ፈልግ

የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ  

የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መሰረታዊ የሆኑ ጽንሰ-ሐሳቦች

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ በሚል አርእስት ስለካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ለእዚህ ለካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መሰረት የጣሉ የቤተ-ክርስቲያን ቀኖናዎችን፣ አንቀጸ እምነቶችን፣ አስተምህሮዎችን፣ እንዲሁም ይህንን የቤተ-ክርስቲያኗን ማኅበራዊ አስተምህሮ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት የቤተ-ክርስቲያን አባቶች የጻፏዋቸውን ሐዋርያዊ መልእክቶች እና ቃለ ምዕዳኖችን በመዳሰስ፣ ነባራዊ የሆነውን የዓለማችንን፣ የቤተ-ክርስቲያናችንን እና የአገራችንን ሁኔታ በዳሰሰ እና ከግምት ባስገባ መልኩ ወደ እናንተ በማቅረብ ላይ እንደ ምንገኝ ይታወቃል።

በክፍል አንድ ዝግጅታችን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ ጠቅላላ ይዘቱን እና ፅንሰ-ሐሳቡን መመልከት መጀመራችን ይታወሳል። በክፍል አንድ ዝግጅታችን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ ጠቅላላ ይዘቱን እና ፅንሰ-ሐሳቡን በቀጣይነት በተከታታይ ለምናደርገው አስተምህሮ የመሰረት ድንጋይ የሚጥል በመሆኑ የተነሳ አንድ በአንድ መመልከት መጀመራችን የሚታወስ ሲሆን በዛሬው በክፍል ሁለት ዝግጅታችን ደግሞ የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መሰረታዊ የሆኑ ጽንስ-ሐሳቦችን በጥልቀት እንዳስሳለን።

ቤተ-ክርስቲያን በክርስቶስ ከተመሰረተችበት ቀን አንስቶ እስከ ዛሬ ቀን ድረስ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች ድምጽ በመሆን፣ በተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ በሕዝቦች ላይ የሚደረሰውን ማኅበራዊ ጫናና በደል በመቃወም ለዓለም ድምጽዋን ስታሰማ መቆየቷን፣ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በቀጥታ ሰላማዊ በሆነ መልኩ የመሳተፍ መብት እንዲኖራት ሕጋዊ እና ስነ-ምግባራዊ በሆነ መልኩ እንድትሳተፍ መብት የሚሰጣትን ዋና ዋና መሰረታዊ የሆኑ ሐሳቦችን በክፍል አንድ ዝግጅታችን መጥቀሳችን ይታወሳል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ትሳተፋለች ሲባል በአንድ አገር ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ትገባለች ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ሲሆን፣ ነገር ግን በተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጫናዎች ምክንያት በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱትን በደሎች፣ ኢፍታዊ ተግባሮችን፣ በተለይም ደግሞ ዝቅተኛ እና ድሃ በሚባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም ለዓለም ድምጿዋን ታሰማለች ማለት እንደ ሆነ ልብ ሊባል ይገባል። በእዚህ ረገድ የቤተ-ክርስቲያናችን ተልዕኮ አንድ እና አንድ ብቻ ነው፣ ቤተ-ክርስቲያን በክርስቶስ የተመሰረተችው የመላእክት ጠባቂ ለመሆን ሳይሆን የሰው ልጆችን አቅፋ ደግፋ፣ በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲኖሩ በማድረግ፣ የሕዝቡ ደስታ ደስታዬ፣ የሕዝቡ ለቅሶ ደግሞ ለቅሶዬ ወይም ሐዘኔ ነው በማለት ሕዝቡ በሰላም እና በደስታ እግዚኣብሔር የሰጣቸውን በረከት እየታቋዳሱ እንዲኖሩ ለማድረግ፣ በመጨረሻም የሰው ልጆችን ለእግዚኣብሔር መንግሥት የማብቃት መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ የሆነ ተልዕኮ እንደ ተሰጣት ይታወቃል።

በመጽሐፍ ቅዱሳችንም ውስጥ ይህ ጽንሰ ሐስብ በብዙ ስፍራዎች ተጠቅሶ እናገኛዋለን። ለምሳሌ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል (ሉቃስ 4፡18) በማለት ኢየሱስ እዚህ ምድር የመጣበት ዋነኛ ዓላማ ሲገልጽ እንሰማለን። በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው እና የድኾች አባት በማባል የሚታወቀው የፈረንሳይ ሀገር ተወላጅ የነበረው ቅዱስ ቪንሰንት ይህንን የእየሱስን ዓላማ የግሉ መፈክር አድርጎ በመያዝ በወቅቱ በፈረንሳይ ሀገር ለነበሩ የድኸ ማህበረሰቦች አልኝታነቱን በመግለጽ ሐብታሞችን ከድኾች ጋር የሚያገናኝ ድልድይ በመሆን ማኅበራዊ ፍትህ ይሰፍን ዘንድ የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋጾ አድርጎ ማለፉን፣ በተመሳሳይ መልኩም በጣም ብዙ የሚባሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቁዱሳን ለድኾች ያላቸውን አለኝታ በመግልጽ ጭቆና እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች እንዲወገዱ የበኩላቸውን ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን አድርገው አለፈዋል። ቤተክርስቲያናችንም የክርስቶስን እና የእነዚህ ቅዱሳንን ፈለግ በመከተል በሕዝቦች ላይ የሚፈጸሙትን በደሎች ሁሉ በደሏ በማድረግ፣ ለቅሶዋቸው ለቅሶዋ፣ ሐዘናቸው ሐዘኔ ነው በማለት አሁንም የሰላም እና የፍትህ ጥሪዋን ታሰማለች።

ቤተክርስቲያን ይህንን የምታድርግበት ምክንያት ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደ ሞከርኩት “የሰው ልጆችን ማዕከል” ባደርገ መልኩ ነው። የሰው ልጆች ባሉበት እመንት አለ፣ እምነት ባለበት ቤተክርስቲያን አለች፣ በተክርስቲያን ባለችበት ማኅበረሰብ አለ፣ ማኅበርሰብ ባለበት ደግሞ መልካም እና ክፉ የሆኑ ነገሮች ይንጸባረቃሉ፣ ቤተ-ክርስቲያን ስነምግባራዊ የሆኑ እሴቶች ተጠብቀው እንዲሄዱ፣ ሰዎች በስላም እና በመከባበር እንዲኖሩ መልካም የሆኑ ነገሮችን በማበረታታት በተቃራኒው ደግሞ የማኅበርሰቡን ሰላም የሚነሱትን ክፉ ነገሮችን በብርቱ ትቃወማለች፣ እንዳይስፋፉም በቅዱስ ወንጌል እና በስበዓዊነት ላይ የተመሰረቱ አስተምህሮችን ትሰጣለች። ምክንያቱም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጫናዎች እና ኢፍታዊ ድርጊቶች ምክንያት የሚጎዳው ያው የሰው ልጅ በመሆኑ የተነሳ ነው፣ በተለይ በአቅም ደካማ የሆነ እና ድኸ የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል በመሆኑ የተነሳ ማኅበራዊ አስተምህሮ አስፈላጊ እንደ ሆነ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ታምንበታለች።

ክቡራን እና ኩብራት ተከታታዮች በዛሬው እለት ዝግጅታችን የካቶልክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መሰረታዊ ዝንጽ-ሐሳቡን እና ሕጋዊ መሰረቱን በተመለከተ ያዘጋጅንላችሁ የክፍል ሁለት ዝግጅት በእዚህ አላበቃም። የዛሬ ሳምንት የእዚህን አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል ይዘንላችሁ እንቀርባለን። አባራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

20 January 2020, 13:30