ፈልግ

“ማሕልየ መሓልይ” (ከመዝሙሮች ሁሉ የሚበልጥ መዝሙር) “ማሕልየ መሓልይ” (ከመዝሙሮች ሁሉ የሚበልጥ መዝሙር) 

በጣሊያን ውስጥ የካቶሊክ እና የአይሁድ እምነት ተከታዮች የወዳጅነት ቀን በማክበር ላይ ይገኛሉ።

ከጥር 7-8/2012 ዓ. ም. በጣሊያን የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን እና የአይሁድ እምነት ተከታዮች የወዳጅነት ቀን በማክበር ላይ መሆናቸው ታውቋል። የወዳጅነት ቀን ዋና ዓላማ በሁለቱ የእምነት ተቋማት መካከል ያለውን የረጅም ዓመታት ግንኙነት የበለጠ ለማዳበር፣ መንፈሳው እሴቶችን ለመጋራት፣ መሠረተ ቢስ የሆኑ ልዩነቶችን አስወግደው የእርስ በእርስ ትውውቅን ለማሳደግ የሚያግዙ የጋራ ውይይቶችን ለማድረግ መሆኑን የሁለቱ ሐይማኖት አባቶች፣ ብጹዕ አቡነ አምብሮጆ ስፕሪያፊኮ እና መምህር ዶ/ር ጁሰፔ ሞሚሊያኖ ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለሁለት ቀናት የሚከበረው የወዳጅነት ቀን በሁለቱም የሐይማኖት ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ያለው፣ በጣሊያን የሚገኙ የካቶሊክ እና የአይሁድ እምነት ተከታዮች የጋራ እሴቶችን ለይተው ለማወቅ፣ ጥርጣሬን አስወግደው መተማመንን እና ወዳጅነትን ለማሳደግ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ሁለቱም የሐይማኖት አባቶች ገልጸዋል። ዛሬ ሐሙስ ጥር 7/2012 ዓ. ም. ተጀምሮ እስከ ዓርብ ጥር 8/2012 ዓ. ም. ድረስ የሚቆየው የወዳጅነት ቀን በዓል ዘንድሮ ለ31ኛ ጊዜ የሚከበር መሆኑ ታውቋል። ይህን ዓመታዊ የወዳጅነት ቀን ምክንያት በማድረግ በጣሊያን ውስጥ በሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች እና ቁምስናዎች ውስጥ የሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች፣ ሁለቱም የሐይማኖት ተቋማት አባላት ስነ መለኮታዊ፣ ሐዋርያዊ እና ባሕላዊ እሴቶቻቸውን ወደ ብርሃን በማውጣት፣ የጋራ ውይይቶችን በማድረግ፣ የበለጠ ለመተዋወቅ እና ለመቀራረብ ዕድል የሚያገኙበት መድረክ መሆኑን ሁለቱም የእምነት አባቶች ገልጸዋል። በሚቀጥለው ዓመት፣ ጥቅምት 18/2013 ዓ. ም. በጣሊያን የሚገኙ ሁለቱ የእምነት ተቋማት ስነ መለኮታዊ ፣ ሐዋርያዊ እና ባሕላዊ እሴቶቻቸውን እርስ በእርስ ለመጋራት የሚያስችል “የእኛ ዘመን” የተሰኘ ሰነድ ተሰማምተው ያጸደቁበት 25ኛ ዓመት የሚከበርበት ዕለት መሆኑ ታውቋል።

ከዚህ በፊት በተከበሩ ዓመታዊ በዓላት ላይ ፣ በመጽሐፈ ሩት እና በመጽሐፈ አስቴር የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ላይ ማስተንተናቸውን የገለጹት፣ በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የክርስቲያኖች አንድነት እና የጋራ ውይይት ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት እና የበዓሉ አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ አምብሮጆ ስፕሪያፊኮ፣ ዘንድሮ ጥር 7 እና 8/2012 ዓ.ም. በሚከበረው የወዳጅነት ቀንም በማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ላይ የሚያስተነትኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ብጹዕ አቡነ አምብሮጆ ስፕሪያፊኮ በቃለ ምልልሳቸው እንደገለጹት፣ ሁለቱም የሐይማኖት ተቋማት አባላት  በሕብረት ሆነው የሚያስተነትኑባቸውን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ መርጠው ያቀረቡት፣ በጣሊያን የአይሁድ እምነት ተከታይ ማሕበረሰብ ተጠሪ ከሆኑት ከመምሕር ሪካርዶ ዲ ሰኚ ጋር በመወያየት መሆኑን አስረድተው፣ ለዘንድሮ የወዳጅነት ቀን እንዲሆን የተመረጠው የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ፣ ካቶሊካዊ ምዕመናን የአይሁድ እምነት ሥርዓተ አምልኮን፣ መንፈሳዊ በዓላትን፣ ባሕሉን እና ታሪኩን ለማወቅ ስለሚያግዝ ነው ብለዋል።

በጣሊያን ውስጥ የአይሁድ እና የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ወዳጅነት፣

በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚገኘውን የሥልጣን ተዋረድ ስንመለከት፣ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ቅድስት መንበር፣ የአይሁድ እምነት መምህራን፣ በእስራኤል የሚገኙ ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው የአይሁድ መምህር፣ በመካከላቸው ትውውቅን፣ ከአሥርት ዓመታት ወዲህ በጋራ ጉዳዮች ላይ በመወያየት፣ ወንድማማችነትን ከጊዜ ወደ ጊዜ ያሳደጉበት ጊዜ መሆኑን ብጹዕ አቡነ አምብሮጆ ገልጸው፣ ይህም በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት፣ በካቶሊክ እና በአይሁድ የሐይማኖት ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ ጥረት የተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ የችግር ዘመንን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ አምብሮጆ፣ በመንፈሳዊ ጉዞአችን ከአይሁድ እምነት ተከታዮች ጋር አንድነት እንዳላቸው አስረድተው፣ በእግዚአብሔር ሕዝቦች መካከል፣ በማሕበረ ሰባችን እና በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ብዙ የወንድማማችነት ሥራዎችን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል። በጣሊያን ውስጥ በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ የአይሁድ እና የክርስትና እምነቶችን ለማቀራረብ የሚደረጉ ጥረቶች በርካታ መሆናቸውን ያስታወቁት ብጹዕ አቡነ አምብሮጆ፣ በሮም ከተማ የሚገኝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር በአይሁድ እና በክርስትና እምነቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ከጥሊያን ወጥቶ በዓለም ደረጃም ለማሳደግ ያደረገው እና በማድረግ ላይ ያለው ጥረት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው፣ ያም ሆኖ በጣሊያን በሚገኙ ሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መካከል ያለው የእርስ በእርስ ትውውቅ፣ መተማመን እና ወዳጅነት አሁንም ማደግ ይኖርበታል ብለዋል።

የአይሁድ እምነትን ከአዲስ ኪዳን ዘመን ጋር እናዛምዳለን ያሉት ብፁዕ አቡነ አምብሮጆ፣ ይህ ግንዛቤ የተሳሳተ መሆኑን ገልጸው፣ በሌላ ወገን ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት የሚያስታውስ ክርስቲያን በአይሁዳዊያን ወንድሞቹ እና እህቶቹ ላይ የደረሰውን ስቃይ ሲዘክር ይኖራል ብለዋል። ብፁዕ አቡነ አምብሮጆ ከዚህም ጋራ በማያያዝ የአይሁድ እምነት በአውሮፓም ሆነ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ከዚህ በፊትም፣ ዛሬም፣ ወደፊትም አብሮን በኢጣሊያ፣ በፈረንሳይ እና በሌሎችም የአውሮፓ አገሮች የሚኖር መሆኑን አስረድተው ይህ በራሱ በመካከላችን ያለውን ግንኙነት የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

በመካከላችን ያለውን ወዳጅነት ማሳደግ ይኖርብናል፣

በመካከላችን ያለው ልዩነት ክፍፍልን የሚፈጥር እና ወዳጅነትን የሚቀንስ ከሆነ ለማሕበረሰባችን እና ለዓለም በሙሉ አይበጅም ያሉት፣ በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የክርስቲያኖች አንድነት እና የጋራ ውይይት ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ አምብሮጆ ስፕሪያፊኮ፣ በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መካከል ልዩነት ቢኖርም በልዩነቱ መካከል አንድ የሚያደርጉን መንፈሳዊ፣ ሥነ መለኮታዊ እና ባሕላዊ እሴቶች በመኖራቸው የጋራ ሃብት ባለቤቶች እንሆናለን ብለዋል። በመሆኑም እያንዳንዱ ወገን የራሱን እሴቶች ለሌላው ይፋ በማድረግ፣ ለመቀራረብ የሚረዳ እገዛን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በጣሊያን የጀኖቫ ከተማ የአይሁድ ማሕበረ ሰብ አስተባባሪ የሆኑት፣ መምህር ዶ/ር ጁሰፔ ሞሚሊያኖ በበኩላቸው በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ፣ ማሕልየ መሓልይ የሁለቱን ፍቅረኛሞች ታሪክ ይተርክልናል ብለው፣ ይህም ጠቅላላውን የሰው ልጅ ሁኔታ የሚያመላክት መሆኑን አስረድተዋል። በብሉይ ኪዳን፣ በማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጠው የፍቅር እና የወዳጅነት ፍለጋ እንደ አይሁድ እምነት መሠረት ጊዜውን ጠብቆ በየደረጃው የሚከናወን መሆኑን ገልጸው፣ በሁለቱ ፍቅረኛሞች መካከል ሳያቋርጥ የሚደረገው የፍቅር ፍለጋ በእግዚአብሔር እና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ያለውን የማያቋርጥ ግንኙነት የሚያመለክት መሆኑን መምህር ዶ/ር ጁሰፔ ሞሚሊያኖ  አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

16 January 2020, 17:35