ፈልግ

የምድራዊ ነገር ከንቱነት የምድራዊ ነገር ከንቱነት 

የምድራዊ ነገር ከንቱነት

“ወንድሞቼ ሆይ ዓለምንና በእርሱ የሚገኘውን አታላይ ነገር አትውደዱ፣ ምክንያቱም ደስታውና ምቾት ፍትወቱ ሁሉ አላፊ ነው” (1ኛ. ዮሐ. 2፣15   )። ንጉሥ ሰለሞን በጣም ሀብታም፣ አዋቂና ትልቅ ሰው ነበረ፤ በልቡ የተመኘውን ነገር ሁሉ አግኝቶ ነበር፡፡  “ትልልቅ ነገሮች አደረግሁ፣ ሁሉ በእጄ ነበረ፣ በልቤ የፈለግሁትንም አልከለከለኝም” እያለ ይናገራል፡፡ ነገር ግን ቀጥሎ እነዚህ ነገሮች በተመለከተ በውስጡ ምን እንደተሰማው ሲገልጽ ሕይወት አስጠላኝ፣ ጊዜያዊ እርባናቢስ ጥረቴ አስጠላኝ፣ የሁሉን ነገር ከንቱነት ሲያስብ “ሁሉም የከንቱ ከንቱ ነው” (መክ. 1-2) እያለ በጊዜያዊ ነገር ተማርሮ ይናገራል፡፡ ይህ ዓለም ምድራዊውን ነገር እንድንጠቀም አለመጠን ይስበናል፡፡ መንፈሳውያን መሆናችንን ረስተን ምድርን ብቻ እንድንመለከት ያሳስበናል፣ እንስሶች ያስመስለናል፣ የሰማይን ሐሳብ ከልባችን ያርቅብናል፡፡

ይህ የተበላሸ ሥጋዊ ባሕርያችን የምድርን ነገር ተከትለን እንድንሄድ ያደርገናል፡፡ በሥጋችን ተስበን የሕይወትን ምቾት እንፈልጋለን፡፡ በሕይወታችን ተመችቶን ከብረን እንድንኖር እንመኛለን፡፡ ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ደግሞ በመላ ኃይላችንና ዕውቀታችን ሌሊትም ቀንም ደከመን ሰለቸን ሳንል ለሥጋዊ ነገር እንሠራለን፡፡ ግን ልብ ብለን ብናስተውል ሁሉ ምድራዊ ነገር አላፊና ጠፊ እንደሆነ እንረዳለን፣ በደንብ እንገነዘባለን፡፡ እንደ ሰሎሞን “ሁሉ ከንቱ ነው” እያልን እንናገራለን፣ የምድርን ነገር ከብዙ ጥረት ካገኘነው በኋላ እንደምናስበው ከመደሰት ይልቅ ውስጣዊ ሰላማችንን ይነሣናል፣ ልባችን በምኞት ብቻ ይቀራል፡፡ መጀመሪያ አበባ፣ ብርሃን መልካም፣ ጣፋጭ ይመስለን የነበረ ነገር ከጨበጥነው በኋላ ጨለማ፣ የማይረባ፣ መጥፎ ሆኖ ይታያል፡፡ እንደዚህ እንደሆነ እያወቅን ምንም ተስፋ አንቆርጥም፣ የዓለም ነገር ጥማታችን አያረካም፡፡

“ወንድሞቼ ሆይ ዓለምንና በእርሱ ያለውን አትውደዱ ምክንያቱም አላፊ ነው፣ እርሱ እርግጥ ምድራዊ ነገር ሀብት ክብር ዕውቀት ጥበብ የሕይወት ምቾት” እግዚአብሔር ለኑሮአችን ለሕይወታችን ብሎ የፈጠረውን ጥሩና አስፈላጊም ነው፡፡ ስለዚህ በመጠን እንድንፈልገውና እንድንጠቀምበት ይገባል፡፡ ነገር ግን አብዝተን ወደ እነርሱ እናዘንብል፣ እነርሱን ተከትለን እቡያን እንሁን፡፡ ለእርሱ ስንል ሰማያዊውን ነገር አንርሳ፣ አናጥፋ፣ አላፊና ከንቱ እንደሆነ እናስታውስ፡፡ ስለዚህ በመጠን እንፈልገው፡፡ በመጀመሪያ መንፈሳዊውን በኋላ ግን ምድራዊውን ነገር እንፈልግ፡፡

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

23 December 2019, 13:31