ፈልግ

የስደተኞች ነፍስ አድን አግልግሎት በቀይ ባሕር፣ የስደተኞች ነፍስ አድን አግልግሎት በቀይ ባሕር፣  

“የክርስቲያኖች አንድነት ያስፈለገበት፣ የእግዚአብሔር እቅድ እንዲፈጸም ነው”።

ከዛሬ ጥር 9 - 16/2012 ዓ. ም. በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲን ዘንድ ለክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ጸሎት የሚደረግበት ሳምንት መሆኑ ታውቋል። በመሆኑም በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ በሚገኙ ቁምስናዎች ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የጸሎት እና የውይይት ዝግጅቶች የሚቀርቡ መሆኑ ታውቋል። ዘንድሮ የሚከበረው የክርስቲያኖች አንድነት ሳምንት ዋና ዓላማ በጦርነት፣ በአመጽ እና በሌሎች ማኅበራዊ ቀውሶች ምክንያት የሚከሰተውን የስደት ቀውስ ያገናዘበ መሆኑ ታውቋል። ይህን ማሕበራዊ ችግር መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ፕሮግራሞች በሀገረ ስብከት እና በቁምስና ደረጃ ተዘጋጅተው መቅረባቸው ታውቋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዘንድሮ ለሚካሄደው የክርስቲያኖች አንድነት ጸሎት እንዲሆን በማለት ከማልታ ደሴት የተላከ የጸሎት እና የአስተንትኖ ሃሳብ፣ በሐዋ. 28:2 ላይ “የደሴቲቱ ነዋሪዎችም የሚያስገርም ደግነት አሳዩን፤ ዝናብና ብርድ ነበርና እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን” በሚለው ጥቅስ ላይ  ያተኮረ መሆኑ ሲታወቅ ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ ከሌሎች የአገልግሎት ወንድሞቹ ጋር በመርከብ ወደ ሮም በተሰደደበት ጊዜ የማልታ ደሴት ነዋሪዎች ያደረጉትን መልካም መስተንግዶ የሚያስታውስ መሆኑ ታውቋል። 

የቅ. ጳውሎስ እና የዛሬው ዘመን የስደት ሁኔታ፣

የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የስደት ጉዞን መሠረት ያደረገ የዘንድሮ የክርስቲያንች አንድነት የጸሎት ሳምንት በዓለማችን ጎልቶ የሚታየውን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚያስታውስ ሲሆን፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ባጋጠመው የስደት ሕይወት ውስጣዊ ሰላምን ሊያገኝ የቻለው እምነቱን እና ተስፋውን በእግዚአብሔር እጅ እንዳደረገ የሚያስታውስ መሆኑ ታውቋል። በዘመናችን ለስደት የተጋለጡ በርካታ ሰዎች፣ በየብስም ሆነ በባሕር ላይ ጉዞ ለከባድ አደጋ እና ስቃይ የሚጋለጡ መሆናቸው ሲታወቅ፣ ለሰዎች መሰደድ ዋና ምክንያቱ ተፈጥሯዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ሰብዓዊ መሆኑ ከማልታ ደሴት ምእመናን የተላኩ አስተያየቶች አረጋግጠዋል።

ለስደት ቀውስ የሚሰጥ ግድየለሽነት፣

የስደተኞች ጉዳይ በአግባቡ አልታየም የሚሉ የማልታ ክርስቲያኖች፣ ስደተኞች ላይ የሚደርሱ ስቃዮችን ሲዘረዝሩ፣ ስደተኞቹ በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ ገብተው እስከ መታረድ እና አካላቸው ለሽያጭ የሚቀርብ መሆኑን አስታውሰው፣ አስጊ የሆነ የባሕር ላይ ጉዞ በሚያደርጉበት ጊዜ፣ በግድ የለሽነት ምክንያት የሕይወት ማዳን እርዳታ እንኳ የማይደረግላቸው መሆኑን አስታውሰዋል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸው ታሪክ፣ በዘመናችን ለተከሰተው የስደት ቀውስ የጋራ ምላሽ እንድንሰጥ ክርስቲያናዊ ግዴታ ያለባቸው መሆኑን የማልታ ምዕመናን ገልጸዋል። ምዕመናኑ በማከልም ያላቸውን ከተቸገሩት ወንድሞቻች እና እህቶቻችን ጋር በመካፈል፣ የእግዚአብሔርን ፍቅራዊ ቸርነት በተግባር እንገልጻለን ብለዋል።    

ለሳምንቱ ቀናት የሚቀርብ የጸሎት ሀሳብ፣

ለስምንት የጸሎት ቀናት እንዲሆን ተብለው የተዘጋጁ ርዕሦች፥ እርቅ፣ ብርሃን፣ ተስፋ፣ እምነት፣ ኃይል፣ መልካም መስተንግዶ፣ የሕይወት መታደስ እና ቸርነት መሆናቸው ታውቋል። ምሕረትን በማስቀደም የሚጀምር እያንዳንዱ የክርስቲያን መንፈሳዊ ጉዞ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃን ለመመስከር እና ከሌሎች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ያለንን አንድነት በገሃድ ለመመስከር የሚያስችል መሆኑን የማልታ ምዕመናን ገልጸዋል። በማልታ ደሴት ውስጥ ከሚኖሩ የተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ከፍተኛ ቁጥር እንዳላቸው ሲነገር በደሴቲቱ ውስጥ የክርስቲያኖችን ሕብረት አጉልተው የሚያሳዩ ባሕሎች አስቀድሞም መኖራቸው ታውቋል። በደሴቲቱ ውስጥ  የክርስቲያኖችን አንድነት የሚገልጽ የመጀመሪያው የጋራ ጉባኤ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1960ቹ ውስጥ መካሄዱ ታውቋል። በማልታ የክርስቲያኖች አንድነት ምክር ቤት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 1995 ዓ. ም. በኢየሱሳዊ ማኅበር ካህን በሆኑት በክቡር አባ ማውሪስ ኤሚኛን አስተባባሪነት፣ የሌሎች አብያተክርስቲያናትን በማሳተፍ መመስረቱ ታውቋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አብያተክርስቲያናቱ በሁለት ወር አንድ ጊዜ የጋራ ስብሰባዎችን በማካሄድ፣ የጋራ ውይይቶችን በማድረግ፣ እንዲሁም አስፈላጊውን እርዳታ ወደ አገራቸው ለሚደርሱት ስደተኞች ሲያበረክቱ መቆየታቸው ታውቋል።       

የማልታ ክርስቲያኖች ምስክርነት፣

በማልታ አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት የተዘጋጀውን የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት እንዲያተባብሩ፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት አስተባባሪ ጳጳሳዊ ምክር ቤት በኩል የተጠየቁት፣ በማልታ የክርስቲያኖች አንድነት እና የጋራ ውይይት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ሸሪ፣ ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ለዘንድሮ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ስለ ተመረጠው መሪ ቃል በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሐዋ. ሥራ መጽሐፍ  ምዕ. 28:2 ላይ “የደሴቲቱ ነዋሪዎችም የሚያስገርም ደግነት አሳዩን፤ በሚለው ጥቅስ ላይ ለማስተንተን መወሰናቸውን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ሸሪ፣ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ ጋር ሆኖ ማልታን አቋርጦ ወደ ሮም ባደረገው የስደት ጉዞ ወቅት የማልታ ክርስቲያኖች ያደረጉላቸውን መስተንግዶ የሚገልጽ መሆኑን አስረድተው፣ በማልታ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በመተባበር፣ በችግር ምክንያት ተሰድደው ወደ ማልታ የሚመጡ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በክብር ተቀብለው የሚያደርጉላቸው መስተንግዶ፣ አገልግሎት፣ እና ድጋፍ ክርስቲያናዊ ግዴታ መሆኑን ገልጸው፣ ዘንድሮ ለክርስቲያኖች አንድነት የሚደረግ ጸሎት መሪ ቃልም በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች፣ ለስደተኞች በሚደረግ የቸርነት አገልግሎት ላይ እንዲያስተነትኑ የሚጋብዝ መሆኑን አስረድተው፣ የተቸገረን መርዳት፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠ አደራ መሆኑን ተናግረው፣ በመካከላችን ድሃ እና አነስተኛ የሆኑት የኢየሱስ ክርስቶስ መሳሌ መሆናቸውን ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ሸሪ አስረድተዋል። 

ጎረቤታሞች የሆኑት የማልታ እና የጎዞ ደሴት ነዋሪዎች በልማድ እንግዳ ተቀባይ መሆናቸውን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ሸሪ፣ የእነዚህ ሁለት ትናንሽ ደሴቶች ነዋሪዎች በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም ካላቸው የማካፈል፣ የተቸገረን የመርዳት ባሕል ያላቸው መሆኑን ተናግረው፣ በሐዋ. ሥራ መጽሐፍ፣ በምዕ. 28 ላይ የተጠቀሰው ማንነታችንን ይገልጻል ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ሄክቶር አክለውም ዓለም አቀፍ የክርስቲያኖች አንድነት ዋና ዓላማም፣ በዘመናችን የሚከሰተውን አስከፊ ማሕበራዊ ቀውሶችንም ሆነ መልካም አጋጣሚዎችን በሕብረት ለመካፈል የሚያስችል መሆኑን አስረድተው፣ ቤተክርስቲያን በአንድነት ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ለመድረስ በጉዞ ላይ የምትገኝ መሆኗን አስረድተዋል።

ማልታ ለ160 ዓመታት ያህል በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር የነበረች መሆኗን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ሸሪ፣ የማልታ ሕዝብ ከተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር በሕብረት መኖሩን አስታውሰው፣ ዛሬ ደግሞ ከምስራቅ አውሮፓ አገሮች የመጡ የበርካታ ሕዝቦች ባሕሎችን እና የክርስትና እምነቶችን በማስተናገድ ላይ መሆኗን ገልጸው፣ በማከልም እነዚህ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ተከታዮች በመተባበር በርካታ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ እገዛን በማበርከት ላይ የሚገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል። በጋራ ሆነው በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙትን ማሕበራዊ እና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያግዙ የተናገሩት ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ሸሪ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ንግግር በማስታወስ እንደተናገሩት “የክርስቲያኖች አንድነት የሚያንጹ ሐዋርያዊ መልዕክቶችን ለማካፈል፣ የቸርነት አገልግሎቶችን ለማበርከት ብቻ የተቋቋመ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ የተገለጠበት በመሆኑ እርስ በርስ በመተማመን፣ በጋራ በመጸለይ፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት ማጠንከር ያስፈልጋል ብለው ክርስቲያናዊ ግዴታችን በዘመናችን እንድናከናውን እግዚአብሔር የሚጠይቀንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ማበርከት ነው ብለዋል።  

18 January 2020, 16:01