ፈልግ

ክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ ክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ  

ክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ በአውሮፓ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ካቶሊካውያን ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ።

ክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ በአውሮፓ አህጉር ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ካቶሊካውያን ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ሆነው በታህሳስ 28/2012 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ተሹመዋል። ክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ በሆላንድ የሐርለም አገረ ስብከት ካህን መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ውስጥ በተለያዩ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በኃላፊነት ደረጃ እያገለገሉ እንደ ሚገኙ ይታወቃል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ እ.አ.አ በታኅሳስ 24/1967 ዓ.ም በኢትዮጲያ መወለዳቸው የሚታወቅ ሲሆን በሆላንድ የፍልስፍና እና የነገረ መለኮት ትምህርታቸውን በሚገባ ካጠናቀቁ በኋላ እ.አ.አ. በ1998 ዓ.ም በሆላንድ በሐርለም አገረ ስብከት ማዕረገ ክህነት ተቀብለው፣ በሆላንድ ሄደም በመባል በሚታወቀው ስፍራ በሚገኘው የቅዱስ ኒኮላስ ቤተክርስቲያን ቆመስ ሁነው አገልግለዋል። በቁምስና ውስጥ እንዲያከናውኑ ከተሰጣቸው ኃላፊነት ባሻገር፣ በአውሮፓ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አገራት ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጲያዊያን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ሐዋርያዊ አገልግሎት ይሰጡ እንደ ነበረ ከታሪካቸው ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በሆላንድ በሚገኘው ሐርለም አገረ ስብከት እና በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ አገረ ስብከት መካከል በተደርገ ስምምነት መሰረት በአሁኑ ወቅት ክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ በአዲስ አበባ አገረ ስብከት ስር በሚተዳደረው ሐዋርያዊ ጽህፈት ቤት ውስጥ ዋና ጸሐፊ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።   

ክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ አንዳንድ የሳይንሳዊ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎ ያደረጉ ካህን ሲሆኑ በርካታ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ተሳትፈዋል። በኢትዮጲያ የክርስትና እምነት ታሪክ ውስጥ ያለውን የገዳም ሕይወት ሥርዓት፣ ቅዱሳን ምስሎችን በተመለከተ ሀሳብን እና የአኗኗር ዘይቤን የሚወክል የስነጥበብ ውጤት የሆኑ ጹሑፎችን፣ የኢትዮጲያ መንፈሳዊ ሕይወት እና ዝማሬን የተመለከቱ ጹሑፎችን ለንባብ አብቅተዋል። ክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ባሻጋር ሆላንድኛ፣ ጣሊያነኛ እና የእንግሊዘኛ ቋንቋ አቀልጥፈው እንደ ሚናጉር ተያይዞ ከደርሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

08 January 2020, 16:20