ፈልግ

ሀብታችን በሰማይ ይሁን ሀብታችን በሰማይ ይሁን 

ሀብታችን በሰማይ ይሁን

ሥጋ ለባሾች እንደ መሆናችን መጠን የምድር ነገር ያሰንፈናል፣ ሀብትን እንወዳለን፣ ምድራዊ ነገር ምንም እንኳ አላፊና ጠፊ እንደሆነ ብንረዳ በልባችን እንፈልገዋለን፡፡ በዚህ ኢየሱስ «ሀብታችሁን በምድር አታከማቹ፣ ምክንያቱም ብልና ዝገት ያበላሹታል፣ ሌቦችም ይሰርቁታል፤ መዝገባችሁንና ሀብታችሁን በሰማይ አከማቹ በዚያ ያለው ሀብት ብልና ዝገት ሊያጠፋው አይችልም፣ ሌቦችም ሰብረው ሊሰርቁት አይችሉም፡፡ ሀብትህ ባለበት ልብህ በዚያ ይገኛል´ (ማቴ. 7፣19-21) እያለ ያስጠነቅቀናል፡፡ ኢየሱስ ይህን ሲነግረን ምድራዊ ነገርን ንቃችሁ ጣሉ በምድር ሀብትን መሰብሰብና ማከማቸቸት ተው ማለቱ አይደለም ነገር ግን ዋና ሐሳባችሁ በሰማይ መንፈሳዊ ሀብትን ማከማቸት ይሁን ማለቱ ነው፡፡ በምድር ሀብታችሁን አታከማቹ፣ ምድራዊ ነገር አላፊና ቶሎ የሚበላሽ ነው፡፡ እኛ በዚህ ዓለም ወርቅ፣ ጥሪት፣ ክብር፣ ችሎታ እናገኛለን ስንል እብዶች እንሆናለን፡፡ ሀብታሞች ሆነን ለመኖር እንዲመቸን እንጓጓለን፣ ብዙ እንሠራለን፣ እንደክማለን፣ እንለፋለን፣ በዚህ ረገድ ስንት ስቃይ ይደርስብናል።

ሐሳባችን ለምድራዊ ነገር ያዘነብላል፣ ሌሊትና ቀን ለሥጋችን የማያገለግል ገንዘብ መፈለግ ይሆናል፣ ባገኘነው መጠን ሌላ ለመጨመር እንባዝናለን፡፡ ይህንና እርሱን የሚያህል ጥረት ካደረግን ማግኘታችንን ወይም አለማግኘታችንን አናውቅም፡፡ ብናገኘም እንደምናስበው ውስጣዊ ዕረፍትን ከሚሰጠን ይልቅ መከራና ጭንቀት ይፈጥርብናል፡፡ ይህ ብቻ አይደም እንዳንዴ በስንት ምክንያት ይጠፋል; ሰው ይወስድብናል ወይም ደግሞ በስንፍናችንና በጥጋባችን በከንቱ እናጠፋዋለን፡፡ የባሰ ግን ከዚህ ዓለም ለዘለዓለም ስንሰናበት ለሌሎች ትተነው እንሄዳለን፡፡ ይህን ሁሉ ለፍተን ሳንጠቀምበት ለሌሎች ያልፋል፣ እነርሱ  ሲጠቀሙበት እኛ ባዶ እጃችንን ወደ መቃብር እንወርዳለን፡፡ ሀብታችን በሰማይ ይሁን፣ በሰማይ የምናከማቸው ሀብት እውነተኛና ፍጹም ለዘለዓለም የሚኖር ነው፣ አንድ እንኳ ሊያበላሸው ወይም ሊሰርቀው የማይችል ለዘለዓለም የሚኖር መንፈሳዊ ሀብት ነው፡፡ ይህ ሀብት ፍጹም ደስታ ይሰጠናል፣ ለዘውትር ይከተለናል፣ ይህ ሀብት ካለን ለዘለዓለም በመንግሥተ ሰማያት ልንነግሥ እንችላለን፣ ብፁዓን እንሆናለን፡፡ የምድር ሀብት ከዳተኛና አላፊ በመሆኑ የሰማዩን ሀብት እንፈልግ፣ የኢየሱስን ቃል ሰምተን በሰማይ የጽድቅ ሀብት እናከማች፣ ጥረታችን ለዘለዓለም የሚጠቅመንን የጽድቅ ፍሬ መፈለግ መሆን አለበት፡፡ የዕለት ጭንቃችን በሰማይ ዘለዓለማዊ ሀብት ማብዛት ይሁን፡፡

31 January 2020, 14:55