ፈልግ

ኢየሱስ በዕድሜ፣ በጸጋና፣ በጥበብ ያድግ ነበር ኢየሱስ በዕድሜ፣ በጸጋና፣ በጥበብ ያድግ ነበር 

ኢየሱስ በዕድሜ፣ በጸጋና፣ በጥበብ ያድግ ነበር

የሉቃስ ወንጌል ስለ ኢየሱስ ሕይወት በናዝሬት ሲናገር “በእግዚአብሔርና በሰው ፊት በዕድሜ በጸጋና በጥበብ ያድግ ነበር” ይላል፡፡ ሰው እንደመሆኑ ኢየሱስ እንደ አዳም ልጅ ሁሉ እያደገና በዕድሜ እየጨመረ ይሄድ ነበር። በሥጋ እያደገ ሲሄድ የአእምሮ ብስለቱም እያደገ መጨረሻ የሌለው ጥልቅና ሰፊ ዕውቀቱ ቀስ በቀስ ይጐለብት ነበር። እንደ ፀሐይ ብርሃን እያደር እየደመቀ ይመጣ ነበር፡፡ አይሁዳውያን ይህንን አይተው “ይህ ወላጆቹ የምናውቃቸው የአናጢው የዮሴፍና የማርያም ልጅ አይደለምን” (ማቴ 13፡55/ማር 6፡3) እያሉ ያሽሟጥጡበት  ነበር።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ መልአክቱንና ከሁሉ አስቀድሞ የአባቱን ፈቃድ ይፈጽም ነበር፡፡ በመቀጠልም የሰውን ደኀንነት ይገልጽ ነበረ፡፡ በመንፈሱ ዘወትር ከሰማያዊ አባቱ ጋር አንድ ሆኖ ይኖርና በሁሉ ነገር እርሱን ለማስደሰት ይሠራ ነበር፡፡ “በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው” (ማቴ 3፡17) እያለ ሰማያዊ አባቱ ይመሰክርለታል፡፡ ኢየሱስ ሥራውን ሁሉ ተመልካቾቹን በሚያንጽ አደራረግ ይፈጽም ስለነበር ሕይወቱ የበለጠ የፍጽምና ምሳሌ ነበር፡፡ በአደገ መጠን ስለ ነፍሳት ያስብ ነበር፡፡

ኢየሱስ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት በዕድሜ በጸጋና በጥበብ አያደገ ይሄድ ነበር ብለናል፡፡ እኛስ በእዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው እይደግን የምንገኘው? እንደዚህ ያለ ግልጽ የሆነው አፍአዊ ዕድገት ይታይብናል ወይ?; አምላክና ሰው በሥጋ ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ጭምር ወደ ፊት እንደምናድግ ሊመሰክሩልን በቻሉ ነበር፡፡ ወደፊት አንደምንራመድ ማን ሊመሰክርልን ይችላል; እንጃ የሚመሰክር የሚገኝ አይመስለኝም በሥጋዊ ኑሮአችን እያደግን እየነቃን ብንሄድም በመንፈስ ግን እንደዚህ አይደለንም፡፡ በሥጋዊ ኑሮአችንና ሕይወታችን ሁልጊዜ እየተሻሻልን እየሰለጠንን እንሄዳለን፡፡ በመንፈስ በኩል ዘወትር ሕፃን እንሆናለን እንጂ እስከ ብስለት ድረስ የምናድግ አይደለንም፡፡ በአንጻሩ ወደ ኋላ እናፈገፍጋለን፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አንድ እርምጃ ወደ ፊት በሄድን ቁጥር ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ እንመለሳለን፡፡

በሥጋ በአደግን እና በሠለጠንን ቁጥር በመንፈስ እንደክማለን፡፡ እየቀዘቀዝን መንፈሳዊ ጉዳያችን ሁሉ ቸል እንላለን፡፡ ኢየሱስን በሥጋ ዕድገታችን እንከተለዋለን፡፡ በእርግጥ በመንፈስ ግን ፈጽሞ እንከተለውም፡፡ ሰይጣንን እየተከተልን ከኢየሱስ ብዙ ወደ ኋላ እንቀራለን፡፡ በመንፈሳዊ ተግባራችን ብንበረታ በድሮ ኑሮአችን ላይ ተገትረን አንቆምም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የአቅማችንን ባለማድረጋችን እና ጥረት ባለማድረጋችን የመጣ ነው። የመንፈስ ኑሮ እንደ ሥጋዊ ነገር ሆነ ብለን ስለማንከታተለው ነው፡፡ በሥጋ ወደ ፊት በመንፈስ ግን ወደ ኋላ መሄድ የዓለም ልጆች ተግባር ነው፡፡ በመንፈስ እየበለጡ ወደ ፊት መሄድ የእግዚአብሔር ልጆች ጠባይ ነው፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን እንግዲህ ክርስቶስን እንምሰል፣ በተለይ በመንፈስ ወደ ፊት እንራመድ፡፡ በሥጋ በአደግን መጠን አንዲሁ በመንፈስ እየተሻሻልን መሄድ ይገባናል፡፡

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

17 January 2020, 14:43