ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት 

“የቅዱስ እስጢፋኖስ የሰማዕትነት ሕይወት ለእኛ ለካቶሊካውያን ልዩ ጸጋና ትምሕርት የሰጠናል”

በቫቲካን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጲያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ መቶኛ ዓመት የምስረታ በዓል በጥር 02/2012 ዓ.ም በደመቀ ሁኔታ መከበሩ ይታወቃል። በማግስቱ ጥር 03/2012 ዓ.ም በቫቲካን ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው ቀዳሜ ሰማዕት በመባል የሚታወቀው የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት አመታዊ በዓል በደመቀ ሁኔታ በርካታ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት ተክብሮ አልፏል። በወቅቱ የተደርገውን መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ሲሆኑ ብጹነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት “የቅዱስ እስጢፋኖስ የሰማዕትነት ሕይወት ለእኛ ለካቶሊካውያን ልዩ ጸጋና ትምሕርት የሰጠናል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅታችን ተከታታዮች ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት በወቅቱ ያደርጉትን ስብከት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።   

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ ኣሜን።

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ እንኳን ለቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በተለይም በዛሬው ዕለት በታላቅ ድምቀት ለምናከብረው 100ኛ ዓመት የቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላምና በፍቅር አደረሳችሁ። መሥዋዕተ ቅዳሴ ስንጀምር ሚመጠን ግርምት ዛቲ ዕለት ወዕጽብት ዛቲ ሰዓት ይህች ሰዓት ምን ያህል ምታስደንቅ ናት ብላን ጀምረናል።

እውነትም ለእኛ ለኢትዮጲያና ኤርትራ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ልጆች ይህቺ ቀን ልዩ ቀን ናት። እግዚኣብሔር በቸርነቱ ለኢትዮጲያውያንና ኤርትራውያን ይህንን የቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳምና የኢትዮጲያ ኮሌጅ ኣዘጋጅቶልን በኣንዲት ቅድስት ካቶሊካዊት ሓዋርያዊት ቤተክርስቲያን እምነት እንድንጸናና ከቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ጋር በፍጹም ሕብረት እንድንጓዝ ትልቅ ሥጦታ ሠጥቶናል።

በታላቋ ቅድስት ከተማ በሮማ እምብርት በምተገኘው ቫቲካን ከተማ ውስጥ በልዩ ክብር ይህ ገዳምና ኮሌጅ መገኘታቸው ለሁለቱም ሃገሮች ካቶሊካውያን ብቻም ሳይሆን ለሃገሮቻችን ሕዝቦች ኩራት የማንነትና የአብሮነት መገለጫ ሆነዋል።

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሃገራችን ክርስትና ጥንታዊነት መንፈሳዊነትና ታሪካዊ መሆኗን በመረዳት ለነጋዲያን ኣባቶቻችን ከዚያም ቤተክርስቲያንን ለሚመሩ እረኞች ካህናት የሕንጸት ቦታ ኣዘጋጅታ ቤተክርስቲያናችን የዚህ ኮሌጅ ፍሬ በሆኑ ልጆቿ ስትመራ ቆይታለች። አሁንም እየተመራች ትገኛለች። በዚህ ገዳምና ኮሌጅ ብዙ የቤተክርስቲያን መሪዎች መጥተው በፍቅር በተስፋና በቅድስና ቤተክርስቲያንን መርተው ብዙ ሕዝቦችን ወደ እግዚኣብሔር ምሕረትና ፍቅር አድርሰዋል። ይህ ትልቅ ጸጋና በረከት ነው። ለዚህ በረከት ነው ዛሬ ሁላችንም እንዲህ ባማረ ሁኔታ በዚህ ታሪካዊና ቅዱስ ሥፍራ ተገኝተን እግዚኣብሔርን እያመሰገንን የምንገኘው። እግዚኣብሔር ለእኛ ለልጆቹ ትልቅ ውለታ ውሎልናልና ሥሙ ከዘለዓለም እስከዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን። የሃገራችን ታሪክ በዚህ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምብርት ውስጥ ይጻፍ ዘንድ መሠረት ለጣሉ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኣበው ቅዱሳን እንዲሁም ነጋዲያን ምሥጋና ይድረሳቸው።

ይህንን ቅዱስ ሥፍራ ያቆዩልን ኣባቶቻችን በረከታቸው በእኛም ላይ ይደርብን። እኛም ልጆቻቸው ታሪኩንና መንፈሳዊነቱን ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የምንችልበትን ጸጋ አብዝቶ ይስጠን። ይህ ገዳም በቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት የተሠየመ ነው። በክርስትና ታሪክ በእምነቱ ምክንያት ሰማዕትነት በመቀበል የመጀመሪያ የሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ የዚህ ገዳም ባልደረባ ነው። ዛሬም የዚህ ታላቅ ሰማዕት ዓመታዊ ክብረ በዓል ከ100ኛ ዓመት ክብረ በዓል ጋር በአንድነት በድምቀት ይከበራል።

 የቅዱስ እስጢፋኖስ የሰማዕትነት ሕይወት ለእኛ ለካቶሊካውያን ልዩ ጸጋና ትምሕርት የሰጠናል። ክርስቲያናዊ ሕይወት ፍሬ የሚያፈራው በፍጹም ለእግዚኣብሔር መሰጠትና በቁርጠኝነት የቅድስናን መንገድ መከተል እንደሆነ ያስተምረናል። የቅዱስ እስጢፋኖስ የመሰጠት ሕይወት በሐዋርያት ሥራ ከምዕራፍ 6-7 በዝርዝር ተፅፎ እናገኘዋለን። ቅዱስ እስጢፋኖስ በምሕረትና በይቅርታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በመከተል ምጥቀት ላይ የደረሰ ታላቅ ቅዱስ ነው። እርሱም ልክ እንደ ክርስቶስ በድንጋይ እየወገሩት ሳለ ለገዳዮቹ ምሕረትን ለበደሉት ሁሉ ይቅርታን ለመነ።

ቅዱስ እስጢፋኖስ የሚያስተምረን የሰው ልጅ እግዚኣብሔር ያዘጋጀለትን ዘለዓለማዊ መንግሥት ወራሽ ለመሆን የሚችለው በፍጹም ፍቅር ራሱን ለእግዚኣብሔርና ለፍጥረት ሁሉ አሳልፎ በመስጠት እንዲሁም በፍጹም የይቅርባይነት መንፈስ በምሕረት መንገድ ላይ መመላለስ ከቻለ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ መሥዋትነትን ይጠይቃል። አንዳንዴም የሕይወት ዘመናችን ሰማዕታት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ የመጡበት ሁኔታ በሰፊው ይስተዋላል። በተለያዩ ኣህጉራት በሚገኙ አገሮች ውስጥ ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት ይሰደዳሉ ይገደላሉ። በየጊዜው በተለያዩ ዜና ማሰራጫዎች የምንሰማው ዜና ይህንኑ እውነታ ያረጋግጥልናል። ለዚህም በጥቂቱ በዚህ በቅርብ ዓመታት በሊቢያ የተገደሉ ኢትዮጲያውያንን እንዲሁም ሌሎች ክርስቲያኖችን ማሰቡ በቂ ይሆናል።

የሰማዕታት ደም የእምነት ዘር ነው። የቅዱስ እስጠፋኖስን ሥም ለምንጠራ ለእኛ ዛሬም ወንጌልን በድፍረት በፍቅርና በትህትና መስበክ እንድንችል ያግዘናል። እኛ ካቶሊካዉያን ከሰማዕታት ጋር ህብረት አለን። ይህ ህብረት ደግሞ በእምነታችን እንድንጸና በፍቅር እንድንኖር በቅድስና እንድንመላለስ ያግዘናል። የዛሬም ጸሎታችን በዚህ ታላቅ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ አማካኝነት በሃገሮቻችን በተለይም በኢትዮጲያና በኤርትራ ለምተገኘው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የእምነት ጀግኖች እንዲበዙላት እንማጸነዋለን። ይህን በዓል ለሁላችንም የበረከትና የፍቅር የእምነት መጠንከር እንዲሁም በቅድስና የመመላለስን ጸጋ የምንቀበልበት ይሁንልን። ለሃገሮቻችን እንዲሁም ለሕዝቦቻችን የፍቅር የሠላም የኣንድነትና የደስታ በዓል ያድርግልን። እንኳን ደስ አለን።

12 January 2020, 16:03