ፈልግ

የታኅሳስ 21/2012 ዓ.ም ዘኖላዊ (የስብከተ ገና 3ኛ) ሳምንት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ የታኅሳስ 21/2012 ዓ.ም ዘኖላዊ (የስብከተ ገና 3ኛ) ሳምንት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ 

የታኅሳስ 26/2011 ዓ.ም ዘኖላዊ (የስብከተ ገና 3ኛ) ሳምንት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

መልካም እረኛ

የእለቱ ምንባባት

1.     ዕብ 13፡ 16-25

2.     1ጴጥ 2፡21-25

3.     ሐዋ 11፡22-30

4.     ዮሐንስ 10፡ 1-21

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

“እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች ጒረኖ በበሩ ሳይሆን፣ በሌላ በኩል ዘሎ የሚገባ ሌባና ነጣቂ ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን እርሱ የበጎቹ እረኛ ነው፤ በር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል። የራሱ የሆኑትንም ሁሉ ካወጣ በኋላ ፊት ፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። እንግዳ የሆነውን ግን ድምፁን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ ፈጽሞ አይከተሉትም።” ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን ምን እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም።

ስለዚህ ኢየሱስ ዳግም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ቀማኞች ነበሩ፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ሁሉ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅ፣ ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ይመጣል፤ እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ።”

“መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል፤ ተቀጣሪው እረኛ ግን በጎቹ የእርሱ ስላልሆኑ፣ ተኵላ ሲመጣ ጥሎአቸው ይሸሻል፤ ተኵላውም በጎቹን ይነጥቃል፤ ይበትናቸዋልም። የሚሸሸውም ተቀጣሪ ስለ ሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው።

“መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤ ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህ ጒረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ። እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለማንሣት ሕይወቴን አሳልፌ ስለምሰጥ አባቴ ይወደኛል። ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ ለማንሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልሁትም ከአባቴ ነው።”

ከዚህም ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ተፈጠረ። ብዙዎቹም፣ “ጋኔን ያደረበት እብድ ነው፤ ለምን ትሰሙ ታለችሁ?” አሉ። ሌሎች ግን፣ “ይህ ጋኔን ያደረበት ሰው ንግግር አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ስውርን ዐይን መክፈት ይችላልን?” አሉ።

 

የታኅሳስ 21/2012 ዓ.ም ዘኖላዊ (የስብከተ ገና 3ኛ) ሳምንት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

የተወደዳችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በታላቅ መንፈሳዊነት ለማክበር ያስችለን ዘንድ የመዘጋጃ ወቅት የሚሆነን የስብከተ ገና ሳምንት የዛሬ ሦስት ሳምንት ገደማ መጀመሩ ይታወሳል። ይህ ሦስተኛ ስብከተ ገና ወቅት ወይም ሳምንት ዘኖላዊ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ትርጉሙም የእረኛው ኢየሱስ ሰንበት ማለት ሲሆን እግዚአብሔር ምን ያህል እያንዳንዳችንን ፈልጎ ለማግኘትና ለመንከባከብ፣ እንዲሁም የእርሱና ለእርሱ፣ ከእርሱ እንዲሁም በእርሱ መሆናችንን እንገነዘብ ዘንድ በዚህ መንፈስ የእርሱ ልደት ለማክበር እንድንዘጋጅ ተጋብዘናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ መልካም እረኛ ነኝ” በማለት መልካም እረኛ የራሱን ነፍስ ለሌሎች አስላፎ እንደ ሚሰጥ ይናገራል። ይህ ኢየሱስ ራሱን በራሱ ያቀረበበት አገላለጽ፣ በስሜታዊነት የተሞላ ሐሳብ ሳይሆን ግልጽ በሆነንና ተጨባጭ በሆነ መልኩ የተገለጸ ንግግር ነው! ኢየሱስ ሕይወትን የሚሰጠን እርሱ ራሱ ሕይወቱን ለእኛ አስላፎ የሚሰጥ እረኛ በመሆን ነው። ለእኛ ሲል ሕይወቱን አስልፎ በመስጠት፣ ኢየሱስ ለእኛ ለእያንዳንዳችን እንዲህ ያላል “ሕይወትህ ለእኔ በጣም ዋጋ ያለው ነው፣ አንተን ለማዳን እራሴን እሰጣለሁ” ይለናል። ይህ ራሱን የመስጠቱ ሁኔታ ነው እንግዲህ እርሱ ከሁሉም ለየተ ያለ መልካም እረኛ መሆኑን የምያሳየው፣ አዳኝ መሆኑንም ያሳያል፣ ውብ የሆነ እና ፍሬያማ የሆነ ሕይወት እንድንኖር የሚያስችለን እርሱ ነው።

በተመሳሳይ መልኩም በሁለተኛው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ውስጥ ኢየሱስ እኛን ሊፈውስ እና ህይወታችን ደስተኛ እና ፍሬያማ እንዲሆን ሊያደርግ የሚችለው እንዴት እንደ ሆነ በመግለጽ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤ ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ” (ዩሐንስ 10፡11-18) ይለናል። ኢየሱስ ሰለአንድ አእምሮኣዊ እውቀት አልተናገረም፣ በፍጹም አለተናግረም! ነገር ግን እርሱ የተናገረው በግለሰብ ደረጃ ከእርሱ ጋር ግንኙነት እንድንመሰርት እርስ በእርስ የመተሳሰብ ስሜት በእሱና በአብ መካከል አንድ ዓይነት የሆነ የፍቅር ግንኙነት ነጸብራቅ እንዲኖረን ነው። ይህ ማለት ከኢየሱስ ጋር ያለን ህይወት የሚገለፅበት ባህሪ ነው፣ እርሱ በሚገባ እንዲያውቀን ለእርሱ ራሳችንን መስጠት የሚለውን ያሰማል። ራሳችንን በራሳችን ዘግተን መኖር ማለት ሳይሆን ኢየሱስ በሚገባ እንዲያውቀን ለእርሱ ራሳችንን መክፈት የገባናል ማለት ነው። እርሱ ለእያንዳንዳችን ትኩረት ይሰጣል፣ ልባችንን በጥልቀት ያውቃል፡ ድክመቶቻችንን እና ስህተቶቻችንን፣ ከእዚህ ቀደም ያከናወናቸውን መልካም ነገሮችን እና እንዲሁም በከንቱ ያለፉትን የተስፋ ጊዜያትን እርሱ በሚገባ ያውቃቸዋል። እንዲሁ እንዳለን ከእነ ሁለንተናችን ይቀበለናል፣ ከእነ ኃጢኣታችን ይቀበለናል፣ ልያድነን፣ ሊፈውሰን፣ በፍቅር ሊመራን ይፈልጋል ምክንያቱም በመንገድ ላይ ደክመን እንዳንጠፋ እና መንገዳችንን እንዳንቀይር እርሱ ከእኛ ጋር ሁሌ አብሮን ይሆናል።

እኛም በበኩላችን ኢየሱስን እንድናውቀው ተጠርተናል። ይህ ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ያመልክታል። እይህም በራሳችን የመመካት ዝንባሌን በመተው በአዲስ ጎዳና ላይ ለመራመድ መዘጋጀት ማለት ሲሆን ይህም ክርስቶስ ራሱን የተገለጠበት እና እርሱ ራሱ ወደ ከፈተው ስፊ አድማስ መራመድ ማለት ነው። ከኢየሱስ ጋር ያለን ግንኙነት ሲበላሽ፣ የእርሱን ድምጽ ለማዳመጥ እና ማኅብረሰቡ በታማኝነት እርሱን ለመከተል የነበረው ፍላጎት ሲቀዘቅዝ በእዚያ ስፍራ ከወንጌሉ ጋር ያልተጣጣሙ ሌሎች የአስተሳሰብና የኑሮ አመራሮች መኖራቸው የማይቀር ጉዳይ ነው። ከኢየሱስ ጋር ያለንን ግንኙነት እያጠናክርን ለመጓዝ እንችል ዘንድ እናታችን ቅድስ ድንግል ማሪያም ትርዳን።

የተወደዳችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ! አንደ ሚታወቀ ዛሬ በስብከተ ገና ሦስተኛ ሳምንት ላይ እንገኛለን። የገና ሚስጢር እና አስደናቂነት እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያሳየው በአክብሮትና በንጽህና የተሞላ ፍቅር ዓመታዊ አስታዋሾች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ልጅ በዚያች የድሆች ከተማ በሆነችው ቤተልሔም ውስጥ መምጣት አስደናቂ እውነታ ለጥቂት ጊዜ ቆም ብለን በአትኩሮት ስናስብ ከራሳችን ማንነትና ዙሪያችንን ከከበቡን ጉዳዮቻችን ሁሉ ለመውጣት እንገደዳለን፡፡ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ለእግዚአብሔር አብ አዳኝ ፍቅርና መለኮታዊ ጥበቃ ምስጋና ወደ ማቅረብ አዲስ አድናቆት ወደ መቸር ከፍ ከፍ እንላለን፡፡

የስብከተ ገና ወራት የመታደሻ፣ አዲስ እምነት የመቀበያና የመለወጫ ጊዜ ነው፡፡ ይህ ወቅት ለመንፈሳዊ እድገት እንቅፋት የሚሆኑትን በርካታ የችግር ሰንሰለቶች የመበጠሻ ጊዜ ነው፡፡ ወቅቱ ከእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይሉና ጥበቃው በሕይወታችን ላይ ካስቀመጣቸው ከወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋርም የአንድነት መተሳሰሪያ ገመዳችንን የምናጠብቅበት ጊዜ ነው፡፡ አንዱ የመጠቀሚያ ዘዴያችንም የእርቅና የፍቅር የሆነው የንስሐ ቅዱስ ሚስጥር ነው፣ ይህ ሚስጢር ኃጢአትን ይቅር ለማለት የሚደርስልንና እውነተኛውን ውስጣዊ መለወጥ ለማግኘት የሚያስችለንነ ፀጋ የያዘ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡

ጌታ በኛ ተፈልጐ መገኘት ያለበት ነው /በርሱ በኩል የሚቻለውን ያህል ቀርቧልና/፡፡ እርሱ እኛ ዘወትር ልንፈልገው የሚገባና እንደ ተገናኘንም ወዲያውኑ ሕይወታችንን ሊለውጠው ዘወተር ተዘጋጅቶ የሚጠብቀን ነው፡፡ እርሱን ፍለጋ እንድንሄድና ልባችንና ነፍሳችን አጥብቀው የሚሹትን አምላክ ፍለጋችንን ቀጥለን እስክናገኘው ድረስ እግዚአብሐር ይደበቅብናል፡፡ በዚህ ምድር ላይ የምናሳልፈው ሕይወታችን የማያቋርጥ ፍለጋ ያለበት፣ እግዚአብሔርን እስከምናገኘው ድረስ መሻታችንን የምንቀጥልበት፣ ካገኘነውም በኋላ ለሁል ጊዜውም ካጠገባችን ሳይለይ እንዲኖር የምናደርግበት ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡ በእርግጥ ከልብ የምንወደው ከሆነ እግዚአብሔርን ማግኘት ማለት ዘወተር አጥብቀን ይዘነው መቆየት ማለት ነውና፡፡

እርሱን ፍለጋ በምንሔድበት ጊዜ፤ ፍለጋህ በሙሉ ልብህና ነፍስህ ከሆነ በእርግጥም ጌታን ታገኘዋለህ፡፡

እርሱን ለመፈለግ ታዲያ እንዴት ነው ልባችንንና ነፍሳችን የምናዘጋጀው? የርሱን ትእዛዛት ለመጠበቅ ለራሳችን ውሳኔ ባሳለፍንበት ቀን፣ የራሳችንን ማንነትና ውስጣችንን መርምረን ንስሐ ለመግባት ቁርጥ ውሳኔ ባደረግንበት ቀን የዚያን ጊዜ ስለርሱ መረዳት እንጀምራለን፣ ልናገኘው ተስፋ አድርገን ፍለጋውን የጀመርንለትን እርሱን ለማየት እንችል ዘንድ ዓይኖቻችን ይከፈታሉ፡፡ ምክንያቱም ልበ ንፁሃን እስካልሆንን ድረስ እርሱን ለማየትና ለማግኘትም አንችልምና ነው፡፡

እርሱን ለመፈለግና ለማግኘት መንገድ ከመጀመራችን በፊት ራሳችንን በጥንቃቄ መመርመርና በልባችን አዳራሽ ውስጥ የተቀመጠው ማን እንደሆነ ተገቢነት ለርሱ ለጌታችን መቀመጫ በሆነው የልባችን አዳራሽ ውስጥ ምን በመካሔድ ላይ እንደሆነ ማየትና ማወቅ አለብን፡፡ በሌላ አነጋገር እርሱን እንግዳችንን ይዘን የምንገባበትን ክፍል ማጽዳት አለብን፡፡ ጌታን ማግኘት ማለት እርሱን መያዝና በልባችን ውስጥ እንዲቀመጥ ወደ ውስጣችን መስገባት ማለት ነውና ጌታም ወደ እኛ ለመምጣትና ከኛ ጋር ለመኖር ይፈልጋል፡፡

እርሱን መፈለግ የሚገባን ያህል የማንፈልገው ከሆነ ምክንያቱ በንስሐ አገባባችን ላይ የሚጐድል ነገር መኖሩና እኛም ከኃጢአታችን ክብደት ለማዳን የተፈለገውን የሕማምና የሥቃይ መስዋዕትነት ልክ አለመገንዘባችን ነው፡፡ የኃጢአተ ይቅርታን ማግኘት አስፈላጊነት ስናውቅና ልምዱም ሲኖረን ብቻ እኛን ይቅር ለማለት ዘወትር ዝግጁ ሆኖ ወደማጠብቀን ጌታ ከልብ ተፀፅተን ፊታችንን ለማዞር የምንችለው ያኔ ብቻ ነው ከልብ በመነጨ ፍቅር እሱን መፈለግና መከተልም የምንጀምረው፣ ምክንያቱም ብዙ ኃጢአት ይቅር የተባለለት በፋንታው ደግሞ ብዙ ይወዳልና፡፡

"ስለዚህ ተስፋ የቆረጠውን ሁሉ በርታ አይዞህ አትፍራ እግዚአብሔር ሊታደግህ ይመጣል" (ኢሳ. 35፡4) እግዚአብሔር ሁሉንም ነገሮች የሠራቸው ለራሳቸው ሲል አይደለም ነገር ግን ለታላቅ ፍጥረት ነው፡፡ ሁሉ ነገር ከተዘጋጀ በኋላ የዚህን ታላቅና ሰፊ ዓለም ንጉሥና ገዢ ሠራ ሰውን ፈጠረ፡፡ መለኮታዊ አስትንፋሱን በሰው ላይ ተነፈሰ፣ ልጁም አደረገው ከዚያም ገደብና ድንበር በሌለው በዘላለማዊ ደስታ ሰውን ተካፋይ እንዲሆንለት እጅግ ከፍተኛ ጉጉት አደረበት፡፡

ሆኖም ግን ሰው ታዛዥ ባለመሆኑ የተነሣ የእግዚአብሔርን እቅድ አበላሸ፡፡ ያም ሆኖ ግን እግዚአብሔር ጨርሶ አልተወውም፣ እራቀውም፡፡ ስለዚህ አዲስና እጅግ አስደናቂ የሆነ እቅድ አዘጋጀ በህልማችን እንኳን ጨርሶ ይሆናል ብለን ያላሰብነውን ዓይነት የሰውን ልጅ እርሱ ወዳዘጋጀለት ታላቅ ደስታ ለማምጣት ነው አዲሱን ዕቅድ የነደፈው፡፡ የሰው ልጅ ዘላለማዊ ደስታን ይጐናጸፍ ዘንድ እግዚአብሔር ያለውን ታላቅ ጉጉት ለማሳየት በመለኮታዊ፣ ጥበብ፣ ሃይልና ፍቅር እስከ መናገር ደረጃ ደረሰ፡፡ አንድያና ብቸኛውን ልጁን የምስጢረ ሥላሴ ሁለተኛውን አካል የሆነውን ልጁን እጅግ አሳፋሪና አሰቃቂ የሆነውን የመስቀል ሞት እንዲሞትና በዚህም ሳቢያ የሰው ልጅ ፈጣሪው ለርሱ ያለውን ፍቅርና የዘላለምንም ደስታ እንዲያገኝ ያለውን ጉጉት እንዲገነዘብ ሁሉም ሰብዓዊ ፈጡር ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስ ያንን ተወዳጅ ልጁን የሰው ልጆች ቤተሰብ አባል አድርጐ ወደ ምድር ላከው፡፡

እርሱ መለኮታዊ ሕይወት መልሶ ሰጥቶናል፣ በድጋሚ ልጆቹ አድርጐናል፣ የርሱ የሆነችው ቤተክርስቲያን አባል አድርጐናል በርሷ አማካይነትም እንደ እግዚአብሔር ልጅነታችን ይህንን ወደ ምድር የተላከውን አዳኝ ለነፍሳችን መጠበቂያ የምንወስደው ምግብና መጠጥ አድርጐ ሰጥቶናል፡፡ በሁሉም የሕይወት መከራዎችና ፈተናዎች ውስጥ ይጠብቀናል፣ ይመራናል፡፡

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

04 January 2020, 09:33