ፈልግ

በማላዊ ሕጻናት ትምህርታቸውን በመከታተል  ላይ፣ በማላዊ ሕጻናት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ፣  

“ቤተሰባችን”፣ ትምህርት የሰውን ልጅ የወደፊት ተስፋ ይወስናል!

ክቡራት እና ክቡራን የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎች በያላችሁበት ሰላም እና ፍቅር ይብዛላችሁ በማለት ከቫቲካን ሬዲዮ የከበረ ሰላምታችንን እናቀርብላችኋለን። ይህ ቤተሰብን ከሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ ጠቃሚ ትምህርቶችን እና አስተያየቶችን የምናካፍልበት “ቤተሰባችን” የተሰኘ ሳምንታዊ ዝግጅት ነው። በዛሬው ዝግጅታችን “ትምህርት የሰውን ልጅ የወደፊት ተስፋ ይወስናል” በሚል አርዕስት የቀረበ መልዕክት እናካፍላችኋለን።

ወላጆች በተጣለባቸው ከፍተኛ ሃላፊነት፣ ልጆቻቸውን መልካም ሥነ ምግባርን፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶችን በማስተማር ወይም በማስተላለፍ ረገድ ከፍተኛ ሚናን የሚጫወቱ መሆናቸውን ተመልክተናል። ከወላጅ ቤተሰብ በተጨማሪ የተለያዩ የትምህርት እና የስልጠና ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ መደበኛ ትምህርትን ለአዳጊ ልጆች፣ ለወጣቶች እና ለጎልማሶች ለማዳረስ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ድህነት በተስፋፋበት፣ የማሕበራዊ ኑሮ አለመመጣጠን በሚታይበት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮች በተበራከቱበት፣ ከማሕበራዊ ሕይወት መገለል እየጨመረ በመጣበት ባሁኑ ጊዜ ተጨማሪ የትምህርት ዘርፎችን በማስተዋወቅ የትምህርት ስርዓትን በማሳደግ ለእያንዳንዱ የሕብረተሰብ ክፍል ተጨማሪ ዕውቀቶችን ማስጨበጥ አስፈላጊ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውቀዋል። በቫቲካን ውስጥ በትምህርት ሥርዓት እና ይዘት ላይ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ጥር 29/2012 ዓ. ም. ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የትምህርት ይዘትን ለማሳደግ ዕቅድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ ሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መኖራቸው አስታውቀው የሰው ልጅ የታደሰ የትምህርት ሥርዓት ሊኖረው እንደሚገባ አስረድተው፣ በሕዝቦች መካከል የሚታየውን የተበላሸ ግንኙነቶች መጠገን የሚችሉ እና የወንድማማችነትን መንፈስ የሚያሳድጉ የጎለመሱ ሰዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል።   

ድህነት ፣ መድልዎ ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፣ ምን አገባኝ ባይነት እና የሰው ልጅ ብዝበዛ በዓለምችን ውስጥ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕጻናት የወደ ፊት ተስፋቸውን አጨልሞባቸዋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እስከ አሁን ሲሰጡ ለቆዩት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቶች ፣ የትምህርት ተቋማትን አመስግነው በዚህም በሁለቱ ጾታዎች መካከል የነበረው ክፍተትም እየጠበበ መምጣቱን አስታውሰዋል።   

የአሁኑን ወጣት ትውልድ እና አዳጊ ልጆች በማስተማር እና በማነጽ ተግባር የወላጅ ቤተሰብ ጥረት ብቻውን በቂ አይደልም።  ትምህርት ቤት፣ ሐይማኖታዊ ተቋማት እና መላው ማሕበረሰብ እውቀትን፣ መልካም ስነ ምግባርን እና የባሕል እሴቶችን በቸርነት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ምን ያህል ዝግጁ መሆኑን መመልከት ያስፈልጋል። ምክንያቱም የዛሬው ማሕበረሰብ መልካም ባሕል፣ እውቀት እና ስነ ምግባር ለመጭው ትውልድ ድጋፍ ስለሚሆንለት ነው። በመሆኑም ከዛሬው ትውልድ በተስፋ የሚጠበቀው ካለፈው ትውልድ የተረከበውን ወይም ያገኙትን መልካም ማሕበራዊ፣ ባሕላዊ እና ሐይማኖታዊ እሴቶች ለነገው ትውልድ የሚጠቅም መሆኑን በመገንዘብ አስተዋጽዖን ማድረግ ያስፈልጋል።        

ትምህርት ሲባል በቀለም ትምህርት አማካይነት የተለያዩ ጽንሰ-ሐሳቦችን ለትውልድ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎች ፣ ከወላጅ ቤተሰብ፣ ከትምህርት ቤት እንዲሁም ከባሕላዊ እና ሐይማኖታዊ ተቋማት ጋር በመተባበር መልካም የሆኑ እሴቶችን ከሌላው ጋር መካፈልን ይጠይቃል። በተለይም የሰውን ሕሊና ለማነጽ የሚሰጡ ትምህርቶችን በማስመልከት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ የሕሊና ሕንጸት በሚለው አርዕስት፣ ከቁ. 1783 – 1785 ድረስ የሚከተለውን ያስነብባል፥

የሕሊና ትምህርት ለአፍራሽ ተጽዕኖዎች ተገዥ ለሆኑ እና በኃጢተገፋፍተው የገዛ ራሳቸውን ፍርድ በመምረጥ ተሰሚነት ሊቸራቸው የተገባ ትምህርቶችን ለማይቀበሉ ሰዎች እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። የሕሊና ትምህርት የዕድሜ ልክ ተግባር ነው። ከሕጻንነት ጊዜ ጀምሮ ልጅን ሕሊና ስለሚያውቀው ውስጣዊ ሕግ ትምህርት እና ገቢራዊነት ያስተምራል። ጥንቃቄ የተመላበት ትምህርት ምግባርን ያስተምራል። ፍርሃትን፣ ራስወዳድነትን እና ትዕቢትን፣ ከኃጢአት የሚመነጨውን ጥላቻ እና ከሰብዓዊ ድክመት እና ስሕተት የሚወለደው የግድ የለሽነት ስሜት ይከለክላል ወይም ከዚያ ይፈውሳል፤ የሕሊና ትምህርት ነጻነትን እና የልብ ሰላምን ያስገኛል።

በሕንጸተ ሕሊና የእግዚ አብሔር ቃል የመንገዶች ብርሃን ነው። በመሆኑም እርሱን ከእምነት እና ከጸሎት ጋር ማጣመር፣ ገቢራዊም ማድረግ አለብን። በጌታ መስቀል ፊት ቀርበን ሕሊናችንን ልንመረምር ይገባል። በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እንታገዛለን፤ በሌሎች ምስክርነት ምክር እንረዳለን፤ በቤተክርስቲያን ጽኑ ትምህርትም እንመራለን።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
15 February 2020, 09:24