ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል። ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል።  

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2012 ዓ. ም. የብርሃነ ልደቱን በዓል መልዕክት አስተላለፉ።

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የብሔራዊ እርቀ ሠላም ኮሚሽን ሰብሳቢ፣ ነገ ታኅሳስ 28/2012 ዓ. ም. በመላው ክርስቲያኖች ዘንድ የሚከበረውን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በማስመልክት ለመላው ምዕመናን የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል. 

“በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

‘ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከልን እርሱም ከሴት ተወለደ፣ ለሕግም ታዛዥ ሆነ’(ገላ.4፡4)፡፡

ብፁዓን ጳጰሳት፤ ክቡራን ካህናት፤ገዳማውያንና/ውያት፣

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ምእመናንና ሕዝበ እግዚአብሐር፣

በኑሮ በትምህርትና በሥራ ከአገራችሁ ውጪ የምትኖሩና የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፣

በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ፤

ክቡራትና ክቡራን፣

ከሁሉ አስቀድሜ እግዚአብሔር አባታችን በምህረቱና በቸርነቱ ጠብቆ ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የ2012 ዓ.ም የልደት በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ በማለት ለመላው ምዕመናን በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ እና በራሴም ስም መልካም ምኞቴን እገልጽላችኋለሁ፡፡

ሁሉም ፍጥረት የተፈጠረው በእግዚአብሔር ነው፡፡ ሕይወትን ለፍጥረት ሁሉ በልግሥና ይሰጣል ፡፡ በተለይም የሰውን ልጅ በልዩ ክብር በአምሳሉና በአርአያው ፈጥሮት በፀጋ ሙላት ከፍጥረት ሁሉ ጋር በልዩ መስተጋብር ይኖር ዘንድ በገነት በደስታ አስቀመጠው፡፡ ሆኖም ግን የሰው ልጅ ከፀጋና ከብርሃን ሙላት ሕይወት ይልቅ የጨለማና የክፋት መንገድ ስለመረጠ ከተሰጠው የፀጋ ሕይወት ርቆ በኃጢአት ሕይወት ተንከራታች ሆኖ ኖረ፡፡ እግዚአብሔር በፍጥረቱ ተስፋ የማይቆርጥ አምላክ ስለሆነ ሰውን ወደተፈጠረለት የፀጋ ሙላት ይመልሰው ዘንድ፤ አንድ ልጁ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ይሆን ዘንድ ወሰነ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ “ቃል ሥጋ ሆነ ፀጋንና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ” (ዮሐ 1፡14)፡፡

ለዓለም ሁሉ ታላቅ ደስታን በመስጠት ስዎችን ከፍ በማድርግ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረንን መራራቅ ወደ ወዳጅነት በመለወጥ ለማይታየው አምላክ ምሳሌ በመሆን የመጀመሪያ የተወደደና የተባረከ ሆነ፤ የእግዚአብሔር የማዳንም ቀን ታየ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁልጊዜ ለኛ ለስዎች የሕይወታችን ብርሃንና መንገድ ሆኖ ዘወትር ይኖራል፡፡ የልደት ትርጉም የደስታ ዕለት ነው፣ ምክንያቱም የነፍሳችን ብርሃን ስለተወለደ ሲሆን ይህን ደስታ ደግሞ በመጀመሪያ በሜዳ ላይ ለነበሩት እረኞች መልአኩ “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና ደስ ይበላችሁ” በማለት አበስራቸው፡፡ ከዚህም በኋላ የሰማይ መላእክት መጥተው “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ስላምም በምድር ለሰውም በጉ ፈቃድ ይሁን" በማለት ዘመሩ (ሉቃ 2፡8-14)፡፡

የእግዚአብሔር ቃል የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩን ትቶ ወደ ምድር ወርዶ የጠፉትን፣ ፀጋ የጎደለባቸውን፣ የተበታተኑትን ልጆቹን ይሰበሰብ ዘንድ በኃጢአት የታሰሩትን ነፃ ያወጣ ዘንድ የመጣበትን በዓል እናከብራለን፡፡ የተወለደው ክርስቶስ የሰላም ንጉሥ፤ የሰላም አለቃ ነው፡፡ የመጣውም በምድራችን ሰላምና ፍትህን ሊያሰፍን፣ ፍቅርን ሊያኖር ነው፡፡

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ

ዛሬ በዚህች ሀገር የምንኖር ዜጎች እያሳሰበን ያለው ሰላማችን፣የአብሮነታችን፣ የመስተጋብራችን ሁኔታ ነው፡፡ በህዝቦች መካከል መተማመን እየሳሳ መጥቶ ዛሬ ዛሬ ወንድም በወንድሙ ላይ በክፉ መንፈስ በመነሳሳት እጁን ሲሰነዝር እያየን ነው፡፡ ወገኖቻችን ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ በሃይማኖታቸው ወይም በብሔር ምክንያት እየተፈናቀሉና እየተሰደዱ የሰቆቃ ኑሮ ሕይወት ይኖራሉ፡፡ ለሰው ልጅ ምድራዊ ሆነ ሰማያዊ ሕይወታቸው መሰረት በመጣል ትልቅ ቦታ ያለው የእምነት ተቋማትና የአምልኮ ቦታዎች ላይ የሚደርሰው ውድመት ያሳዝነናል፡፡

ሀገር ያለ ህዝብ፣ ህዝብም ያለ ሀገር መኖር እንደማይችል አውቀን እግዚአብሔር ባርኮና መርጦ የሰጠንን ይህቺን ቅድስት አገር ከክፋትና ከጥፋት መንገድ በመታደግ ልንሠራና ልንጠብቃት ይገባል፡፡ አዳጊ ልጆች በደስታና በተስፋ የሚያድጉባት አገር እንጂ በጭንቀትና በሰቆቃ ብሎም በስደት ሕይወታቸውን የሚገፉባት መሆን የለበትም፡፡ አሁን በገሃድ እያየን ያለነው ሁኔታ በሰከነ አእምሮ እንየው ካልን ፈጣሪንም ሰውንም የሚያሳዝኑ ድርጊቶች በመሆናቸው ፈጣረያችን እና እምነታችን ወዴት ነው? ምን ወሰደብን? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በእውነት፣ በይቅርታ፤ በዕርቅና በፍቅር ፊታችንን ወደ እውነተኛው ብርሃን ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፡፡

የተወደዳችሁ ምዕመናን

ሰላም የውስጥ እረፍት ነው፡፡ ራሳችንን ከክፉ ሥራና ከመጥፎ ነገር በመጠበቅ መልካም ነገርን እናድርግ፡፡ አንዳችን ለአንዳችን ጠላት ከመሆንና በጠላትነት ከመተያየት እርስ በርሳችን ተፋቅረንና ተሳስበን እንኑር፡፡ ያለንበት ሁኔታ አስጨናቂ መስሎ ቢታየንም ፈተናዎችን በድል የሚያሸንፍ ጌታ ስላለን ወደርሱ የፀሎት ልመናችንን ማቅረብ አንርሳ፡፡ እግዚአብሔር የተጨነቁትን ይስማልና፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተልሔም ጀግና እንደሆነ እኛም የእምነታችንና የክርስትናችን ጀግኖች ለመሆን ለሰው ሳይሆን ለእርሱ ያለንን ታማኝነት እናስቀድም፤ ሁሉም ከእርሱ በእርሱም ነውና፡፡

በዚህ በልደት በዓል ምዕመናኖቻችን በዓሉን ከችግረኞችና ከምስኪኖች እንዲሁም ከአቅመደካሞችና አስታዋሽ ከሌላቸው ጋር በመሆን ያለንን በመለገስና በማካፈል በጋራ እንድናሳልፍ አደራ ማለት እወዳለሁ፡፡ ለድሃና ለችግራኛ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነዉና።

በመጨረሻም በህመምና በአልጋ ቁራኛ ሆናችሁ በየሆስፒታሉና በየቤታችሁ የምትገኙትን እግዚአብሔር ምህረቱን፣ በየማረሚያ ቤት ላላችሁ መፈታትን፤ ላዘናችሁ መጽናናትን፤ ለተቸገራችሁ እርዳታውን፣ ከየቦታችሁና ከየቄያችሁ ለተፈናቀላችሁ መሰባሰብን እግዚአብሔር እንዲሰጥልንና የጌታችን ልደት በረከትና ትሩፋት ከሁላችሁ ጋር እንዲሆን እየተመኘሁ፤ በመቀጠልም በአገር ድንበርና ፀጥታ በማስከበር ሥራ እንዲሁም በውጭ አገራት የተሰማራችሁ የደኅንነት ኃይሎችና መላው ማህበረ ክርስቲያን እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡

ልዑል እግዚአብሔር አገራችንንና ሕዝባችንን ይባርክልን”፡፡

+ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ
ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
06 January 2020, 17:18