ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የቅዱስ ቤተሰብ ምስልን ሲጎበኙ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የቅዱስ ቤተሰብ ምስልን ሲጎበኙ፣ 

“ቤተሰባችን” ፣ የመልካም ቤተሰብ መገለጫዎች።

ክቡራት እና ክቡራን የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎች፣ በያላችሁበት ሰላም እና ፍቅር ይብዛላችሁ በማለት ከቫቲካን ሬዲዮ የከበረ ሰላምታችንን እናቀርብላችኋለን። ይህ ቤተሰብን ከሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ ጠቃሚ ትምህርቶችን እና አስተያየቶችን የምናካፍልበት ሳምንታዊ ዝግጅት ነው። በዛሬው ዝግጅታችን ከመልካም ቤተሰብ መገለጫዎች መካከል ጥቂቶችን እንመለከታቸዋለን።

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን ነኝ።

ቤተሰብ፣ ከአምስቱ ታላላቅ ማሕበራዊ ተቋማት መካከል አንዱ እንደሆነ፣ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል በሚደረግ የጋብቻ ትስስር ተጀምሮ እያደገ የሚመጣ ማሕበራዊ ተቋም መሆኑን ከዚህ በፊት በቀረበው ዝግጅት ተመልክተናል። በሁለት የተለያዩ ጾታዎች መካከል የሚመሰረት ቤተሰብ ፍሬያማ ሊሆን የሚችለው በእውነተኛ ፍቅር የተመሰረተ እንደሆነ ነው። እርስ በእርስ በመዋደድ፣ መልካም በሆኑ ስነ ምግባር በመመራት አንድነቱን እና ዘላቂነቱን ያረጋገጠ ቤተሰብ ከሆነ ለማሕበራዊ ሰላም እና እድገት የሚያበረክተው እገዛ ከፍተኛ ነው።

በማሕበረሰብ መካከል በስነ ምግባር እና በዕውቀት የታነጸ፣ በሃብትም ቢሆን ራሱን የሚችል ቤተሰብ ጥሩ ኑሮን መኖር ይችላል ቢባልም በዚህ ቤተሰብ መካከል ፍቅር፣ ሰላም እና አንድነት ከሌለ መልካም ቤተሰብ ሊባል አይችልም። በቤተሰብ መካከል መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ከተፈለገ የቤተሰብ አባላትን የሚሰበስብ የጋራ ሥራዎች ሊኖሩ ይገባል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶችን ለመጥቀስ ያህል፣ በየቀኑ ሊከናወኑ የሚገቡ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ተከፋፍሎ መሥራት፣ በማዕድ ሰዓት በተቻለ መጠን በሕብረት ተገኝቶ መመገብ፣ ሲመሽ በጊዜ ወደ ቤት መመለስ እና አብሮ መሆን፣ ይህም በአንድ ወይም በሁለት ሰው ጫንቃ ብቻ ሊወድቅ የሚችለውን ድካም በመቀነስ፣ በቤተሰብ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን ጭንቀት በማስወገድ፣ መላው ቤተስብ ዘላቂ እና የተመቻቸ ሕይወት እንዲኖር ያግዛል።     

ሁለተኛው የመልካም ቤተሰብ መገለጫ፣ የቤተሰብ አባላት ዓመታዊ በዓላትን በጋራ የሚያከብሩ ቢሆን የሚል ነው። ብዙን ጊዜ የበርካታ ቤተሰብ በሥራ ወይም በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ከሚኖሩበ አካባቢ፣ ልጆች ከወላጅ ቤተሰብ፣ ወላጅ ቤተሰብ ከልጆቻቸው ርቀው የሚኖሩበት አጋጣሚዎች አሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የቤተሰብ ዓባላት በተቻለ መጠን አንድ ላይ የሚሰባሰቡበትን አጋጣሚ ማመቻቸት መልካም ነው። ይህን ለማድረግ ታዲያ የግድ ታላላቅ ዓመታዊ በዓላትን መጠበቅ አስፈላጊ አይደለም። ለምሳሌ የቤተሰብ አባል የልደት በዓልን ከቤተሰብ እና ከጓደኛ ጋር በመሆን አብሮ ማክበር ይቻላል።

ሦስተኛው የመልካም ቤተሰብ መገለጫ በተለይም ልጆች የወላጆችን ፍላጎት እና ምኞት ማሟላት የሚል ነው። የአንድ ቤተሰብ ሕይወት መልካም እንዲሆን ለማድረግ የሚያግዙ የተለያዩ መንገዶች ቢኖሩም፣ ልጆች ለወላጆቻቸው የሚያሳዩት ታዛዥነት እና ትህትና ወላጅ ቤተሰብን እጅግ ያስደስታል። የታዛዥነት እና የትህትና ሕይወት ከሌሎች መልካም ስነ ምግባሮች ጋር በቅድሚያ ለሕግ ወይም ለሥርዓት መታዘዝ፣ ለወላጅ ቤተሰብ መታዘዝ እና ለአረጋዊያን መታዘዝን ይጠይቃል። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መዋልን፣ የሚሄዱበት ቦታ ካለም ልጆቻቸውን አስከትለው መሄድን ይመርጣሉ። ልጆች ለወላጆቻቸው መመኪያ እና መከታ እንዲሁም ኩራት ናቸው። በወላጆች ልብ ውስጥ የሚገኝ የአባትነት ወይም የእናትነት ስሜት ተፈጥሮአዊ ነው።  

በቀን ውስጥ ልጅ ከወላጅ፣ ወላጅ ከልጅ ጋር ተገናኝቶ የሚነጋገርበት፣ የሚወያዩበት፣ የሚቃለዱበት እና አብረው የሚበሉብት ጊዜ ሊኖር ይገባል። በተለይ ቤተሰብ በመሰባሰብ ማዕድን በጋራ ሲካፈሉ በመካከላቸው ያለው የቤተሰብነት ስሜት ሊያድግ ይችላል። ቤተሰብ ለማዕድ በሚሰበሰብበት ጊዜ ማዕድን በጋራ ከመቁረስ በተጨማሪ እርስ በእርስ የመነጋገር፣ የመወያየት እና ሃሳብ የመለዋወጥ እድልን ያገኛሉ። አንዱ የሌላውን ውሎ መስማት፣ ያከናወናቸውን ሥራዎች ማዳመጥ እና በዕለቱ ማከናወን ስላለበት ተግባር ማዳመጥ እና አስተያየት ወይም ምክር ማካፈል በቤተሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያሳድግ ይችላል።    

የአንድ ቤተሰብ መልካምነት ከሚገለጽባቸው መንገዶች ጥቂቶችን የገለጽን ሲሆን፣ ከወላጅ ቤተሰብ አንስቶ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል መልካም ጥረት እና ተግባር በተግባር ሊታይ ይገባል። ወላጅ ቤተሰብ በልጆቻቸው መልካም አስተዳደግ ትልቅ ሃላፊነት እንደተጣለባቸው ይታወቃል። ከወላጅ ቤተሰብ ቀጥሎ ልጆችም ለመልካም አስተዳደግ ራሳቸውን ያዘጋጁ፣ ወላጆቻቸውን የሚያዳምጡ ሊሆን ይገባል። ልጆች ይህን አድርገው ከተገኙ፣ በቤተሰብ ውስጥ ዕለተ ዕለት የሚኖረውን ግንኙነት በማሳደግ፣ ለአስተዳደጋቸውም ትክክለኛ አቅጣጫን ማግኘት ይችላሉ። ከላይ የጠቀስናቸውን መልካም ስነ ምግባርን በማካፈል ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም በቤተሰብ መካከል በራስ የመተማመን ስሜት፣ የፍቅር እና የአንድነትን ሕይወት ማሳደግ ይችላሉ።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
15 February 2020, 09:38