ፈልግ

ኢየሱስ የአምላክ ክቡር ስም ነው፣ መድኃኒት ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ የአምላክ ክቡር ስም ነው፣ መድኃኒት ማለት ነው፡፡  

የኢየሱስ ስም

የጥር 13/2012 ዓ.ም አስተንትኖ

ጌታ አምላክ ሆይ ስምህ በዓለምና በምድር ሁሉ ክቡርና የተመሰገነ ነው፡፡ (መዝ. 8) “ስሙ ቅዱስና አስደናቂ ነው” (መዝ. 110) ቅዱስ በርናርዶስ ስለዚህ ነገር ሲናገር “የኢየሱስ ስም በአፍ ማር፣ በጆሮ ጣዕም ያለው ዜማ፣ የልብ ደስታ ነው$ ይላል፡፡ ይህ ስም ከሰማይ የመጣ መልአክ የገለጠው መለኮታዊ ስም ነው፡፡ “ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ፤ ወንድ ልጅ ትወልጂያለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፡፡ እርሱ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡ እግዚአብሐር አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፡፡ ለዘለዓለም በያዕቆብ ቤት ይነግሣል” (ሉቃ. 1፣30)፡፡ እንዲሁም ዮሴፍ መጠራጠር ሲጀምር “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ እጮኛህን ማርይምን ለመውሰድ አትፍራ፡፡ ምክንያቱም ከእርስዋ የሚወለደው ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ወንድ ልጅ ትወልዳለች ስሙንም ኢየሱስ ብለህ ትጠራዋለህ፡፡ እርሱ ሕዝቡን ሁሉ ከኃጢአት ያድናቸዋል” (ማቴ፣ 2፣21) አለው፡፡ ዮሴፍም እንደተነገረው ከእንቅልፉ ተነሥቶ ሁሉን በትሕትና ፈጸመ፡፡

ኢየሱስ የአምላክ ክቡር ስም ነው፣ መድኃኒት ማለት ነው፡፡ “ምክንያቱም እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ሊያድናቸው ነው” ቅዱስ ጳውሎስ “በኢየሱስ ስም ጸድቃችኋል” (ሮሜ 10፣13) ይለናል፡፡ ኢየሱስ ሁሉን ሥነ-ፍጥረት በእጁ የያዘ አምላክ ቢሆንም ስለ እኛ ትሕትናንና ደኀንነትን ወደደ፣ መለኮታዊ ማዕረጉን ትቶ እኛን ሊያድን ደካማ ባሕርያችንን ለበሰ፡፡ በደሙ መስዋዕት ከኃጢአት እንዲያነጻን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲያስታርቀን ከእርሱ ጋር እንዲያገናኘን የሰማያት መዝገብ ከፈተልን፡፡ “አምላክ ነው ግን ክብሩን አዋረደ፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፣ ባሪያ መሰለ፣ እስከ ሞትም ታዘዘ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ከሁሉ የሚበልጥ ስም ሰጠው፡፡ በማሰይና በምድር በባሕርም ከምድርም በታች ሳይቀር ሁሉ ጉልበት ለኢየሱስ ስም እንዲንበረከክ አደረገ” (ፊሊ. 2፣8-11) ይላል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡

ኢየሱስ ኃይለኛ ስም ነው፡፡ በመሆኑም ሳውል የኢየሱስን ተከታዮች እያሰረና እየገረፈ ሲያሳድድ ይህን አረማዊ ሥራ ተግባራዊ ለማድረግ ሲሄድ በደማስቆ አካባቢ በደረሰ ጊዜ መብረቅ ከሰማይ በድንገት መጥቶ በምድር ላይ ጣለው፡፡ መጣል ብቻ ሳይሆን ዓይኑንም አሳወረው፡፡ “ሳውል! ሳውል! ስለምን ታሳድደኛለህ;$ አለው ኢየሱስ፡፡ እሱም በምድር ወድቆ ዓይኑ ታውሮ ጌታ ሆይ አንተ ማንነህ; ሲል ጠየቀው፡፡ “እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ክርስቶስ ናዝራዊ ነኝ” ብሎ መለሰለት (የሐዋ. 9፣5-8) ስንት ጠላቶቹ በፊት ወድቀው ለስሙ ኃይል ተንበርክከዋል፡፡

የኢየሱስ ኃይል ሁሉን የሰማይንና የምድርን ኃይል ያሸንፋል፣ ደንደናና አመጸኛ ልብን ሳይቀር ያሟሽሻል፣ የኢየሱስ ስም ተአምራዊ ነው፡፡ “በኢየሱስ ስም$ ብቻ በሽተኞች ይፈወሳሉ፣ ዕውሮች ያያሉ፡፡ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፣ ሙታን ይነሣሉ፣ በማይታወቅ አዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፣ መርዝ ቢጠጡ እንኳ አይጐዳቸውም በሽተኞችን ይፈውሳሉ” (5 17፣18) ይላል ኢየሱስ ራሱ፡፡

የኢየሱስ ስም ምሕረት ነው፡፡ በስሙ ኃጢአት ይደመሰሳል፣ ጸጋን እንቀበላለን፡፡ ስሙ ከጠላት ዲያብሎስ የሚከላከልልን ጋሻችንና መከታችን ነው፡፡ “ረዳታችን የእግዚአብሔር ስም ነው$ ይላል ዳዊት፡፡ “አባቴን በስሜ ብትለምኑ ይሰጣችኋል” (ሉቃ. 10፣199) ይለናል ኢየሱስ መድኃኒታችን፣ ጠበቃችን፣ የኃጢአታችን ካሣ ነው፣ ተስፋችን በስሙ ብቻ ነው፡፡ ይኸው ቅዱስ ስሙ በልባችን ሲታተም ያን ጊዜ የሚደፍረን የለም፡፡ በፍቅሩ ጸሎታችን ወደ አባታችን ወደ ሰማይ እናደርሳለን በአስፈለገን ጊዜ ሁሉ ስሙን እንጥራ፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን  

22 January 2020, 13:28