ፈልግ

አሜሪካዊ የመብት ተሟጋች የነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ አሜሪካዊ የመብት ተሟጋች የነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ 

ብጹዕ አቡነ ሆሴ ጎሜዝ፣ “የማርቲን ሉተር ኪንግ ሕልም እውን ለማድረግ ብዙ ይቀራል”።

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎሜዝ በማርቲን ሉተር ኪንግ የልደት ቀን መታሰቢያ በሆነው በጥር 11/2012 ዓ. ም. ባሰሙት ንግግር ፣ በሰሜን አሜሪካ በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ መድልዎ እና ኢፍትሃዊነት አፍሪካዊ ዝርያ ባላቸው ወጣቶች ላይ የሚፈጸም መሆኑን ተናግረው በማከልም በርካታ ጥቁር ያላቸው አፍሮ አሜሪካዊያን መገደላቸውን እና እስር ቤት መገኘታቸውን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሰሜን አሜሪካ በሚኖሩ አፍሮ አሜሪካዊያን ላይ የሚፈጸም በደል እና የዘር አድልዎ ዛሬም ቢሆን አለመወገዱን እናስታውሳለን ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ጎሜዝ፣ አሜሪካዊ የመብት ተሟጋች የነበሩት የማርቲን ሉተር ኪንግ ህልም መልስ አላገኘም ብለዋል። በሰሜን አሜሪካ የመብት ተሟጋች የነበሩት ማርቲን ሉተር ኪንግ ብሔራዊ የልደት ቀን መታሰቢያ በሆነው በጥር 11/2012 ዓ. ም. ባሰሙት ንግግር ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ጎሜዝ፣ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ለሚወደው ለአፍሮ አሜርካዊያን መብት ሲል ሕይወቱን አሳልፎ መስጠቱን አስረድተዋል።

ዘረኝነትን ለመቃወም የተኬደው መንገድ በቂ አይደለም፣

የመብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ ለተጨቆኑት፣ መብታቸውን ላጡት እና ከማሕበረሰቡ ማካከል ለተገለሉት ፍትህን እና ማሕበራዊ ለውጥን ለማስገኘት ያደረገው ሰላማዊ ጥረት የፍቅር ምስክርነት እንደ ነበር ያስረዱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ጎሜዝ፣ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር፣ የዘር መድልዎን ለማስወገድ እና ፍትሕን ለማምጣት የተደረጉ በርካታ ጥረቶች መኖራቸው ቢታወቅም የተኬደው መንገድ በቂ አይደለም ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎሜዝ አክለውም በወጣት አፍሮ አሜሪካዊያን ላይ የሚደርስ በደል መበራከቱን፣ የዘር መድልዎ መኖሩን፣ ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ የግድያ እርምጃ የሚወሰድባቸው መሆኑን እና ለእስር መዳረጋቸውን አስታውሰዋል። በመብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ የሕይወት ዘመን የነበሩ ድሃ እና የተጎሳቆሉ መንደሮች አሁንም በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

እውነተኛ የልብ መለወጥ ያስፈልጋል፣

በመጨረሻዎቹ ዓመታት በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ዘረኝነት መስፋፋቱን ተመልክተናል ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ጎሜዝ፣ በአፍሮ አሜሪካዊያን፣ የላቲን አሜሪካ ዝርያ ባላቸው፣ እንዲሁም በሌሎች ስደተኛ ዜጎች ላይ የሚወሰድ የግድያ እርምጃ መጨመሩን ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳሱ አክለውም በሰሜን አሜሪካ ሕዝቦች መካከል እውነተኛ የልብ መለወጥ እንዲታይ፣ ከዚህም በተጨማሪ በማሕበረሰቦቻቸው እና በማሕበራዊ ተቋሞቻችው ተሐድሶ እና ለውጥ እንዲደረግ በማለት፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2018 ዓ. ም. የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ይፋ ያደረጉትን ሐዋርያዊ መልዕክት በመጥቀስ ጥሪ አቅርበዋል።    

ማርቲን ሉተር ኪንግን በክብር ማስታወስ የሚቻልበት መንገድ፣

ማርቲን ሉተር ኪንግን ማስታወስ የሚቻለው በፍቅር የተገነባ ማሕበረሰብን በመፍጠር፣ የሰሜን አሜሪካ ዜጎች በሙሉ፣ ወንድ እና ሴቶች፣ የእግዚአብሔር ልጆች፣ በእርሱ አምሳል የተፈጠሩ፣ እኩል ሰብዓዊ ክብር እና መብት ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ ነው ብለዋል። የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሆሴ ጎሜዝ፣ የማርቲን ሉተር ኪንግ ዝክረ ቀን ምክንያት በማድረግ ያሰሙትን ንግግር ሲያጠቃለሉ፣ የመብት ተሟጋች የነበረውን ማርቲን ሉተር ኪንግን በክብር ማስታወስ የሚቻለው ሰዎችን በቆዳ ቀለማቸው፣ በቋንቋቸው እና በትውልድ አካባቢያቸው ምክንያት የሚደረግባቸውን ልዩነቶች ማስወገድ ሲቻል ነው ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
20 January 2020, 15:00