ፈልግ

በቫቲካን የሚገኘው የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ መቶኛ ዓመቱ የምስረታ በዓል አከበረ! በቫቲካን የሚገኘው የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ መቶኛ ዓመቱ የምስረታ በዓል አከበረ! 

በቫቲካን የሚገኘው የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ መቶኛ ዓመቱ የምስረታ በዓል አከበረ!

የክርስትና እምነት ደሴት በመባል የምትታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች ሲደርስባት የነበረውን እና በክርስትና እምነቷ ላይ ተቃቶ የነበረውን ፈተና እና አደጋ ተቋቁማ ክርስትናዋን ጠብቃ ለመቆየት የቻለችው ከሁሉም በላይ እምነቷን በእግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በሆነው በቅድስት ስላሴ ላይ ባላት ከፍተኛ እምነት የተነሳ ሲሆን በተጨማሪም የክርስትና እምነት መገለጫ እና ማዕከል በመጎብኘት እና በመሳለም፣ በእነዚህ እና እነዚህን በመሳሰሉ መንፈሳዊ ድጋፎች እና የጥንት አባቶቻችን በከፈሉት ከፍተኛ መስዋዕትነት ጭምር የክርስትና እምነቷን እስከ ዛሬ ድረስ ጠብቃ ትገኛለች።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ እና እንዲሁም ከዚያም ባሻገር ጥንታዊ የክርስትና እምነት ታሪክ ባላቸው አገራት ውስጥ ሳይቀር ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ምዕመናኖቿ መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደበት ከቤተልሔም አንስቶ፣ የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት መስዋዕትነትን በተቀበሉባቸው አገራት ውስጥ የሚገኙትን ቅዱሳን ስፍራዎችን የመጎብኘት እና የመሳለም ባሕል የነበራቸው ሕዝቦች ሲሆኑ በዚህም መሠረት በተለያየ ወቅት በክርስትና እምነት የበሰሉ፣ በመንፈሳዊ ሕይወት የበሰሉ ልጆቿ መንፈሳዊ ንግደት በሚያደርጉበት ወቅት ልዩ ልዩ ችግሮች እና ፈተናዎች ተቋቁመው የሚደርስባቸውን ፈተና በእምነት እና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አሸንፈው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደበት የቤተልሔም ከተማ አንስቶ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መካነ መቃብር የሚገኝበትን ስፍራ እንደ ሚጎበኙ እና እንደ ሚሳለሙ የሚታወቅ ሲሆን ከዚያም ባሻገር አንጋፋ የነበሩትን እና የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት አለቃ የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስ እና በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች ስብከተ ወንጌልን በማሰራጨት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ መስዋዕትነት ወደ ከፈሉባት የሮም ከተማ ንግደት በማደረግ የሁለቱን ቅዱሳና ሐዋርያት መካነ መቃብር ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ይሳለሙ እንደ ነበር ከታሪክ ለመረዳት ይቻላል።

በእዚህም መሠረት ከመካከለኛው ዘመን አንስቶ ከኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ነጋዲያን የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ መካነ መቃብር ለመሳለም ወደ ሮም ንግደት ያደርጉ የነበረ ሲሆን በወቅቱ የነጋድያኑ የወል ስም ሐበሻ ወይም ኢትዮጵያዊያን በመባል ይጠሩ እንደ ነበር ከታሪክ ድርሳናት ለመረዳት የተቻለ ሲሆን እ.አ.አ በ1404 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሮም ሲመጡ ይታዩ እንደ ነበረ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል።

የኢትዮጵያዊያን ቡድን መልእክት ሱታፌ በፍሎሬንስ ጉባሄ (እ.አ.አ 02/09/1441 ዓ.ም)

በ15ኛው ክፈለ ዘመን የነበሩት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን 207ኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ኤውጀንዮ 4ኛ ዘመን እ.አ.አ. በ1441 ዓ.ም በፍሎረንስ ከተማ ታላቁ የፍሎረንስ ጉባኤ ይካሄድ ነበር። በወቅቱ ጉባኤው ትኩረቱን አድርጎ የተወያየው ስለክርስቲያኖች አንድነት እንደ ነበረ ከታሪክ ለመረዳት የሚቻል ሲሆን በጉባኤው ላይ በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተማህዶ ቤተክርስቲያን መነኩሳት አባ ኒቆዲሞስ በመባል በሚታወቁ አበምኔት የተላከ አንድ ቡድን ወደ ፍሎረንስ በመምጣት በጉባኤው ላይ በታዛቢነት ተሳትፏል። የታሪክ አዋቂው የሲታዊያን ማኅበር መነኩሴ የሆኑት ክቡር አባ ብሩክ ወልደጋብር በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ እንደ ገለጹት “ የቡድኑ መሪ ስለ አገራቸው ኢትዮጲያ ታሪክና የሃይማኖት ገድል ለጉባሄው ተሳታፊዎች ደስ በሚል መልኩ ንግግር ማደረጋቸው በላቲን ቋንቋ ተመዝግቦ እንደ ሚገኝ” የገለጹ ሲሆን ተወካዮቹ ወደ መጡበት ወደ ኢየሩሳሌም ከመመለሳቸው በፊት የሮም ከተማን መጎብኘታቸውን፣ የሮም ቤተክርስቲያን መሪዎች እና የመንግሥት መኳንንት ሕዝቡም ጭምር ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉላቸው፣ ለአቀባበሉም መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን በመካከለኛው ትልቁ የብረት በር ላይ የመልእክተኞቹ ንግደት ሥዕል ተቀርጾ እንደ ሚገኝ፣ ይህም ሊሰረዝ የማይችል መታሰቢያ እንደ ሆነ አባ ብሩክ ጨምረው ገለጸዋል።

በቫቲካን ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን

በቫቲካን ውስጥ ከሚገኘው ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ጀርባ የሚገኝ በአምስተኛው ክፍለ ዘመን እ.አ.አ በ440-461 ዓ. ም. መካከል 45ኛው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት ሊዮን ቀዳማዊ የተገነባ ቤተክርስቲያን፣ የመጀመሪያው ሰማዕት በመባል የሚታወቀው የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ይገኛል። ቀደም ሲል እንደ ገለጽነው ኢትዮጵያዊያን መንፈሳዊ ነጋዲያን በቫቲካን የሚገኘውን የቅዱስ ጴጥሮስ እና እንዲሁም በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የቅዱስ ጳውሎስ መካነ መቃብር ለመሳለም ወደ ሮም ከተማ ይመጡ እንደ ነበረ ከታሪክ ድርሳናት ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በሃያኛው ክፍለ ዘመን የኖሩ የካፑቺን ማኅበር መነኩሴ እና ታዋቂ የታሪክ ተመራማሪ የነበሩ አባ ማውሮ ዳ ልዮንሳ እ.አ.አ በ1929 ዓ.ም ይፋ ባደረጉት የጥናት ምርምር ስራቸው እንደ ገለጹት ይህ በቫቲካን ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን 212ኛው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት በስክስቱስ 4ኛ አማካይነት ለኢትዮጵያዊያን ነጋዲያን እ.አ.አ. በ1481 ዓ.ም እንደ ተሰጠ በጥናታቸው ይፋ አድርገዋል።    

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ስክስቱስ 4ኛ (የርዕሰ ጵጵስና ዘመናቸው 1471-1484) ከኢትዮጵያዊያኑ መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር በቫቲካን የተገናኙት እ.አ.አ በ1481 ዓ.ም እንደ ነበረ የታሪክ አዋቂው ክቡር አባ ብሩክ ወልደጋብር በጥናታቸው ያረጋገጡ ሲሆን በወቅቱ ብዙ ኢትዮጵያዊያን መንፈሳዊ ነጋዲያን የቅዱስ ጴጥሮስን መካነ መቃብር ለመሳለም ወደ ቫቲካን በብዛት የሚመጡበት ወቅት በመሆኑ የተነሳ እኝሁ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስክስቱስ 4ኛ የቅዱስ እስጢፋኖስን ቤተክርስቲያን ለኢትዮጵያዊያኑ መንፈሳዊ ነጋዲያን እንዲሰጥ ትዕዛዝ እንዳስተላለፉ እና ከእዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተክርስቲያኑ “የሐበሾች ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን” በመባል መጠራት እንደ ጀመረ ክቡር አባ ብሩክ በጥናታቸው ይፋ አድርገዋል። ከዚህ “የሐበሾች ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን” ጎን ለኢትዮጵያዊያኑ ነጋዲያን የሚሆን ማረፊያ ቤት እ.አ.አ በ1483 ዓ.ም መገንባቱን ጨምረው የገለጹት የታሪክ አዋቂው ክቡር አባ ብሩክ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሲስቶ ክስቱስ ይህንን መልካም የሚባል ተግባር ለኢትዮጵያዊያኑ ነጋዲያን በስጦታ ካበረከቱ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ እ.አ.አ በነሐሴ 12/1484 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት እንደ ተለዩ ታሪክ ያስረዳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስክስቱስ 4ኛ ይህንን ታላቅ ስጦታ ለኢትዮጵያዊያኑ ነጋዲያን ያበረከቱት ኢትዮጵያዊያኑ ለክርስትና እምነታቸው ያላቸውን ታማኝነት እና ጥማት በማድነቅና ለክርስናቸው ዋጋ የሚሰጡ በመሆናቸው ለማበረታታትና ብሎም ኢትዮጵያውያኑ ከሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የጠነከረ ግንኙነት እንዲኖራቸው በማሰብ ያደረጉት ነው። ኢትዮጵያዊያኑም ቢሆኑ ለክርስትና እምነታቸው እድገት ያደርጉት የነበረውን ጥረት ሁሉ እግዚአብሔር ሳይደሰትባቸው አይቀርም፣ ለዚህም ይመስላል የወንድሞቻቸውን የኢትዮጵያዊያን ቅን አገልግሎት እና መሻት ለማበረታታት በማሰብ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስክስቱስ 4ኛ እና ከሳቸውም በኋላ የመንበረ ጴጥሮስ ተተኪ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳትን መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶ ለኢትዮጵያዊያን ይህንን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ፀጋ ለማበርከት የቻሉት በእዚሁ ምክንያት ነው። ልዩ የሚያደርገው ደግሞ የሐዋርያት አለቆችና የክርስትና እምነት አምዶች የነበሩትን የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስን መካነ መቃብሮች ለመሳለም ወደ ቫቲካን እና ሮም ከተማ ይጎርፉ የነበሩት መነኮሳት ሊቃውንት እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ኢትዮጵያዊያን ብቻ እንዳልነበሩ ይታወቃል፣ ነገር ግን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ስጦታ ለመቀበል የቻሉት አባቶቻችን በነበራቸው ጠንካራ የክርስትና እምነት የተነሳ ነው፤ ይህም ድንቅ የሆነ ተገባር ነው።

ቀደም ሲል በገለጽነው መሠረት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስክስቱስ 4ኛ ለኢትዮጵያዊያን ነጋዲያን የሚሆን የእንግዳ ማረፊያ ቤት እንዲሰራ ባዘዙት መሠረት ትዕዛዛቸው ተፈጽሞ የእንግዳ ማረፊያ ቤቱ አግልግሎት መስጠት እንደ ጀመረ መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን እንግዳ ቤቱ ኢትዮጵያዊያን ነጋዲያን ወደ ሮም ከተማ በሚመጡበት ወቅት እንዲያርፉበት ታስቦ የተገነባ ነው። በዚህም መሠረት የእንግዳ ማረፊያ ቤቱ እንግዶቹ ለተወሰነ ጊዜ በእንግድነት የሚኖሩበት ቤት እንዲሆን ታስቦ የተሠራ ቢሆንም ቅሉ ነገር ግን የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መንፈሳዊ ነጋዲያንን ተቀብለው በሚገባ የሚያስተናግዱ መሆናቸውን ነጋዲያኑ በመረዳታቸው የተነሳ ቀስ በቀስ የነጋዲያኑ ቁጥር እየጨመረ መጣ፣ ለአጭር ጊዜ ብቻ ሳይሆን ረዘም ላሉ ጊዜያት በዚያው ስፍራ መቆየት ጀመሩ፤ ከዚያም የእንግዳ ማረፊያ ቤቱ የመነኩሳቱ ማረፊያ ገዳም ለመሆን በቅቷል።

በቫቲካን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሌጅ አመሰራረት በአጭሩ፤

በቫቲካን ውስጥ የሚገኘው ብቸኛው የኢትዮጵያ ኮሌጅ ምሥረታ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጾ ካደረጉት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን 258ኛው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት በነዲክት 15ኛ እና 259ኛው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ፒዮስ 11ኛ እንደ ሆኑ ከታሪክ ለመረዳት ተችሏል። ለኢትዮጵያዊያን ነጋዲያን ማረፊያ ተብሎ የተሰጠው ይህ የቅዱስ እስጢፋኖስ የእንግዳ ማረፊያ ቤት ቀስ በቀስ ተራ የእንግዳ ማረፊያ ቦታ መሆኑ ቀርቶ የኢትዮጵያ ምርጥ ተማሪዎች በእውቀትና በመንፈሳዊ ሕይወት እየታነጹ የሚያድጉበት የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ማረፊያ ገዳም ወደ መሆን ተሸጋገረ። በ1919 ዓ. ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ስምንት የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ከአለቆቻቸው እና ከመንፈሳዊ አባታቸው ጋር በቋሚነት በዚያው መኖር ጀመሩ። እንደ አለመታደል ሆኖ ቦታው የሌላ አገር ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ከለመዱት የአየር ንብረት አኳያ ሲታይ ቀዛቃዛ የሆነ የአየር ንብረት የሚገኝበት ሥፍራ በመሆኑ የተነሳ ከሌላ አገር የአየር ንብረት ጠባይ ጋር ተለማምደው ለመጡት ወጣት ተማሪዎች በጣም ቀዝቃዛ ስለሆነባቸው አንዳንዶቹ ሞቱ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ አገራቸው ተመለሱ።

ከጊዜ በኋላ ደግሞ እ.አ.አ በ1919 ዓ.ም እነሆ ዘንድሮ (እ.አ.አ 2020) መቶኛ ዓመት የምስረታ በዓል የሚከበርለት ይህ የኢትዮጵያ ኮሌጅ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያና ከኤርትራ፣ ከፍተኛ የነገረ መለኮት ትምህርት ለመማር የሚመጡ ካህናት እና በእንግድነት ከሁለቱም አገራት ለሚመጡ ጳጳሳት ማረፊያ ሆኖ እንዲያገለግል በማሰብ አሁን ያለውን ትልቅ ሕንጻ እንዲገነባ ያደረጉትን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 15ኛ እና ፒዮስ 11ኛ ናቸው። የሁለቱም ምስል በኮሌጁ መግቢያ ላይ ቆሞ እናገኛለን። እ.አ.አ በ1930 ዓ.ም ይህ አሁን ያለው ዘመናዊ ሕንጻ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ የሚታወቅ ሲሆን በቫቲካን የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ የሚል መጠሪያ ስም ተሰጠው። በዚህም የተነሳ የእንግዳ ማረፊያ መሆኑን ቀርቶ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት የሚማሩ ካህናት የሚኖሩበት መኖሪያ ሆኖ ተሰየመ።

11 January 2020, 18:36