ፈልግ

የጥር 24/2012 ዓ.ም ዘጥምቀት አስተርእዮ 2ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የጥር 24/2012 ዓ.ም ዘጥምቀት አስተርእዮ 2ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የጥር 24/2012 ዓ.ም ዘጥምቀት አስተርእዮ 2ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ኢየሱስ በዐሥራ ሁለት ዓመቱ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ

የእለቱ ምንባባት

1.    2ቆሮ.1፡13-24

2.   1ዬሐ.2፡22-29

3.   ሐ.ሥራ. 13፡20-27

4.  ሉቃ 2፡45-52

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ በዐሥራ ሁለት ዓመቱ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ

ወላጆቹም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። ልጁም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ፣ እንደተለመደው ወደ በዓሉ ወጡ። በዓሉን ከፈጸሙ በኋላ፣ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀረ፤ ወላጆቹ ግን መቅረቱን አላወቁም ነበር። አብሮአቸው ያለ መስሎአቸው፣ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ፤ በኋላ ግን ከዘመዶቻቸውና ከወዳጆቻቸው ዘንድ ይፈልጉት ጀመር፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

ከሦስት ቀንም በኋላ፣ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፤ የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር። ወላጆቹም ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤ እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለምን እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔኮ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።

እርሱም፣ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። እነርሱ ግን የተናገራቸው ነገር አልገባቸውም።ከዚያም አብሮአቸው ወደ ናዝሬት ወረደ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር። ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ።

የእለት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ!

ዛሬ እንደ ቤተ-ክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት ዘጥምቀት ወይም አስተርእዬ ሁለተኛ የተሰኘውን ሰንበት እናከብራለን፡፡

በዚህም ዕለት በተነበቡት ንባባት አማካኝነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምረን የሚያስታውሰን ነገር አለ፡፡  ይኸውም በመጀመሪያው ምንባብ ላይ እንደተጠቀሰው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲላስና ጢሞቴዎስ በቆሮንጦስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል እየሰበኩ በኖሩበት ጊዜ በቅድስናና በቅንነት እንደኖሩ ይናገራል፡፡

ይህንን የቅድስናና የቅንነት ኑሮ ለመኖር የቻሉትም ከእግዚአብሔር ባገኙት ጸጋ ነው፡፡  ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ራሱ ሲመሰክር እንዲህ ይለል፦ “ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለው ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም እንደውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሰርቻለሁ ዳሩ ግን ይህ ሁሉ የሆነው ከእኔ ጋር ባለው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው” (1ቆሮ 15፡10) ይላል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ በቆሮንጦስ ወንጌልን እየሰበከ ሲመላለስ “በቅድስናና በቅንነት እንደኖርኩ ከሁሉ በላይ ሕሊናዬ ይመሰክርልኛል” በማለት ያናገራል።  እኛም ሁላችን በቅድስናና በቅነነት የምንመላለስ ከሆነ የመጀመሪያ ምሥክር ሰጪ ሕሊናችን ነው።  ሕሊና እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ክፉና ደጉን እንዲለይ በውስጡ ያስቀመጠለት እውነተኛ ዳኛ ነው፡፡

ሕሊናችን በቅንነት እንድትመራ ደግሞ የግድ የእግዚአብሔር ጸጋ እንዲያግዛት ያስፈልጋል፡፡  ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስም እንደሚመሰክረው እርሱም በቅን ሕሊናና በቅድስና መመላለስ የቻለው በዚሁ እግዚአብሔር በሚሰጠው ጸጋ ብቻ ነው፡፡ ሰው ሁል ጊዜ በኃጢአት ውስጥ የሚመላለስ ከሆነ ከእግዚአብሔር ጸጋ እርቆ እንደሚኖር ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡  ይህ የእግዚአብሔር ጸጋ በሕሊናው ውስጥ የማይመላለስ ከሆነ በምንም ዓይነት የቅንነትና የቅድስናን ጉዞ መጓዝ አይችልም፡፡

እግዚአብሔር ጸሎታችንን ልመናችንን የሚሰማው በቅንነትና በቅድስና ለመኖር ብርቱ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው፡፡  ዘወትር በኃጢያት ጐዳና የምንመላለስ ከሆንን እግዘአብሔር እንዴት ጸሎታችንን ሊሰማን ይችላል? ዳዊት በመዝሙሩ “ኃጢአትን በልቤ አስተናግጄ ቢሆን ኖሮ ጌታ ባልሰማኝ ነበር ይላል” (መዝ.66፡18) ።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር ሁላችንም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፀንተን እንድንቆም በመንፈሱ የቀባንና ያተመን እግዚአብሔር ራሱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር እያንዳዳችን ዘወትር በእርሱ መንፈስና እርሱ በሚሰጠን ጸጋ መልካም ነገር ሁሉ እየሰራን እንድንኖር ይፈልጋል፣ ለዚህም ነው ዘወትር በአጠገባችን ሆኖ የሚያስፈልገንን ጸጋና በረከት የሚያፈስልን፡፡  ከዚህ ከሚፈሰው ጸጋና በረከት መቋደስ ደግሞ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው፡፡ እግዚአብሔር በሚሰጠን ጸጋ የምንመላለስ ከሆነ በእርግጠኝነት የዘለዓለም ሕይወት ወራሽ መሆናችንን እናስመሰክራለን፡፡  ሁለተኛው ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ዩሐንስ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው የጸጋ ቅባት ሁልጊዜ እውነትን ብቻ እንድንመሰክር ያስተምረናል ይለናል፡፡

እግዚአብሔር በሚሰጠን ጸጋ የማንመላለስ ከሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማወቅ አንችልም፣ ወደ እግዚአብሔር የሚመራንን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ካላወቅን ደግሞ እግዚአብሔርን ለማወቅ አንችልም። “መንገዱ እኔ ነኘ እውነትና ሕይወትም እኔ ነኝ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” (ዬሐ 14፡6) ይላል፡፡

አንድ ሰው በእግዚአብሔር ጸጋ ውስጥ የሚመላለስ ከሆነ ማንም ሰው አያሳስተውም፣ ምክንያቱም በውስጡ ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ በሕሊናው አማካኝነት እውነትንና የቅድስናን መንገድ ስለሚገልፅለት ነው፡፡  እግዚአብሔር በሰጠን ንጹህ ሕሊና የምንኖር ከሆነ በአብ እንዲሁም በወልድ ውስጥ እንኖራለን ማለት ነው። በአብና በወልድ ውስጥ የምንኖር ከሆነ ደግሞ በዩሐንስ ወንጌል 4፡14 እንደተጠቀሰው ምንጩ ከማይደርቀው የሕይወት ውኃ እንጠጣለንና በእርግጠኝነት መንገዳችን የተቃና የዘለዓለም ሕይወትም ወራሾች እንሆናለን፡፡

በአብና በወልድ ውስጥ የማንኖር ከሆነ ደግሞ ዘወትር ሐሰትን በመናገርና ለቅድስና ጉዞ የማይመቹ ነገሮችን እናደርጋለን፡፡ ይህ ደግሞ በዩሐ. ወንጌል 15፡6 ጀምሮ እንደተጠቀሰው እንደማይጠቅም ቅርንጫፍ ተቆርጠን እንጣላለን መጨረሻችንም በእሳት ውስጥ ተጥሎ መቃጠል ይሆናል፡፡

ለዚህ ነው ቅዱስ ሐዋርያው ዩሐንስ የእግዚአብሔርን ቃል በውስጣችን ይዘን፣ የመንፈስ ቀዱስ ቅባት የሚሰጠንን ብርታት ይዘን ፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኑር እያለ ምክሩን የሚለግሰን፡፡

በዛሬው በሉቃስ ወንጌል ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 12 ዓመት በሞላው ጊዜ የፋሲካን በዓል ለማክበር ከወለጆቹ ጋር ወደ እየሩሳሌም እንደሄደ ይናገራል፡፡  ይህ የወንጌል ክፍል ሕጻኑ ኢየሱስ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ከወላጆቹ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ለፋሲካ በዓል እንደሔደ እና ከበዓሉም በኋላ እሱ በቤተ መቅደስ እንደቀረ፣ ወላጆቹም ከሦሰት ቀናት ፍለጋ በኋላ እንዳገኙት የሚተርክ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ማርያም ይህ የእግአብሔር አደራ አለባቸውና እንደገና ወደኋላ ተመልሰው መፈለግና ማገኘት ግድ ሆኖባቸው ነበር፡፡ እኛም የአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር አደራ አለብን፤ ልጁን ልኮልናል፣ብዙ በረከትን በእቅፋችን ውስጥ አስቀምጧል፣ ጸጋን ሰጥቶናል፤ ይህን ክቡር የሆነውን የአምላክ ስጦታ እንዴት ነው የያዝነው? ኢየሱስ ከሕይወታችን የራቀ ሲመስለንስ እንዴት ነው ወደ ፍለጋ የምንወጣው? የት ነው ኢየሱስን የምንፈልገው?

ለኢየሱስ ያለን ፍቅር እሱን ለመፈለግ በምናደርገው ጥረት እና በምንደክመው ድካም ይለካል፡፡ ከሁሉ በማስቀደም ኢየሱስን ለመፈለግ ስንነሳ ራሳችንን ማዘጋጀት ይገባናል ምክንያቱም ይህ ጉዞ ተጀምሮ ግማሽ መንገድ ላይ የሚተው አይደለም፡፡ ከኢየሱስ ወላጆች ይህን ጽናት ነው እንደ አብነት መውሰድ የሚገባን፡፡ እነሱ እንደሚያገኙት አምነው ነው የወጡት፡፡ በመጨረሻም የፈለጉትን አገኙ፡፡ እግዚአብሔር በቅን ልብ ለሚፈልጉት ጊዜውን ጠብቆ ይገለጣል፣ በልባቸውም በመገኘት ደስ ያሰኛቸዋል፤ ይህን አምላክ በተረጋጋ ልብ እና መንፈስ መፈለግ፣ ፍለጋውም በእምነት እና በተስፋ የታገዘ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በትንሹም በትልቁም ማጉረምረም እና ማማረር ሳይሆን እንደነዚህ ሁለት ቅዱሳኖች በትዕግስት በመጽናት መጓዝ ነው የሚገባን፣ክርስቶስን የራስ እስከ ማድረግ ድረስ መትጋት፣ ለጸሎት እና ከእግዚአብሔር ጋር ለሚያገናኙን መንፈሳዊ ሰዓታትና መንፈሳዊ ተግባራት ታማኝ መሆን፡፡

ቀላልና የተመቻቸ ሕይወት የለመደች ነፍስ ግን በመንፈስ እንቅልፋም ትሆናለች፤ ድካምን፣ ተጋድሎን፣ መስዋዕትነትን የምትጠላ፣ መስቀልንም የምትጸየፍ ከሆነ ወይም ከላይ እንደተጠቀሰው ማጉረምረም ብቻ የሚቀናት ነፍስ ኢየሱስን ማግኘት አትችልም፣ የክርስትናው መንገድ ይከብዳታል፡፡

አምላካችን ግን ራሱንም ሆነ በእኛ ላይ ያለውን ዕቅድ፣ ፍቃዱንም የሚገልጽልን ተግዳሮቶችን በትዕግስት መቀበልና ማስተናገድ ስንችል ነው፤ እሳት ሸክላን እንደሚያጠነክር ፈተናም ነፍስን፣ እምነትን፣ ክርስትናን ያጠነክራል፤ በዚህ በእምነት ጉዞ፣ በየዕለቱ ክርስቶስን የበለጠ ለማግኘትና የራሳችን ለማደረግ በምንደክመው ድካም ፈተና እንዳይገጥመን የምንሻና የምንመኝ ከሆነ መንገድም ምርጫም ተሳስተናል፤ ይህን ስላወቁ ነው ዮሴፍና ማርያም እነዚያን ፈታኝ ቀናት በትዕግስትና በእምነት የኖሯቸው፤በዚህ በፈተና መንገድ በመራመዳቸው የበለጠ በእምነት ጠንካሮች ሆኑ፡፡

ስለዚህ ማንም ሳይፈተን አይቀርም፤ እንኳን እኛ ክርስቶስ ራሱ መስቀልና ፈተና በበዛበት መንገድ ነው የተጓዘው፤ «ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ፤ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ» እስከማለት ደረሶ ነበር፤ ጌታችን ግን እዚያ ላይ አላቆመም፣ጉዞውን አላቋረጠም  «ያንተ ፍቃድ ይሁን» ብሎ እስከ መጨረሻው የመስቀል መስዋዕትነት ራሱን አቅርቧል፡፡ ምክንያቱም የመጣው በአባቱ ቤት ለመገኘትና የአባቱን ፍቃድ ለመፈጸም ነው፡፡

ስለዚህ ኢየሱስን ስንፈልግ እንደ ዮሴፍና ማርያም እምነትንና ትዕግስትን ስንቅ አድርገን ነው፡፡ ተራ እና ቀላል መንገድንማ እምነት የሌላቸውም ሰዎች ሊጓዙት ይችላሉ፤ እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት መኖር ለማን ያዳግተዋለ? ይህ ተራና ቀላል መንገድ ግን ክስትናውን አያጣፍጠውም፡፡ እነዚህ የኢየሱስ ወላጆች ባለፉበት መንገድ ማለፍና ወደ ቅድስና ለመድረስ ግን አድካሚውንና ተራራማውን መንገድ በትዕግስት፣በእምነትና በተስፋ መጓዝ የግድ ነው - ክርስቶስን ለማግኘትና ከእርሱ ጋር ለመወገን፤

ከኢየሱስ መልስም የምንማረው ትልቅ ትምሕርት አለ፡፡ እርሱ ከወላጆቹ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ «ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አታወቁምን?» ነበር ያላቸው ከአባቱ የተቀበለውን ተልዕኮ ሲያመለክት፤ በወንጌልም «አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ፈልጉ» (ማቴ 6፡33) ነውና የተባለው ፡፡ በእንዲህ ያለ መንፈስ፣ በየዋህ ልብና በክርስቲያናዊ ፍቅር የሚመላለስ አማኝ እንደ ብላቴናው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት በጥበብና በጸጋ እንዲሁም በሞገስ ያድጋል፣ ጣፋጭ የሆነ የክርስትና ሕይወትን መኖር ይችላል፣ከእግዚአብሔርም ጋር በቅርብ ይተዋወቃል፤ ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእከቱ «ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል የሚለን» (ያዕ 4፡8)። እኛም ይህንን የእግዚኣብሔር ቃል ሰምተን ወደ እርሱ በመቅረብ እርሱን የሕይወታችን ማዕከል አድርገን መኖር እንችል ዘንድ በአማልጅነቷ እንድትረዳን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት ልንማጸን ይገባል። የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን። አሜን!  

01 February 2020, 13:34