ፈልግ

 ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ  

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2012 ዓ.ም. ዐብይ ጾም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልእክት

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

የ2012 ዓ.ም. ዐብይ ጾም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልእክት

 

 

ከሁሉ አስቀድሜ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ለምትኖሩ ካቶሊካውያን ምእመናን እና በጎ ፈቃድ ላላችሁ ሁሉ እንኳን ለ2012 ዓ.ም. ዐብይ ጾም በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ የተቀደሰ የተባረከ የጾም ጊዜ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡

ዐብይ ጾም እግዚአብሔር ዘወትር ወደ እርሱ እንድንመለስ ለሚያቀርብልን ጥሪ በተዐቅቦ፣ በጸሎት እና በልግስና ምላሽ የምንሰጥበት እጅግ የተቀደሰ ወቅት ነው፡፡ ሁላችንም ኃጥያትን ሠርተናል፡፡ ኃጥያት በቤተሰባችን እና በማህበረሰባችን ውሰጥ ያስከተለውን መበታተንም እንገነዘባለን፡፡  በኃጥያታችን ምክንያት ወደ ዓለም የገባውን ጥል፣ መለያየት እና ደም መፋሰስ አስቀርተን በይቅርታ፣ በዕርቅ፣ በፍቅር በመኖር የክርስትና ጉዟችንን የምንመሰክርበት እና ሀገራችን የምትገኝበትን ነባራዊ ሁኔታዎች ለመለወጥ የምንተጋበት ዕድል ይህ የዐብይ ጾም ነው፡፡

የጾም ወቅት የልብ መለወጥ ወቅት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሕይወታችን ፍጹም እንዲለወጥ ይፈልጋል፡፡ በዐብይ ጾም በሥርዓተ ሊጡርጊያችን የምናነባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ሁላችንም ለቅድስና የተጠራን መሆኑን ያረጋግጡልናል፡፡ ለዚሕ በጎ የሕይወት ፍጻሜ እንድንተጋም ያሳስቡናል፡፡ ወደ ቅድሰና በምናደርገው የጋራ ጉዞ ከእግዚአብሔር እና ከሰዎች ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት በእግዚአብሔር ጸጋ በመመርመር ከኃጥያት ተመልሰን ሰላም እና ዕርቅን በማስፈን ለወንጌሉ ቃል ታማኝነታችንን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡

ጾም ለክርሰቲያናዊ ቤተሰብ የተለየ ዕድልን ይዞ ይመጣል፡፡ ቤተሰብ ሰፊ ጊዜ አብሮ እንዲያሳልፍ፣ አብሮ እንዲጸልይ፣ እና ለልጆችም የመሥዋዕትነትን ትርጉም በተግባር እንድናስተምር ይረዳናል፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው መልካም ሥነምግባራትን በማስተማር፣ በቤት ውስጥ የተጣለባቸውን የኃላፊነት ድርሻ እንዲወጡ በማበረታታት፣ በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ በመጠመድ የሚያባክኑትን ጊዜ በአግባቡ እነዲጠቀሙበት በመቆጣጠር፣ ሌሎችን እንዲንከባከቡ እና ያላቸውን ተካፍለው እንዲጠቀሙ በማለማመድ ይህንን ቅዱሰ ጊዜ በጋራ በማሳለፍ ልዩ በረከትን ያገኙበታል፡፡

ጾም ለብቻ ተዘግቶ በመቆዘም የምናሳለፈው ጊዜ አይደለም፡፡ ይልቁንም አገልግሎታችን እና እንክብካቤያችን ወደ ሚያስፈልጋቸው ለመድረስ ወደ ሌሎች የምንሄድበት፣ ለራሳችን ብቻ ከማሰብ ወጥተን በእግዚአብሔር ምህረት የተነሣ ያገኘነውን የመንፈስ እርካታ በዙሪያችን ወደ ሚኖሩ ሰዎች የምናስተላልፍበት፣ የመቀራረብ፣ የመተሳሰብ፣ የመዋደድ እና እርስ በእርስ በይቅርታ የመጎበኛኘት ጊዜ ነው፡፡

ይህ ወቅት ደቀ መዛሙርት ለጌታ “እንዴት መጸለይ እንዳለብን አናውቅም፤ እባክህ አስተምረን?” በሚል ያቀረቡትን ጥያቄ ደግመን የምናቀርብበት ጊዜ ነው፡፡  በማይነገር መቃተት የሚማልድልን መንፈስ ቅዱስ ራሱ ድካማችንን ይሞላል (ሮሜ። 8፡26)፡፡ በዚህ በጾም ወቅት መሥዋዕተ ቅዳሴን፣ ምሥጢረ ንሰሃን እና ምሥጢረ ቁርባንን ማዘውተር ይገባናል፡፡ በየዕለቱም ከቅዱሰ ወንጌል እያነበብን በቤተሰብ መካከል የእግዚአብሔርን ቃል ማዳመጥ ጠቃሚ ነው፡፡ መዝሙረ ዳዊትን፣ የእመቤታችንን የመቁጠሪያ ጸሎት እና ውዳሴ ማርያምን መድገምም የበለጠ ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ ይረዳናል፡፡

በየቁምስናችን በምናደርሳቸው የፍኖተ መስቀል ጸሎቶች የገዛ ራሳችንን መስቀል ከክርስቶስ መስቀል ጋር እናስታርቃለን፡፡ የኑሮ ውጣ ውረዶቻችንንም ከእርሱ ህማማት ጋር እናቀርባለን፡፡ በዚህም ክርስቶስ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ እኛም ከራስ ወዳድነት ትብታብ ተላቀን ራሳችንን ለሌሎች በፍቅር ማቅረብን እንማራለን፡፡  መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን እንኳን ሳይቀር በትሁት ልቦና ሌሎችን ለማገልገል እንድናቀርብ ይጠይቀናል፡፡

በጾም ወቅት ቤተክርስቲያን በምታዘው መሠረት ከምግብ መታቅብ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች ይህ ችላ እየተባለ የመጣ ይመስላል፡፡ ከምግብ መታቀብ የጾማችን ማዕከል ነው፡፡ ይህም ለዐዳም ሁሉ ተፈቅዶለት ሳለ ከአንዲቷ ፍሬ እንዳይበላ የታዘዘበት ቅድመ ታሪክ ጀምሮ የነበረ ነው (ዘፍ. 2፡16-17)፡፡ ከምግብ መታቀባችን በተለምዶ የጾም እና የፍስክ ብለን በምንለያቸው ምግቦች ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ወይም ከአንዱ በመታቀብ ሌላውን መተካትም መሆን የለበትም፡፡ ትክክለኛው ጾም ራስን ማስራብ፣ ሥጋን ማድከም፣ ነፍስን ግን ማበርታት ነው፡፡ መጾም የእግዚአብሔርን ፍቅር እንድንራብ ያደርገናል፡፡ እርሱን ለማገልገል ያለንን ጥማት ያጠናክርልናል፡፡ መጾም በዙሪያችን ላሉ ስዎች እንድናስብ እና የበለጠ ለጋስ እንድንሆን ይረዳናል፡፡

በጾም ወቅት የምንፈጽመው ልግስና የተፈጠርነው ለራሳችን ብቻ እንድንኖር አለመሆኑን ያሳስበናል፡፡ ልግስና መስጠት ብቻ ሳይሆን የእኛ ያልሆነውን አለመውሰድንም የሚጨምር ተግባር ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የሚያስኘው ልግስናም በግንባራችን ወዝ ለፍተን ካፈራነው ላይ የምንሰጠው ሰጦታ ብቻ ነው፡፡ ያለን እጅግ ጥቂት ቢሆን እንኳን የምናቀርብበት ፍቅር የስጦታችንን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል። ያፈራናቸው በረከቶች ለሰው ልጆች እንዲሁም ለተፈጥሮ  ልማት እና ብልጽግና እንድናውላቸው እና ለሌሎች እንድናካፍላቸው ጭምር በአደራ የተሰጡን ሀብታት ናቸው እንጂ እንደፈለግን የምናዝባቸው አይደሉም፡፡ ልግስና በእግዚአብሔር ተስፋ እንደምናደርግ እና የበረከት ሁሉ ምንጭ እግዚአብሔር እንደሆነ የምናምን መሆኑን የምንገልጽበት መንገድ ነው፡፡

ጾም የጌታ ኢየሱስን ህማማት በመካፈል በሞቱ አማካኝነት በተከፈተልን የጽድቅ በር ወደ ትነሣኤ ክብር የምንዘልቀበት ቀና ጎዳና ነው።በመሆኑም የፍቅር እና የድኅነት ዜና የሆነውን ቅዱስ ወንጌልን ከሌሎች ጋር እንካፈል፡፡  በተለይ የእግዚአብሔር ፍቅር እና እንክብካቤ የሚያሻቸውን ድሆችን፣ በህመም ምክንያት የሚሰቃዩትን እና አረጋውያንን እንጎብኝ፡፡ ስደተኞችን እና መጻተኞችን እናጽናናቸው፡፡ ሰለሀገራችን ስላም እና አንድነትም እንማልድ፤ ቤተ ክርሰቲያንን እኛንም አገልጋዮቻቸሁን በጸሎት አግዙን፣ አበርቱን፡፡

እግዚአብሔር የተባረከ ዐብይ ጾም ያድርግልን! አሜን!

ካርዲናል ብርነየሱስ

ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት እና የምሥራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ዪኒቨርሲቲ ቻንስለር

የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሊቀመንበር

22 February 2020, 12:48