ፈልግ

የ4ኛው የዐብይ ጾም ሳምንት (መጋቢት 20/2012 ዓ.ም )እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.      1ሳሙኤል 16:1. 6-7. 10-13

2.    መዝሙር 22

3.    ኤፌሶን 5:8-14

4.    ዮሐንስ 9: 1-41

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ፈወሰ

በመንገድ ሲያልፍም ከተወለደ ጀምሮ ዐይነ ስውር የሆነ ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ረቢ፤ ይህ ሰው ዐይነ ስውር ሆኖ እንዲወለድ ኀጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ራሱ ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እርሱ ወይም ወላጆቹ ኀጢአት አልሠሩም፤ ይህ የሆነው ግን የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ ሕይወት እንዲገለጥ ነው። ቀን ሳለ፣ የላከኝን ሥራ መሥራት አለብን፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል፤ በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ።”

ይህን ካለ በኋላ፣ በምድር ላይ እንትፍ ብሎ በምራቁ ጭቃ አበጀ፤ የሰውየውንም ዐይን ቀባና፣ “ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው፤ ሰሊሆም ማለት ‘የተላከ’ ማለት ነው። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም ተመልሶ መጣ።

ጎረቤቶቹና ከዚህ ቀደም ብሎ ሲለምን ያዩት ሰዎች፣ “ይህ ሰው ተቀምጦ ሲለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። አንዳንዶቹም፣ “በርግጥ እርሱ ነው” አሉ። ሌሎችም፣ “ይመስለዋል እንጂ እርሱ አይደለም” አሉ።

እርሱ ግን፣ “እኔው ነኝ” አለ።

እነርሱም፣ “ታዲያ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም፣ “ኢየሱስ የሚሉት ሰው ጭቃ አድርጎ ዐይኔን ቀባኝ፤ ወደ ሰሊሆም ሄጄ እንድታጠብም ነገረኝ፤ ሄጄ ታጠብሁ፤ ማየትም ቻልሁ” ሲል መለሰ። እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ያ ሰው የት አለ?” አሉት። እርሱም፣ “እኔ አላውቅም” አለ።

ፈሪሳውያን ሰውየው እንዴት እንደ ተፈወሰ ማጣራት ቀጠሉ

እነርሱም ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ኢየሱስ ጭቃ የሠራበት፣ የሰውየውንም ዐይን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበር። 15ስለዚህ ፈሪሳውያንም እንዴት ማየት እንደ ቻለ ጠየቁት። ሰውየውም፣ “እርሱ ዐይኔን ጭቃ ቀባኝ፤ እኔም ታጠብሁ፤ ይኸው አያለሁ” አላቸው።

ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ፣ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር፣ ከእግዚአብሔር አይደለም” አሉ። ሌሎች ግን፣ “ኀጢአተኛ፣ እንዲህ ያሉትን ታምራዊ ምልክቶች እንዴት ሊያደርግ ይችላል?” አሉ። በመካከላቸውም አለመስማማት ተፈጠረ።

ስለዚህ፣ ዐይነ ስውር ወደ ነበረው ሰው ተመልሰው፣ “ዐይንህን ስለ ከፈተው ሰው፣ እንግዲህ አንተ ምን ትላለህ?” አሉት። ሰውየውም፣ “እርሱ ነቢይ ነው” አለ።

አይሁድ ወደ ወላጆቹ ልከው እስኪያስ ጠሯቸው ድረስ፣ ሰውየው ዐይነ ስውር እንደ ነበረና እንዳየ አላመኑም ነበር። እነርሱም፣ “ዐይነ ስውር ሆኖ ተወልዶአል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” አሏቸው። ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ልጃችን መሆኑንና ዐይነ ስውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤ አሁን ግን እንዴት ማየት እንደቻለና ዐይኖቹን ማን እንደ ከፈተለት እኛ አናውቅም። ሙሉ ሰው ስለ ሆነ፣ ስለ ራሱ መናገር ይችላልና እርሱን ጠይቁት።” ኢየሱስን፣ ክርስቶስ ነው ብሎ የመሰከረ ሁሉ ከምኲራብ እንዲባረር አይሁድ አስቀድመው ወስነው ስለ ነበር፣ ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁድን ፈርተው ነው። ስለዚህ ወላጆቹ፣ “ሙሉ ሰው ስለ ሆነ እርሱን ጠይቁት” አሉ።

ዐይነ ስውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው፣ “አንተ ሰው፤ እግዚአብሔርን አክብር፤ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት። እርሱም፣ “ኀጢአተኛ መሆኑን እኔ አላውቅም፤ ነገር ግን ዐይነ ስውር እንደ ነበርሁ፤ አሁን ግን እንደማይ ይህን አንድ ነገር ዐውቃለሁ” አለ።እነርሱም፣ “ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዐይንህን ከፈተ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ፤ አላዳመጣችሁኝም፤ ለምን እንደ ገና መስማት ፈለጋችሁ? እናንተም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁ?” አለ።

ከዚህ በኋላ በእርሱ ላይ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ አሉት፤ “የዚህ ሰው ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛስ የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን!እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደ መጣ እንኳ አናውቅም።” ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እናንተ ከየት እንደ መጣ አለማወቃችሁ የሚያስደንቅ ነው፤ ይሁን እንጂ እርሱ ዐይኖቼን ከፈተልኝ። እግዚአብሔር የሚሰማው፣ የሚፈራውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን እንጂ፣ ኀጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዐይን የከፈተ አለ ሲባል፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ማንም ሰምቶ አያውቅም። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ይህን ማድረግ ባልቻለ ነበር።”

እነርሱም፣ “ሁለንተናህ በኀጢአት ተነክሮ የተወለድህ፣ አንተ እኛን ለማስተማር እንዴት ትደፍራለህ?” ሲሉ መለሱለት፤ አባረሩትም።

መንፈሳዊ ዕውርነት

ኢየሱስም ሰውየውን እንዳባረሩት ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ፣ “በሰው ልጅ ታምታምናለ ህን?” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታዬ፤ አምንበት ዘንድ እርሱ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አይተኸዋል፤ አሁንም ከአንተ ጋር የሚነጋገረው እርሱ ነው” አለው።

ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አምናለሁ” አለ፤ ሰገደለትም።

ኢየሱስም፣ “ዕውሮች እንዲያዩ፣ የሚያዩም እንዲታወሩ፣ ለፍርድ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ” አለ። ከእርሱ ጋር ከነበሩት ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው፣ “ምን ማለትህ ነው? ታዲያ እኛም ዕውሮች መሆናችን ነው?” አሉት።

ኢየሱስም፣ “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኀጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ስለምትሉ፣ ኀጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል” አላቸው።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

በዚህ አራተኛው የዐብይ ጾም እለተ ስንበት ስርዓተ አምልኮ ውስጥ ብርሃንን የሚመለከት ጭብጥ እናገኛለን። በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ  (ዮሐ 9፡1 -14) ኢየሱስ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ስለአዳነበት ሁኔታ ይናገራል። ይህ ተዓምራዊ ምልክት “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” (ዮሐንስ 9፡5) በማለት ኢየሱስ ጨለማን የሚያበራ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ነው። እርሱም በሁለት ደረጃዎች ብርሃናዊ የሆነ ተዐምራቱን ይሠራል፣ እርሱም በአንድ በኩል አካላዊ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ መንፈሳዊ የሆነ ተዐምር ይፈጽማል፣  ዐይነ ስውሩ የነበረው ሰው በመጀመሪያ የዐይን ብርሃን ያገኛል፣ ከዚያም በመቀጠል “የሰው ልጅ” (ዮሐንስ 9፡35) በሆነው ማለትም በኢየሱስ ማመን ይጀምራል። ዛሬ ሁላችሁም ይህንን በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ዘጠኝ ውስጥ የተጠቀሰውን ውብ ይሆነ ታሪክ ብታነቡት መልካም ነው፣ አንድ ጊዜ ወይም ደጋግማችሁ ይህንን የቅዱስ ወንጌል ክፍል ማንበብ መልካም ነው። ኢየሱስ ያደረጋቸው አስደናቂ ነገሮች አስደናቂ ምልክቶች ቢቻ አይደሉም ፣ ነገር ግን ወደ ውስጣዊ ለውጥ የማምጫ መንገድ  ወደ እምነት የመምራት ዓላማ አላቸው።

ፈሪሳውያንና የሕግ መምሕራን በስፍራው የነበሩ ሲሆን ኢየሱስ የፈጸመውን ተዓምር አምነው ለመቀበል አሻፈረን ብለው ይህ ተዓምር የተፈጸመለትን ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው በርከት ያሉ ጥያቄዎችን ያቀርቡለታል።  እሱ ግን በእውነተኛ ኃይል ተሞልቶ “አንድ ነገር አውቃለሁ፣ ዐይነ ስውር ነበርኩኝ አሁን ግን አያለሁ” በማለት ይመልስላቸዋል። በዙሪያው ባሉት ሰዎች መካከል በሚሰትዋለው ያለ ማመን ስሜት እና ጥላቻ ተሞልተው ጥያቄ ያቅርቡለት ለነበሩ ሰዎች በሚያስደንቅ ሁኔታ መልስ በመስጠት ዐይኖቹን በከፈተው እና በእርሱ ላይ እምነትን እንዲያሳድር በጠየቀው ኢየሱስን ለማመን የሚያስችለውን የጉዞ መስመር ቀስ በቀስ ይጀምራል። በመጀመሪያ እሱን እንደ ነቢይ ይቆጥረዋል ( ዮሐንስ 9፡17 ይመልከቱ)፣ ከዚያም እሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ተላከ ይገነዘባል (ዮሐንስ 9፡33)፣ በመጨረሻም እንደ መሲህ አድርጎ ተቀበለው በፊቱ ተንበርክኮ ሰገደለት (ዮሐንስ 9፡36-38)።  ኢየሱስ የማየት ችሎታውን እንዲያገኝ በማደረግ “የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጽ” (ዮሐንስ 9፡3) እንዳደረገ ተረድቱዋል።

እኛም ይህንን ተሞክሮ ተግባራዊ እናድርግ! ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደው ሰው አዲሱን ማንነቱን በእምነት ብርሃን አማካይነት ያገኛል። እሱ አሁን በሕይወቱ እና በዙሪያው ያለውን ዓለም በአዲስ ብርሃን ማየት የሚችል “አዲስ ፍጡር” ነው ፣ ምክንያቱም ከክርስቶስ ጋር ሕብረት በመፍጠሩ የተነሳ ሕይወቱ ወደ አዲስ አቅጣጫ ያመራል። እሱ ከአሁን በኋላ በማህበረሰቡ የታወቀ ምጽዋዕት ጠያቂ የእኔ ቢጤ አይደለም፣ እሱ ከአሁን በኋላ የዐይነ ስውርነት ጨለማ እና የጭፍን ጥላቻ ባሪያ አይደለም። የእሱ የተጓዘበት እና ብርሃን ያገኝበት ጉዞ እኛ የተጠራነው ከኃጢኣት ሕይወት ነፃ እንድንሆን መሆኑን የሚገልጽ ምሳሌ ነው። ኃጢአት ፊታችንን እንደሚሸፍን፣ እራሳችንን እና ዓለማችንን በግልጽ እንዳናስተውል የሚጋርደን የጨለማ መሸፈኛ ነው፣ የጌታ ይቅር ባይነት ይህንን የጨለማ ግርዶሽ በማስወገድ አዲስ ብርሃን ይሰጠናል። አሁን የምንገኝበት የዐብይ ጾም ወቅት ወደ ጌታ እንድንቀርብ እድሉን የሚፈጥርልን ወድ የሆነ ጊዜ ሊሆን የገባዋል፣ የእርሱን ምሕረት የምንጠይቅበት፣ ቤተክርስቲያን የምትጠይቀንን የተለያዩ ተግባራትን የምንፈጽምበት አመቺ የሆነ ወቅት ሊሆን ይገባዋል።

ከዓይነ ስውርነት ተፈውሶ በሁለቱም ማለትም በአካላዊ እና በመንፈስ ዐይኖቹ ጭምር ማየት የጀመረው ዓይነ ስውር የነበረ ሰው እያንዳንዱን ምስጢረ ጥምቀት የተቀበለ ሰው የሚያመልክት ሲሆን በጸጋ አማካይነት ከጨለማ ወደ ብርሃን እና ወደ እመንት የተመለሰ ሰው መገለጫ ነው።  ነገር ግን ብርሃን መቀበል ብቻ በቂ አይደለም፣ ብርሃን መሆን ያስፈልጋል። እያንዳንዳችን በሕይወታችን በሙሉ እሱን ለማሳየት መለኮታዊውን ብርሃን እንድንቀበል ተጠርተናል። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች፣ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የነበሩ የነገረ መለኮት ምሁራን የክርስቲያን ማህበረሰብ ማለትም ቤተክርስቲያን “የጨረቃ ምስጢር” ነች ይሉ ነበር፣ ምክንያቱም ብርሃንን የምትሰጥ እንጂ ራሷ ብርሃን ስላልነበረች ነው፣ የምትሰጠውን ብርሃን የተቀበለችው ራሱ በርሃን ከሆነው ከክርስቶስ በመሆኑ የተነሳ ነው። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ዛሬ እንደሚለን “ቀድሞ በጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና” (ኤፌሶን 5፡8-9) በማለት ይናገራል። በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት በውስጣችን የተቀመጠው አዲሱ የሕይወት ዘር ልክ በመጀመሪያ እኛን የሚያነጻን ፣ በልባችን ውስጥ ያለውን ክፋት የሚያቃጥል ፣ እና እንድንበራ እና ብርሃን እንድንሰጥ የሚያደርገን የእሳት ነበልባል ነው። የህም የሚከናወነው በኢየሱስ ብርሃን።

በክርስቶስ ብርሃን እንድንሞላ እና ከእርሱ ጋር በደህንነት መንገድ ላይ መራመድ እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዛሬው ቅድስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰውን ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ታሪክ እንድንላበስ በአማላጅነቷ እንድረዳን ልንማጸናት ይገባል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቡ መብራቱ ሀ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

27 March 2020, 14:38