ፈልግ

ወላጅ ቤተሰብ ከሕጻን ልጆቻቸው ጋር፤ ወላጅ ቤተሰብ ከሕጻን ልጆቻቸው ጋር፤ 

“ቤተሰብ የዓብይ ጾም ወቅትን እንዴት ያሳልፈዋል”?

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን፣ ቤተሰብን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ በማትኮር፣ ይጠቅማሉ ያልናቸውን ማሕበራዊ እና መንፈሳዊ አስተምህሮችን እናቀርብላችኋለን። ከዚህ ቀጥሎ በቀረበው አጭር ጽሑፍ “ቤተሰብ የዓብይ ጾም ወቅትን እንዴት ያሳልፈዋል?” በሚል ርዕሥ የቀረበ ጽሑፍ እናስነብባችኋለን።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን ነኝ።

በክርስትና አምልኮ ሥነ ሥርዓት መሠረት ቤተክርስቲያን በአመቱ ውስጥ የተለያዩ ቀናትን፣ ሳምንታትን፣ ወራትን ወይም ዓመታትን ለይታ በማስቀመጥ፣ ምዕመናን እነዚህን ጊዜያት በተቀደሰ መታሰቢያ እንዲያከብሯቸው ታስተምራለች ወይም ታበረታታለች። ምዕመናን በዓመት ውስጥ በተቀደሰ መታሰቢያ ከሚያከብሯቸው በዓላት መካከል አንዱ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ ነው። ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ መታሰቢያ በዓል ከመድረሳችን በፊት ወደ ግል የክርስትና ሕይወታችን ተመልሰን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ለማዳን በመስቀል ላይ የተቀበለውን መከራ እና ስቃይ የምናስብበት፣ የጽሞና፣ የጾም እና የጸሎት ጊዜን በማዘጋጀት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ምስጢር ላይ እንድናስተነትን ቤተክርስቲያን ታግዘናለች።

የክርስቲያን ቤተሰብ አባል የሆንን ሁሉ በዓብይ ጾም ወቅት የተለያዩ መልካም ተግባራትን የእኛን ድጋፍ ለሚጠይቁ ወንድሞቻችን፣ ለእህቶቻችን፣ ለምናውቃቸው ብቻ ሳይሆን ለማናውቃቸውም ሁሉ ማከናወን ወይም ማበርከት እንችላለን። የዓብይ ጾም ጊዜን ከሌሎች ክርስቲያን እና ክርስቲያን ካልሆኑ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ሆነን ከምናሳልፋቸው ዝግጅቶች በተጨማሪ በቤተሰብ ውስጥ ከወላጅ አባት እና እናት፣ ከስጋ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ሆነን በቤት ውስጥ በምናደርጋቸው  መንፈሳዊ ዝግጅቶች፣ በምናበረክታቸው መልካም ተግባራት አማካይነት በጥሩ መንገድ ማሳለፍ እንችላለን። በቤተሰብ ውስጥ አብሮ መጸለይ እና ቅዱሳት መጽሐፍትን በሕብረት ማስተንተን አንዱ የክርስቲያን ቤተሰብ መልካም ተግባር ነው። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር፣ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ከተለመደው ዕለታዊ ግንኙነት በተለየ መልኩ በመንፈሳዊነት መንገድ ተገናኝተው የሚወያዩበት፣ የሚያስተነትኑበት እና አብረው የሚጸልዩበት ጊዜ ሊኖር ይገባል። በተለይ ቤተሰብ በአንድ ሥፍራ በሚሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላቸው ያለው ቤተሰባዊ አንድነት እና ፍቅር ያድጋል። በዕለታዊ ኑሮአችን ውስጥ ከአካባቢያችን እና ከአካባቢያችን ርቀው ከሚገኙ ሰዎች ጋር ያለንን መንፈሳዊ ግንኙነት ማሳደግ አስፈላጊ ነው። በተለይ በማሕበራዊ ችግሮች ውስጥ የወደቁትን፣ የታመሙትን፣ የታሰሩትን፣ የሚበላ እና የሚጠጣ አጥተው የሚሰቃዩትን፣ ማኅበራዊ ኑሮአቸው ባላሰቡት አደጋ የተናጋባቸውን ቤተሰቦች ወይም ሰዎች መርዳት እና ድጋፍ መሆን ለሰው ልጆች በሙሉ የተሰጠ መንፈሳዊ እና ማሕበራዊ ግዴታ ነው።     

እነዚህን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንዴት ማገዝ ይቻላል የሚለውን ስንመለከት፣ እገዛችን የግድ ቁሳዊ ብቻ መሆን የለበትም። በጸሎት ማስታወስ፣ ወደሚገኙበት ሥፍራ ወይም ቤት በመሄድ መጠየቅ፣ ማጽናናት እና ሰላምታ መለዋወጥ ለሰዎች ማድረግ ከምንችልባቸው መልካም ተግባራት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።  

የአንድ ቤተሰብ አባላት አብረው ለመሆን በሚፈልጉበት አጭር ጊዜ በተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ በማስተንተን፣ የሚኖሩበትን ዓለም በጸሎት ማስታወስ፣ በሕመም፣ በጦርነት እና በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን በጸሎታቸው ማስታወስ በዚህ በጾም ወቅት ከሚደረጉ መንፈሳዊ ተግባራት መካከል አንዱ ነው። የቤተሰብ አባላት አንድ ላይ በሚሰበሰቡበት ወቅት አንዱ የሌላውን የቀን ውሎ፣ የዕለት ተግባሩን፣ የሕይወት ገጠመኞችንም ሳይቀር በጽሞና በማዳመጥ ብርታትን የመለዋወጥ ባሕል ሊኖር ይገባል። ይህም በማካከላቸው ያለውን ቤተሰባዊ አንድነት እና ፍቅር በማሳደግ ሰላማዊ ሕይወት ለመኖር ያግዛል።

ከቤተሰብ ውጭ ለሚገኙ ሌሎች ሰዎችም ፍቅራችንን በመግለጽ፣ አቅመ ደካማ እና ጧሪ የሌላቸው  አረጋዊያንን፣ ያለ ደጋፊ የብቸኝነት ሕይወት ለሚኖሩ ሰዎች የምንችለውን ዕርዳታ ማድረግ ፣ በዚህ በዓብይ ጾም ወቅት ልናበረክትላቸው ከምንችላቸው መልካም ተግባራት መካከል ጥቂቶች ቢሆኑም በዚህ የዓብይ ጾም ወቅት ለሌሎች በምናደርገው መልካም ተግባር አማካይነት የክርስትና ሕይወታችንን በተግባር መግለጽ እንችላለን።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
07 March 2020, 16:20