግጥ እሱ በሚራመደው በእግዚአብሔር ህዝብ መካከል መገኘቱ ምስጢራዊ አምሳያ ነው (1 ቆሮ 10፡ 4)። በእርግጥ ክርስቶስ በነቢያቱ ራእይ እንደ ተናገረው መንፈስ ቅዱስ የሚፈስበት፣ እርሱም የሚያነፃና ሕይወት የሚሰጥ፣ የሕይወት ውሃ ነው። ለመዳን የተጠሙ ሰዎች በነፃነት ከኢየሱስ ይህንን የሕይወት ውሃ ሊስቡ ይችላሉ፣ እናም መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ወይም በእርሷ ውስጥ ሙሉ እና የዘላለም ሕይወት ምንጭ ይሆናል። ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት የሰጠው የሕይወት ውሃ የፋሲካ በዓል እውነታን የሚያሳየን ሲሆን እርሱ በመስቀል ላይ በነበረበት ወቅት ጎኑን ሲወጉት ከጎኑ “ውሃ እና ደም ወጣ” (ዮሐንስ 19፡34) የሚለውን አጋጣሚ ያስታውሰናል።  ለእኛ ሲሊ የታረደው በግ እና ከሙታን የተነሳው ክርስቶስ ኃጢአትን ይቅር የሚል እና ወደ አዲስ ሕይወት የሚመልስ መንፈስ ቅዱስ የሚፈልቅበት ምንጭ ነው።

ይህ ስጦታ የምስክርነት ምንጭ ነው። እንደ ሳምራዊቷ ሴት በግል ሕይወታቸው ኢየሱስን ያገኘ  ማንኛውም ሰው ስለኢየሱስ ለሌሎች ሰዎች መናገር አስፈላጊ እንደ ሆነ ኢየሱስ ራሱ ይሰማዋል፣ በዚህም ምክንያት ስማራዊቷ ሴት ለአገሯ ሰዎች እንደ ተናግረችው ሁሉም የአገሩ ሰዎች ኢየሱስ “በእውነት የዓለም አዳኝ” (ዮሐንስ 4፡42) መሆኑን ለሁሉም ሰው እንዲመሰክሩ ተጠርተዋል።  እኛም በጥምቀት አዲስ ሕይወት ይዘን የተወለድን፣ በእኛ ውስጥ የሚገኘውን ሕይወት እና ተስፋ እንድንመሰክር ተጠርተናል። ፍለጋችን እና ጥማችን በክርስቶስ ሙሉ በሙል እርካታን ካገኘ በመጨረሻም ደህንነት የሚገኘው በእዚህ ዓለም በሚገኙ ቁስ በሆኑ ነገሮች ላይ አለመሆኑን እናሳያለን፣ ነገር ግን በሚወደን እና ሁል ጊዜም በሚወደን እርሱ ማለትም አዳኛችን ኢየሱስ እሱ በሚሰጠን ሕያው ውሃ ውስጥ እርካታ እንደ ሚገኝ እንገነዘባለን።በልባችን ውስጥ የያዝነውን የህይወትን ጥማት እና ፍቅርን ማርካት የሚችል ብቸኛ የሕይወት ውሃ ምንጭ የሆነውን የክርስቶስን ፍላጎት ለማርካት እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ትርዳን።

አቅራቢ መብራቱ ሀ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
22 March 2020, 12:26