ፈልግ

ርግብ የሰላም ምልክት፣ ርግብ የሰላም ምልክት፣ 

“ቤተሰባችን” ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ሰላም ታላቅነት ማስተማር መልካም ነው።

ክቡራት እና ክቡራን የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎች በያላችሁበት ሰላም እና ፍቅር ይብዛላችሁ በማለት ከቫቲካን ሬዲዮ የከበረ ሰላምታችንን እናቀርብላችኋለን። ይህ ቤተሰብን ከሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን የምናካፍልበት ሳምንታዊ ዝግጅት ነው። በዛሬው ዝግጅት ልጆች ከወላጆቻቸው ከሚማሯቸው በርካታ መልካም ሥነ ምግባራት መካከል አንዱ የሆነውን እና በማህበረሰብ ውስጥ መልካም ግንኙነት እንዲኖር መንገድን ስለሚከፍት የሰላም ግንባታ ተልዕኮ እንመለከታለን።

ወላጆች ሥነ ምግባርን፣ መልካም የሆኑ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶችን ለልጆቻቸው በማስተማር ወይም በማስተላለፍ ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ፤ ይህን የማድረግ ሃላፊነትም አለባቸው። ለመልካም አስተዳደግ የሚያግዝ ጥሩ ትምህርት ከወላጆቻቸው ያገኙ ወይም የቀሰሙ ልጆች ከሚያሳድጓቸው ወላጅ ቤተሰብ አልፈው ለሚኖሩበት ማሕበርሰብ፣ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ አገልግሎቶች ውስጥ ተሰማርተው ለሚያበረክቱት ተግባር መልካም ፍሬን የሚያዩበት አጋጣሚ ይሆንላቸዋል። ወላጆች በልጆቻቸው መልካም አስተዳደግ ላይ ያላቸውን ሃላፊነት በማስመልከት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ የሚከተለውን መልዕክት ይናገራል፥

“የባለትዳሮች የፍቅር ዓላማ ልጆችን በማፍራት ብቻ ሳይወሰን ሥነ ምግባራዊ ትምህርት እና መንፈሳዊ አስተዳደጋቸውንም በሚመለከት ጉዳይ ያላቸውን ሚና በጣም ወሳኝ በመሆኑ ይህን በተመለከተ እነርሱን መተካት እጅጉን ኣዳቻች ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር ያላቸው መብት እና ግዴታ ፍጹም እና የማይገረሰስ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆኑ አድርገው ማየት እና በሰብዓዊነታቸውም ሊያከብሯቸው ይገባል። ወላጆች በሰማይ ላለው አባት ፈቃድ ራሳቸውን ታዛዥ በማድረግ ልጆቻቸው የእግዚአብሔር ሕግ እንዲፈጽሙ ያስተምሯቸዋል።       

ወላጆች ልጆቻቸውን የማስተማር ተቀዳሚ ኃላፊነት አለባቸው ሲባል ኃላፊነታቸውንም የሚመሰክሩት ከሁሉ በፊት ገርነትን፣ ይቅርታን፣ አክብሮትን፣ አመኔታን እና ከራስ ወዳድነት የነጻ አገልግሎትን መመሪያ አድርጎ የሚኖር ቤተሰብ ሲመሰርቱ ነው። ቤት ምግባራትን ለማስተማር የተመቸ ሥፍራ ነው። ይህ ትምህርት የእውነተኛ ነጻነት ቅድመ ሁኔታዎች የሆኑትን ራስን የመካድ፣ ቅን የሆነ ፍርድን የመስጠት እና የመቆጣጠር ብቃትን ይጠይቃል። ወላጆች ልጆቻቸው ሰብዓዊ ሕብረተሰብን ከሚያውኩ አስጊ እና አዋራጅ ነገሮች የሚርቁበትን መንገድ ማስተማር አለባቸው” በማለት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ፣ የቤተሰብ አባላት ኃላፊነቶች በሚለው ርዕሥ፣ የወላጅ ግዴታዎች በሚለው ንዑስ ርዕሥ፣ ከቁ. 2221 – 2224 ድረስ የተገለጸው ምክር ይህን ያስገነዝባል።  

ሕብረተሰብን ከሚያውኩ፣ ለማሕበራዊ ጸጥታ አስጊ ከሚባሉ ማሕበራዊ ቀውሶች መካከል አንዱ የሰላም መደፍረስ ነው። ሰላም ለሰብዓዊ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ፍጥረት የሚሻው የሕይወት መሠረት እና ዋስትና ነው። የሰው ልጆች ሰላም ካልተከበረ፣ በነጻነት ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ እና የመሥራት ነጻነት ካልተከበረ፣ ልዚህም ብርቱ ጥረት ካልተደረገ በቀር ሰላምን በምድራችን ማንገሥ አዳጋች ይሆናል። ሰላም ሊገኝ የሚችለው እያንዳንዱ ሰው በአስተሳሰቡ፣ በንግግሩ እና በሥራው ትክክለኛነቱ የተረጋገጠለትን ተግባር ሲያከናውን ነው። ንግግራችን እና ሥራችን ሰላምን የተላበሰ፣ ፍቅርን እና አንድነትን መሠረት ያደረገ እንጂ ጥላቻን የሚቀሰቅስ፣ ልባችንም ምህረትን እና እርቅን የሚያደርግ እንጂ በቀልን የሚመኝ መሆን የለበትም። “በሰዎች መካከል እርቅ እና ሰላምን የሚያደርጉ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚባሉ ደስ ይበላቸው” (ማቴ. 5:9)። 

ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ሰላም አስፈላጊነት የማስተማር፣ በመልካም ሥነ ምግባር የማነጽ፣ የመምከር፣ የመገሰጽ፣ በአጠቃላይ መልካም ሥነ ምግባርን ይዘው እንዲያድጉ የማድረግ ግዴታ አለባቸው። ይህን የሚያደርጉት ከሁሉ አስቀድሞ ራስን የሰላም መሣሪያ በማድረግ፣ ቀዳሚ የሰላም ምሳሌ በመሆን ነው። ሰላምን ማስፈን ለቤተሰብ ፍቅር፣ ለማሕበረሰብ አንድነት እና ለአገር መረጋጋት ወሳኝ ተግባር ነው ካልን ትኩረትን በመስጠት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ የሚያስፈልግ መሆኑን እንገነዘባለን። ሰላምን አንድ የማሕበረሰብ ክፍል ብቻ ያመጣል ብሎ ማሰብ ከንቱ ነው። ሰላም በገንዘብ የሚገዛ፣ በሃብት የሚለወጥ አይደለም።

ክቡራት እና ክቡራን፣ “ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ሰላም ታላቅነት ማስተማር” በሚል አርዕስት የቀረበ አጭር ጽሑፍ በዚህ እንፈጽማለን። በሚቀጥለው ዝግጅት በሌላ ርዕሥ እስከምንገናኝ ሰላምን እና ፍቅርን የምመኝላችሁ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን ነው።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

01 February 2020, 16:24