ፈልግ

ወላጅ ቤተሰብ ከሕጻን ልጆቻቸው ጋር፤ ወላጅ ቤተሰብ ከሕጻን ልጆቻቸው ጋር፤ 

“ቤተሰባችን” ፣ ቤተሰብ የልጆቻቸውን ሥነ ምግባር በማነጽ ተግባር፤

ወላጆች በልጆቻቸው መልካም አስተዳደግ ትልቅ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ከወላጅ ቤተሰብ ቀጥሎ ወንድም፣ እህት፣ ጓደኛ እና መምህራን የአዳጊ ልጆችን እና የወጣቶችን መልካም አስተዳደግ በማገዝ የማይናቅ ሚና ይጫወታሉ። እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች በአካባቢያቸው ከሚያገኟቸው ወጣት እና አዳጊ ልጆች ጋር ባላቸው የዕለተ ዕለት ግንኙነት፣ አስተዳደጋቸው፣ ባሕርያቸው እና አመለካከታቸው ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲኖረው በማድረግ ትልቅ እገዛን ያበረክታሉ። ከላይ የጠቀስናቸው የማሕበረሰብ ክፍሎች መልካም ስነ ምግባራቸውን እና የሕይወት ልምዳቸውን ለወጣቶች እና ለአዳጊ ልጆች በማካፈል ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም በወጣቶች መካከል በራስ የመተማመን ስሜትን ማሳደግ ይችላሉ።       

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ” ብለው ባስተላለፉት የድሕረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክራቸው፣ ቤተሰብ መልካም የሆኑ የስነ ምግባር እሴቶች የሚቀሰምበት፣ ደስታን እና ነጻነትን መለማመድ እና መጠቀም የሚጀመርበት ተቋም ነው ብለው፣ ቤተሰብ ነጻነትን በጥበብ መጠቀምን የምንማርበት፣ የሰው ልጅ እሴቶች ቀዳሚ ትምህርት ቤት ነው በማለት ያስገነዝባሉ። በመልካም ስነ ምግባር ከታነጸ ቤተሰብ የሚወልድ ልጅ ከራሱ አልፎ ለሌሎች በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑ የማሕበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሊሆን ይችላል።

የአዳጊ ልጆች ወይም የወጣቶችን ስነ ምግባር ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዱ የሚችሉ ገጠመኞች፣ ትምህርቶች እና ልማዶች ብዙ ናቸው። የወጣቶችን እና የአዳጊ ሕጻናት ስነ ምግባር ሊያስተካክሉ ወይም ሊያበላሹ ከሚችሉ መንገዶች መካከል አንዱ ማኅበራዊ መገናኛ ወይም ማኅበራዊ ሚዲያ የምንለው ነው። ኢንተርኔት ወይም ድረ ገጽ የተባለ የዘመናችን የመገናኛ እና ዕውቀት የመቅሰሚያ ቴክኖሎጂ ማህበራዊ ግንኙነታችንን በተለያየ መልኩ ማሳደግ እንድንችል ያደረገን ትልቅ የሰው ልጅ የጥበብ ውጤት ነው። በዚህ የመገናኛ መንገድ በኩል የጊዜ እና የቦታ ርቀት ሳያግደን በፍጥነት የጽሑፍ፣ የምስል እና የድምጽ መልዕክቶችን መለዋወጥ ችለናል። በዚህ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከተለያዩ ሰዎች ጋር የምናደርገው የመልዕክት ልውውጥ ሃሳባችንን፣ እምነታችንን፣ እውቀታችንን እና ባሕሎቻችንን በምስል፣ በጽሑፍ እና በድምጽ እንድንጋራ አስችሎናል።

በድረ ገጽ በኩል የምንገለገልባቸው የማሕበራዊ መገናኛ ዜደዎች፣ የተለያየ ሃሳብ፣ እውቀት፣ ዓላማ ወይም አቋም፣ ምኞት፣ እምነት፣ ባሕል እና ቋንቋ ያላቸው፣ በቁጥር እጅግ በጣም በርካታ ሰዎች የሚገናኙበት ሰፊ መድረክ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። የማህበራዊ መገናኛ ድረ-ገጾችን በብዛት የሚጠቀሙት ወይም የሚገለገሉት ወጣቶች መሆናቸውን ጥናቶች አረጋግጠዋል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መሠረት ያደረገ የማሕበራዊ መገናኛ መረብ ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ ከሚሰጡት ከፍተኛ ጥቅም ባሻገር ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉበት መንገድ መኖሩ ተረጋግጧል። ወላጆች ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ ካላደረጉላቸው እና ወጣቶችም የማሕበራዊ መገናኛ መሣሪያዎች ወይም መንገዶች በትክክል ካልተረዱ ለተለያዩ የስነ ምግባር መቃወስ ሊጋለጡ ይችላሉ። 

ነጻነት ድንቅ ነገር ቢሆንም፣ ሊባክን እና ሊጠፋ ይችላል። የግብረ ገብ ትምህርት በሐሳብ፣ በማበረታቻ፣ በተግባራዊ ልምድ፣ በቅስቀሳ፣ በሽልማት፣ በምሳሌ፣ በምክር፣ በውይይት እና ነገሮችን የምናከናውናቸውን መንገዶች ያለመታከት በማጤን ነጻነትን ከማዳበር ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህ ሁሉ በቀጥታ መልካም ነገርን ወደ ማድረግ የሚመሩንን የተረጋጉ ውስጣዊ መርሆች ለማዳበር የሚረዱ ናቸው። ጥሩነት ጽኑ ውስጣዊ የአሰራር መርሆ እና እምነት ነው። ስለዚህ ጥሩ ሕይወት ነጻነትን ይገነባል፣ ያጠነክራል፣ ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርድ የጸረ ኅብረተሰብ ዝንባሌ ባሮች እንዳንሆን ያደርገናል። ምክንያቱም ሰብዓዊ ክብር ራሱ እያንዳንዳችን ከውስጥ በመነጨ እና በተቀሰቀሰ ግላዊ መንገድ በማስተዋል እና በነጻ ምርጫ ይጠይቀናል፣ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ” ብለው ባስተላለፉት የድሕረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በኩል፣ በምዕራፍ ሰባት፣ በቁጥር 267 ላይ ምክራቸው አካፍለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
27 January 2020, 15:11