ፈልግ

በፓኪስታን ከሚገኝ የክርስቲያን ማኅበረሰብ መካከል አንዱ፣      በፓኪስታን ከሚገኝ የክርስቲያን ማኅበረሰብ መካከል አንዱ፣  

በፓክስታን ሙስሊሞች ለቤተክርስቲያን ግንባታ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።

በፓክስታን፣ ጉጅራንዋላ በምትባል ከተማ ውስጥ የሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ለክርስቲያን ቤተሰቦች የቤተክርስቲያን ማሰሪያ ድጋፍ ማድረጋቸው ተነገረ። የገንዘብ ድጋፍ የተደረገው በከተማዋ የሚኖሩ በቁጥር ወደ ሃምሳ የሚጠጉ የክርስትና እምነት ተከታይ ቤተሰቦች የጀመሩትን የቤተክርስቲያን ግንባታ ማስፈጸሚያ የገንዘብ አቅም ስላነሳቸው ነው ተብሏል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፓክስታን፣ ጉጅራንዋላ ከተማ፣ ቡትራንዋሊ በተባለ አካባቢ የሚገኝ የቅዱስ ዮሴፍ ካቶሊካዊ ቁምስና መሪ ካህን የሆኑት አባ ሳምራን አኗር እንደገለጹት “ከእስልምና እምነት ተከታይ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው የተደረገላቸውን ድጋፍ ምን ጊዜም ቢሆን የምንረሳው አይደለም” ብለው እርዳታው የዋለውም በአካባቢው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ቤት ለማነጽ መዋሉንም አስረድተዋል። የጉጅራዋላ ከተማ በፓክስታን፣ የፑንጃብ ክፍለ ሀገር ዋና ከተማ ከሆነው የላሆሬ ከተማ በስተ ሰሜን፣ ሰማንያ ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ መሆኑ ታውቋል። አባ ሳምራን አኗር፣ የእመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ቤት ለማነጽ ሲባል ከእስልምና ተከታዮች በኩል የተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ፣ በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሰረተ የወንድማማችነት ምሳሌ የተገለጠበት ነው ብለዋል። በጸሎት ቤት ማሰሪያ ቦታ ላይ የመጀመሪያ ድንጋይ የተቀመጠው ያለፈው ህዳር ወር ውስጥ መሆኑንም አባ አኗር ገልጸዋል።

የሰላም ምልክት ነው፣

ቤተክርስቲያንን ለማነጽ ሲባል ከአካባቢው የእስልምና እምነት ተከታዮች በኩል የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ፣ የሁለቱም እምነት ተከታዮች እስካሁን ያቆዩትን አንድነት እና ወዳጅነት ለመጠበቅ የተደረገ ድጋፍ ነው ተብሏል። የተዋጣውን የገንዘብ መጠን መቁጠሩ ወይም ማወቁ ጠቃሚ አይደለም ያሉት የቅዱስ ዮሴፍ ካቶሊካዊ ቁምስና መሪ ካህን የሆኑት አባ አኗር፣ በአካባቢው በቁጥር በልጠው የሚገኙት የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ ይህን የመሰለ ተግባር ለመፈጸም የወሰዱት ምርጫ ከመልካም እሴትነት ባሻገር ፣ በማህበረሰባቸው ውስጥም እንደ እውነተኛ ተምሳሌነት ሲታሰብ ይኖራል ብለዋል። አባ አኗር፣ የጸሎት ቤቱን ግንባታ ለማስፈጸም ተጨማሪ እገዛ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ግንባታው የሚጠናቀቅበትን ጊዜ በትክክል ማወቅ አዳጋች ነው ብለዋል።

የጋራ ውይይት እና ወጣቶች ተስፋዎቻችን ናቸው፣

የእስልምና እምነት ተከታይ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ያደረጉልን ድጋፍ በአገሩ ለክርስቲያን ማኅበረሰብ ተስፋን የሚሰጥ መልካም ምሳሌ ነው በማለት በሮም ከተማ በሚገኝ የኡርባኒያና ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የበርካታ መጽሐፍት ደራሲ የሆኑት አቶ ሞቢን ሻሂድ ካቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። በፓክስታን፣ ላሆሬ ሀገረ ስብከት ውስጥ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ጉልህ ነው ያሉት መምህር ሻሂድ፣ በዚህ ሀገረ ስብከት ውስጥ፣ በአሲዚው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ስም የሚጠራ አራተኛው ቤተክርስቲያን በቅርቡ የታነጸ መሆኑን አስታውቀዋል። ከሰባት ዓመት በፊት በአካባቢው ሙስሊም እና ክርስቲያን ወጣቶች መካከል በተነሳው ግጭት በርካታ ወጣቶች ላይ ጉዳቶች መድረሱን ያስታወሱት መምህር ሻሂድ፣ ሆኖም በአካባቢው መሪ ካህን በኩል በተደረገው ጥረት በወጣቶች፣ በፖለቲካ መሪዎች እና በሐይማኖት አባቶች መካከል በተደረጉት የጋራ ውይይቶች በኩል ግጭቶች መቀዝቀዛቸውን አስረድተ፣ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረጉ የጋራ ውይይቶች አነሰ በዛም ትልቅ አስተውጽዖ እንዳላቸው ገልጸው አክለውም በአገሩ ወጣቶች ዘንድ እጅግ የሚወደደው የክሪኬት ኳስ ጨዋታ በክርስቲያ እና ሙስሊም ወጣቶች መካከል ወዳጅነትን ያሳደገ መሆኑን መምህር ሻሂድ አስረድተዋል። 

በፓክስታን ውስጥ ጥንታዊት ቤተክርስቲያን፣

በሥሩ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ቤትን የሚይዝ የቅዱስ ዮሴፍ ካቶሊካዊ ቁምስና፣ በምሥራቅ ላሆሬ ሀገረ ስብከት ውስጥ የሁለቱን እምነቶች ተከታዮች በማቀራረብ ታሪካዊ ጠቀሜታ ያለው እንደሆነ ሲታወቅ፣ ቁምስናው በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ከሚገኙ 27 ቁምስናዎች መካከል በጥንታዊነት የሚታወቅ መሆኑ ታውቋል። የተቋቋመው እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1953 ዓ. ም. መሆኑ ሲታወቅ በውቅቱ የወንጌል ምስክርነታቸውን ለመስጠት ከቤልጄም በሄዱት ፍራንችስካዊያን ካፑቺን ወንድሞች መሆኑ ታውቋል። አሁን በመገንባት ላይ ከሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ቤት ጋር በመሆን በአካባቢው ጉልህ የሆነ የክርስትና እምነት ማንነት መገለጫ እንደ ሆነ ታውቋል። ከዚህም ጋር ከእስልማና እምነት ተከታዮች በኩል የተደረገ ድጋፍም የወንድማማችነት ፍቅር በተግባር የታየበት መሆኑ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 February 2020, 16:10