ፈልግ

ወደ ሰሜን አሜሪካ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ የላቲን አሜሪካ ስደተኞች፣ ወደ ሰሜን አሜሪካ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ የላቲን አሜሪካ ስደተኞች፣ 

የሰሜን አሜሪካ ጳጳሳት መንግሥታቸው ያስቀመጠውን አዲስ የጉዞ ማዕቀብ ተቃወሙ።

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ የሰሜን አሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሰሜን አሜሪካ ለመጓዝ በሚፈልጉ የጥቂት አገሮች ስደተኛ ዜጎች ላይ የጣሉትን አዲስ የጉዞ ማዕቀብ መቃወማቸው ታውቋል። ወደ ሰሜን አሜሪካ እንዳይገቡ አዲሱ የጉዞ ማዕቀብ የተቀመጠባቸው ዜጎች ከሚያንማር፣ የኤርትራ፣ የኪርጊዚስታን፣ የናይጀሪያ የሱዳን እና የታንዛኒያ ስደተኞች መሆናቸው ታውቋል። የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ይፋ ባደረገው መልዕክቱ መንግሥት አዲስ ያወጣውን እርምጃ በድጋሚ እንዲያጤነው እና እገዳው ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጸምባቸውን ሰዎች ከግምት ውስጥ እንዲያስገባ አሳስቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሰሜን አሜሪካ መንግሥት የተወሰደው እርምጃ ስደተኞች ከወላጅ ቤተሰቦቻቸው እንዳይገናኙ እና በተለያዩ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሐይማኖታዊ ችግሮች ምክንያት አገራቸውን ለቀው ለሚሰደዱት ስደተኞች በሚደረግ እገዛ እና ድጋፍ ላይ ችግርን የሚፈጥር መሆኑን የጉዞ ማዕቀቡ ይፋ ከሆነ በኋላ የወጣው የብጹዓን ጳጳሳቱ መልዕክት አስታውቋል። አዲስ የተዘረጋው የጉዞ ማዕቀቡ ከዚህ በፊት በቁጥር 9645 ላይ ከተደነገገው እና ፕሬዚደንታዊ ደንብ ተብሎ ከሚታወቀው ደንብ ጋር የሚመሳሰል ሲሆን ይህ ደንብ በሀገራዊ ደህንነት ጉዳዮች ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የማይተባበሩ አገሮች ያሏቸውን ኢራን፣ ሊቢያ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ሶርያ፣ ቨነዙዌላ፣ የመን እና ሶማሊያ መሆናቸው ታውቋል።

ቤተሰብን የመለያየት ተግባር፣

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በመልዕክታቸው እንዳስታወቁት አሁን የወጣው አዲስ ደንብ ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2017 ዓ. ም. የወጣውን እና የአሜሪካ መንግሥት የሚመካበትን የሐይማኖት ነጻነት መብት የሚገድበውን ደንብ የሚያስታውስ  መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በማከልም አዲስ የወጣው ደንብ የቤተሰብ አባል ቢታመም እንኳ ሕክምናን የማግኘት መብት የሚገድብ መሆኑን አስረድተው፣ ከዚህም በተጨማሪ በጉዞ እገዳ ምክንያት በመለያየት ስጋት ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦች መኖራቸውን በሐዘን አስታውሰው አዲሱ ደንብ ችግሮችን የበለጠ ከማሳደግ ሌላ የሚሰጠው ፋይዳ የለውም ብለዋል።

ቤተሰብን ችግር ውስጥ የጣለ ደንብ ነው፣

አንድ አገር የዜጎቹን ደህንነትን የማስጠበቅ ግዴታ እንዳለበት እንገነዘባለን ያሉት የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ይህ ቢባልም ምንም ክፋት በሌለባቸው ቤተሰቦች ላይ ያልታሰበ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። በብጹዓን ጳጳሳቱ መልዕክት ማጠቃለያ ላይ ድምጻቸውን ያሰሙት የጉባኤው ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ ብሱዕ አቡነ ሆሲ ጎሜዝ፣ ወደ ሰሜን አሜሪካ የሚመጡትን ስደተኞች ተቀብሎ ማስተናገድ ባለፉት ትውልዶችም ዘንድ የተለመደ መሆኑን አስታውሰው፣ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተሰድደው ወደ ሰሜን አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች የእምነታቸውን እና የእውቀታቸውን እሴቶች ይዘው የሚመጡ በመሆናቸው ለአገር እድገት ከፍተኛ ድጋፍ የሚያበረክቱ መሆኑን አስረድተዋል።

የመንግሥት የጉዞ ፈቃድ ማዕቀብ ስደተኞችን አይመለከትም፣

በሰሜን አሜሪካ መንግሥት ያለፈው ዓርብ ታኅሳስ 22/2012 ዓ. ም. የተደነገገው የጉዞ ፈቃድ ማዕቀብ ስድስት አገሮች እነርሱም ሚያንማር፣ ኤርትራ፣ ኪርጊዚስታን፣ ናይጀሪያ ሱዳን እና ታንዛኒያ፣ በሀገራዊ ደህንነት ጉዳዮች ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ሆነው ወይም ሳይችሉ በመቅረታቸው የተነሳ መሆኑን ያስታወቀው የ“ዋይት ሃውስ” መግለጫ፣ የጉዞ ፈቃድ ማዕቀብ የስደት ጉዞን እንጂ የሃገር ጉብኝትን ጨምሮ ከሌሎች የጉዞ ዓይነቶች ጋር የማይገናኝ መሆኑን አስታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
05 February 2020, 15:05