ፈልግ

የጥር 10/2012 ዓ.ም ዘናዝሬት እለተ ስንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የጥር 10/2012 ዓ.ም ዘናዝሬት እለተ ስንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የጥር 10/2012 ዓ.ም ዘናዝሬት እለተ ስንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.     ሮሜ. 15፡1-13

2.     ዮሐ. 4፡14-21

3.     ሐዋ.ሥ. 13፡32-43

4.     ማቴ.2፡19-23

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

 

ከግብፅ ወደ ናዝሬት

ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ተመለስ፤ ሕፃኑን ለመግደል የሚሹት ሞተዋልና” አለው። ዮሴፍም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤ ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ቦታ በይሁዳ መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ጌታ በሕልም ስላስጠነቀቀው፣ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ ናዝሬት ወደምትባል ከተማም ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚህም በነቢያት፣ “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተ-ክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘናዝሬት የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን። በዚሁ ሰንበት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ሰዎች በኩል አድርጐ ለእኛም መልእክቱን ያስተላልፍልናል። እርሱም እንደሚለን በምድር ላይ በምንኖርበት ጊዜ ስለራሳችን ብቻ ሣይሆን ስለሌሎችም ማሠብ መጨነቅ እንደሚያስፈልግ ይናገራል። “ብርቱ የሆኑ ሰዎች የደካሞችን ወድቀት መሸከም አንዳለባቸው ያሳስባል”። ይህ ማለት ለምሳሌ አንድ ሰው ቶሎ የሚቆጣ ከሆነ፣ በመስከር ቤተሰቡንና ጐረቤቱን የሚበጠብጥ ከሆነ፣ ሰውን ሁሉ የሚሳደብና የሚያስቀይም ከሆን በቃ ይህ ሰው ፀባዮ ነውና ተውት እንዳሻው ያድርግ ማለት ሣይሆን ያንን ሠው ከዚህ አስነዋሪ ሥራው እንዲመለስ በተደጋጋሚ በፍቅርና በትሕትና መርዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ነው የደካሞችን ሸክም መሸከም ማለት ካለበት አስከፈ ሁኔታ ወይንም ባሕሪ እንዲላቀቅ ማገዝ መርዳት ማለት ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከነ ውድቀታችን፣ ከነደካማነታችን ተቀብሎናል። በኋላ ግን ከውድቀታችን አነሣን ተመልሰን እንዳንወድቅም በምን አቅጣጫ መጓዝ እንዳለብን መንገዱን በፍቅርና በትሕትና አስተማረን።

ይህም ሆኖ በድካማችን ብዛት ብንወድቅም የምንመለስበትን መንገድ ምሥጢረ ንሰሀን አበጀልን። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዚሁ መልዕክቱ በመቀጠል ክርስቲያኖች አንድ ልብ አንድ ሐሳብ ሆነው እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግኑ ይመክራል። ምክንያቱም ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በኖረበት ዘመን አይሁዳውያን እኛ ከመጀመሪያው ጀምሮ እግዚአብሔርን እናውቃለን በማለት አረማውያንንና ከአረማውያን ወገን የሆኑትን ክርስቲያኖችን ሁሉ ይንቁ ነበር፡፡

በዚህ በተከፋፈለ ልብ ግን እግዚአብሔርን ማመስገን እንደማይቻል ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ይናገራል ለዚህ ነው ክርስቲያኖች በአንድ ልብ በአንድ ሐሳብ እግዚአብሔርን ያመስግኑ የሚለው፡፡  በክርስቲያን ማኀበረሰብ ውስጥ መከፋፈልና መለያየት ካለ ይህ መንፈስ ከእግዚአብሔር የመጣ መንፈስ አይደለም ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንፈስ ሁሌም የአንድነትና የመተባበር የመረዳዳትና የመከባበር መንፈስ ነው ፡፡

ዛሬም ምንአልባት ይህ ክስተት በኛ በክርስቲያኖች መካከል ሊኖር ይችላል፡፡  ሀብታሞች፣ ድሆችን, የተማሩት ያልተማሩትን, ጤነኞች በሽተኞችን ለመቀበል የሚቸገሩበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡

ይህ ግን የክርስቶስ ወዳጅ ነኘ በሚል ሰው የክርስቶስ ተከታይ ነኝ በሚል ሰው ሊንፀባረቅ አይገባም፡፡  ምክንያቱም ዓላማችን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ, በፍጹም ሐሳብ በፍጹም ኃይል መውደድና ባልእንጀራችንን እንደራሳችን አድርገን መውደድ ነውና፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ በመልዕክቱ “ እግዚአብሔር ፍቅር ነው ” ይላል ስለዚህ ይህን ፍቅር የሆነን አምላክ የምናፈቅረው በፍርሃትና በመርበድበድ ሳይሆን በፍቅር ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡

እግዘአብሔርን ይቀጣናል ወደ ገሃነም ይከተናል በሚል ሐሳብ የምንቀርበው ከሆነ የምናመልከው ከሆነ ይህ ስሕተት ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሁሌም ፍቅር የሆነ ፍቅርን የሚሰጥ ፍቅርን የሚያበረታታና ስለ ልጆቹ ፍቅር ብሎ ሕይወቱን በመስቀል ላይ ሰቶ ያዳነን አምላክ ነው ፡፡

በዚሁ በዮሐንስ መልዕክት 4፣18 ላይ “በፍቅር ፍርሃት የለም ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል፣ ፍርሃት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና፡፡ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም” ይላል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን በፍጹም ፍቅር እንጂ በፍርሃት መንፈስ ልናፈቅረው አይገባም፡፡ ባለ እንጀራችንንም እንዲሁ ንጹህ በሆነ ፍቅር እንጂ ብድር ስለሚመልስ መሆን የለበትም፡፡ ሉቃስ 14፣13 እንዲህ ይላል ግብዣ ባዘጋጀህ ጊዜ ድሆችን አካለ ስንኩሎችን ሽባዎችንና ዓይነስውሮችን ጥራ ትባረካለህም እነዚህ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ በጻድቃን ትንሣኤ እግዚአብሔር ራሱ ብድራትህን ይመልስልሃል፡፡

የማቴዎስ ወንጌል 2፡19-23 ላይም እግዚአብሔርን የሚወድና በእርሱ ፈቃድ የሚመላለስ ሰው እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ እንደሚረዳው፣ እንደሚመራው፣  እንደሚያግዘው፣ ያስተምረናል። የፃድቁ የቅዱስ ዬሴፍ ሕይወት የሚያመላክተን ይህንኑ ነው። ገና ከጅምሩ እመቤታችን ድንግል ማርያምን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከፀነሰችበት ጊዜ አንስቶ እግዚአብሔር ምን ማድረግ እንዳለበት ይነግረው ነበር በሕልሙ ይገልፅለት ነበር፡፡  እርሱም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድይመላለስ ነበር፡፡ ወደ ግብፅ እናቱንና ሕፃኑን ይዞ እንዲሄድ እንደነገረው አሁን ደግሞ ከግብፅ ወደ እስራኤል እንዲመለስ ነገረው፡፡

እኛም በሕይወታችን ለእግዚአብሔር ታማኞች ታዛዦች ከሆንን እርሱን ከልባችን በማፍቀር በእርሱ እቅድ የምንመላለስ ከሆንን እሱ ሁሌም ከእኛ ጋር ይሆናል በለመለመው መስክም ይመራናል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ታላቅ ሥራ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት እንድትሆን ስትመረጥ በደስታ መቀበሏ ሳይገርመን አይቀርም። በወቅቱ ማርያም ለምንድር ነው፣ ሌሎች የአካባቢዋ ወጣት ልጃገረዶች ለግል ሕይወት እንደሚጨነቁ ሁሉ ከእጮኛዋ ከዮሴፍ ጋር የነበራትን ግንኙነት ለማጠናከር ያልተጨነቀችው? ቅድስት ድንግል ማርያም ጥሪው ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ ልዩ ጥሪ መሆኑን በተረዳች ጊዜ ራሷን የእግዚአብሔር አገልጋይ መሆኗን ይፋ ለማድረግ ወይ ለማሳወቅ ወደ ኋላ አላለችም  “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች (ሉቃ. 1፡38)። በዚህ የተነሳ ከእርሷ የሚወለድ ሕጻን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅነቱን ለዓለም ይገልጻል። ታላቅነቱን የሚገልጸው ከማርያም በመወለዱ፣ ወይም በእርሷ እናትነት ሳይሆን ከሁሉም በላይ ማርያም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽማ ስለተገኘች ነው። ኢየሱስም እንዲህ አለ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ናቸው” አለ (ሉቃ. 11፡28) እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም ማለት ነው። ቅድስት ማርያም በሕይወቷ እየሆነ ያለውን ነገር በሚገባ ሳትረዳው ስትቀር በዝምታ በማሰላሰል፣ ለመለኮታዊ ሃይል ሥራ አድናቆቷን ታሳይ ነበር። በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሥር መገኘቷ ራሷን ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ማስገዛቷን ያረጋግጣል።

ቀጥሎም እጮኛዋ ዮሴፍን ስንመለከት፣ ቅዱስ ወንጌል አንዳች ነገር ስለ ዮሴፍ ባይነግረንም እርሱ የሚሆነውን ሁሉ እየተመለከተ መታዘዝን ብቻ መምረጡን እንገነዘባለን። እርሱ ዝምታን የሚመርጥ፣ መታዘዝን ብቻ የመረጠ መሆኑን እንመለከታለን። ዛሬ ከማቴ. 2፡ 13-15 እና ከ19-23 የተነበበው ቅዱስ ወንጌል የዮሴፍን ታዛዥነት ሥስት ጊዜ ያረጋግጥልናል። የመጀመሪያው ቤተሰቡን ይዞ ወደ ግብጽ ምድር መሰደዱን፣ ቀጥሎም ከግብጽ ወደ እስራኤል ምድር መመለሱን ይነግረናል። ጥበቃ እንዲደረግለት ከእግዚአብሔር ዘንድ በተላከው ቅዱስ መልአክ በመመራት ቤተሰቡን ወደ ወደ ሩቅ አገር በመውሰድ ከሄሮድስ ጥቃት ሊያድን ችሏል። ይህን ክስተት በጥልቀት ስንመለከት ዛሬ በዘመናችን፣ በርካታ ቤተሰቦች ላይ የደረሰውን እና በመድረስ ላይ ያለውን የስደት ሕይወት የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብም መጋራቱን እንመለከታለን። የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ፣ በዓለማችን በአመጽ፣ በጦርነት፣ በተለያዩ የጭቆና አገዛዝ ምክንያት መኖሪያቸውን ለቅቀው ከሚሰደዱት ቤተሰቦች ጋር መሆናቸውን እንረዳለን።

በመጨረሻም ሦስተኛው የቅዱስ ቤተሰብ አባል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጸመበት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው ሁለተኛ መልዕክት እንደሚነግረን “ምክንያቱም እኔም ሆንሁ ሲላስና ጢሞቴዎስ፣ እኛ የሰበክንላችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘አዎን’ እና ‘አይደለም’ አልነበረም፤ ነገር ግን በእርሱ ዘወትር፣ ‘አዎን’ ነው” በማለት የእግዚአብሔር ፈቃድ በእርሱ መገለጡን ይገልጽልናል።(2ቆሮ. 1፡19) የእግዚአብሔር ፈቃን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ውስጥ መገለጹን በተደጋጋሚ እናያለን። ከእነዚህም መካከል ጠፍቶባቸው በመጨነቅ ሲፈልጉት ለነበሩት ማርያም እና ዮሴፍ፣ ባገኙትም ጊዜ ለምን እንዲህ እንዳደረገ በጠየቁት ጊዜ እርሱም፣ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። (ሉቃ. 2፡49) በዮሐ. 4፡34 ላይም “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው በማለት መለሰላቸው። በማቴ. 26፡42 ላይም “አባት ሆይ፤ ይህ ሳልጠጣው የማያልፍ ጽዋ ከሆነ፣ ፈቃድህ ይፈጸም” ብሎ ጸለየ።

እነዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ቃላት ወይም ንግግሮች በሙሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ በእርሱ ፍጻሜን ማግኘቱን ያረጋግጣሉ። ስለዚህ ክርስቶስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ ብሏል፤ “መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም፤ ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሚቃጠል መሥዋዕትና ለኀጢአት በሚቀርብ መሥዋዕት ደስ አልተሰኘህም። በዚያን ጊዜ እንዲህ አልሁ፤ ‘ስለ እኔ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈ፣ አምላክ ሆይ፤ እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ”። (ዕብ. 10፡5-7) እንደዚሁም  “እነሆ፤ መጥቻለሁ፤ ስለ እኔ በመጽሐፍ ተጽፎአል፤ አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ።” በታላቅ ጉባኤ ውስጥ ጽድቅን አበሠርሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ እንደምታውቀው፣ ከንፈሮቼን አልገጠምሁም። (መዝ. 40፡ 7-9)

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቅዱስ ዮሴፍ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱም የእግዚአብሔር ፈቃድ በግልጽ የተፈጸመባቸው የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተስብ አባላት ናቸው። ሦስቱም የእግዚአብሔር ፈቃድ በእነርሱ በኩል እንዲገለጽ አንዱ ለሌላው እገዛን አድርገዋል። ይህንንም በጸሎታቸው፣ በዕለታዊ ሥራዎቻቸው እና ባሳዩት የሕይወት ምስክርነት ገልጸዋል። ለመሆኑ ስንቶቻችን በቤተሰብ መካከል እርስ በእርስ በመነጋገር እና በመመካከር ራሳችንን መግለጽ እንችላለን። ወይም ብዙዎች እንደሚያደርጉ በገበታ ዙሪያ ለመግብ ተቀምጠው በስልክ ከጓደኞቻቸው ጋር እንደሚገናኙ ሰዎች ነን። በዚያ ቤተሰብ መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነት የለም፣ በዚያ ቤተሰብ መካከል ጸጥታ እንጂ የቃላት ልውውጥ የለም። በቤተሰብ መካከል ውይይት፣ ንግግር ሊኖር ይገባል። የቤተሰብ አባል የሆኑት በሙሉ፣ እናት፣ አባት፣ አያት ልጅ፣ እህት ወንድም እርስ በእርስ መነጋገር፣ መወያየት፣ መመካከር ይኖርባቸዋል። የናዝሬቱን ቅዱስ ቤተሰብ በምናስታውስበት በዛሬው ዕለት ማስታወስ ያለብን ቀዳሚ ተግባር በቤተሰብ መካከል መወያየት፣ መረዳዳት እና መመካከር እንዲኖር ማድረግ ነው። ለዚህም ዋና ምሳሌ የሚሆነው የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ በመሆኑ እገዛውን እንለምናለን።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን 

17 January 2020, 14:57