ፈልግ

“ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ” “ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ”  

ኢየሱስ እርሱ የሕይወታችን ንጉሥ ይሆን ዘንድ እንድንፈቅድለት ልባችንን እያንኳኳ ይገኛል!

በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጪው ኅዳር 28/2012 ዓ.ም “ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ” አመታዊ በዓለ እንደ ሚከበር ይታወቃል። ይህንን በዓል አስመልክተን ያዘጋጀንላችሁን አጠር ያለ አስተንትኖ እንደ ሚከተለው አሰናድተናል፣ ተከታተሉን።

ጲላጦስም ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን አስጠራና፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ይህ ሐሳብ የራስህ ነው? ወይስ ሌሎች ስለ እኔ የነገሩህ?” ሲል መለሰለት። ጲላጦስም መልሶ፣ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወደ እኔ የላኩህ የራስህ ወገኖችና የካህናት አለቆች ናቸው፤ ለመሆኑ ምን አድርገህ ነው?” አለው። ኢየሱስም፣ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ ሎሌዎቼ በተከላከሉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም” አለው። ጲላጦስም፣ “ታዲያ፣ ንጉሥ ነህ ማለት ነዋ!” አለው (ዮሐንስ 18፡33-37)።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

 

 

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ

ሕዳር 28/2012 ዓ.ም ላይ በዓመቱ የስርዓተ አምልኮ ማብቂያ ላይ የምናከብረው “ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ” ዓመታዊ በዓል የፍጥረታት ሕይወት እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነገር እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ወደ አንድ መጨረሻ ግብ የሚያመራ፡ የታሪኮች እና የፍጥረታት ሁሉ ጌታ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ የመጨረሻ ግልጸት እንደ ሚያመራ የሚያሳይ ነው። የታሪኩ መደምደሚያ ዘለዓለማዊ መንግሥቱ ይሆናል ማለት ነው። በዮሐንስ 18፡33-37 ላይ ስለ ክርስቶስ መንግሥት፣ ስለ ኢየሱስ መንግሥት፣ ኢየሱስ በጌተሰማኒ ከታሰረ በኋላ ስለደረሰበት ውርደት ሁኔታ በመጥቀስ ያሳለፈውን ታሪክ ያመለክታል፡ "ታስሯል፣ ተሰድቡዋል፣ ተከሱዋል በኢየሩሳሌም ባለሥልጣናት ፊት ቀርቦአል"። ከዚያም በኋላ ፖለቲካዊ ለሆነ ሥልጣን እና የአይሁድ ንጉሥ ለመሆን እንደ ሚፈልግ ተደርጎ በሮም አቃቤ ሕግ ፊት እንዲቆም ይደረጋል። ጲላጦስ ጥያቄውን በማቅረብ አስገራሚ የሆነ ምርመራ ማድረግ በጀመረበት ወቅት እርሱ ንጉሥ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ሁለት ጊዜ ይጠይቀዋል (ዮሐ 18፡33,37)።

ኢየሱስም በቅድሚያ “የእኔ ምንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም” በማለት ይመልሳል። ከዚያን በኋላ ደግሞ “አንተ እንዳልከው ነኝ” በማለት ያረጋግጣል። ይህም ኢየሱስ በመላው ሕይወቱ ፖለቲካዊ ለሆነ ስልጣን ምንም ዓይነት ፍላጎት እንዳልነበረው ያሳያል።

ኢየሱስ በአምስት እንጀራ እና በሁለት ዓሳ ብቻ 5ሺ የሚሆኑ ሰዎችን ከመገበ በኃላ በዚህ ተዓምር እጅግ በጣም ተደንቀው የነበሩ ሰዎች የሮማን መንግሥት ገርስሶ የእስራኤል መንግሥት እንዲገነባ ፈልገው እርሱን ልያነግሱት ፈልገው እንደ ነበረ እናስታውሳለን። ነገር ግን ለኢየሱስ መንግሥት ማለት ርዕዮት፣ ብጥብጥ እና መሳሪያ የታጠቀ ኃይል ማለት አይደለም። 5ሺ ሰዎችን በአምስት እንጀራ እና በሁለት ዓሳ ከመገበ በኋላ ሕዝቡ ልያነግሡት በፈለጉ ወቅት እነርሱን ትቶ ወደ ተራራ የወጣው በዚሁ ምክንያት ነው (ዮሐ 6፡5-15)። አሁን ለጲላጦስ መልስ ሲሰጥ ደቀ መዛሙርቱ እሱን ለመከላከል አልተዋጉም ነበር። መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” (ዮሐ. 18፡36) በማለት የመለሰውም በዚሁ ምክንያት ነው። ኢየሱስ ከፖለቲካው ኃይል በላይ እጅግ የላቀ የሆነ፣ በሰው ልጆች አማካይነት ሥልጣን ላይ ያልተቀመጠ መሆኑን ግልፅ ማድረግ ይፈልጋል። እርሱ ወደ ምድር የመጣው ኃይል ተጠቅሞ ዓለምን ለመግዛት ሳይሆን በፍቅር ስለእውነት ለመመስከር ነው። ይህም የቅዱስ ወንጌል ዋና መልእክት የሆነው “እግዚኣብሔር ፍቅር ነው” የሚለው መለኮታዊ እውነት ሲሆን እርሱ በዓለም ውስጥ የእርሱን የፍቅር፣ የፍትህ እና የሰለም መንግሥት ለመመስረት ነው የመጣው። እናም ይህ ኢየሱስ የነገሠበት እና እስከ መጨረሻው ዘመን የሚዘልቅ ነው። ከታሪክ እንደ ምንማረው በጦር መሳሪያ እና በምድራዊ ስልጣን ላይ  መሰርቱን በማድረግ የተገነባ መንግሥት በመጀመሪያ በቀላሉ ይበታተናሉ ቀጥሎም ብዙ ሳይቆይ ተዳክመው የፈራርሳሉ። ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት በፍቅር ላይ የተመሰረተ እና በልባችን ውስጥ ሥር መሰረት ያለው ነው፡ የእግዚኣብሔር መንግሥት በልባችን ውስጥ ሥሩን ይዘረጋል-ይህንን የሚቀበል ሰው ደግሞ ሰላምን ያገኛል፣ ነጻነትን ይጎናጸፋል ምልኣት ያለው ሕይወት ይኖራል። ሁላችንም ሰላምን እንፈልጋለን፣ ሁላችንም ነጻነት እንፈልጋለን፣ ሁላችንም ምልኣት ያለው ሕይወት እንፈልጋለን። ታዲያ ይህንን እንዴት ማግኘት እንችላለን? የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንግሥት፣ የኢየሱስ ፍቅር በልባችሁ ውስጥ ሥር እንዲሰድ ብታደርጉ ሰላም ታገኛላችሁ፣ ነጻነት ይኖራችኋል እንዲሁም ደስተኛ የሆነ ሕይወት ትኖራላችሁ።

ዛሬ ኢየሱስ እርሱ የሕይወታችን ንጉሥ ይሆን ዘንድ እንድንፈቅድለት ይጠይቀናል። በቃሉ፣ በመላካም አብነቱ፣ በመስቀል ላይ ተሰውቶ እኛን ከሞት ያዳነን ይህ ንጉሳችን የደጉን ሳምራዊ መንገድ እንድንከተል በማመልከት በጥርጣሬ ለተሞላው ሕይወታችን አዲስ የሕይወት ሕልውና ብርሃን በመስጠት ከፍርሃት ነጻ ሆንን እና በእየእለቱ ከሚገጥሙን ፈተናዎች ተላቀን እንድንኖር ይረዳናል። ነገር ግን እኛ የኢየሱስ መንግሥት ከዚህ ዓለም እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ በስህተቶቻችንን እና በኃጢአቶቻችንን እንድንፈትሽ ጊዜ በመስጠት፣ የዓለምን እና የዓለም ምንግሥታት አምክንዮ  እንዳንከተል በማድረግ ህይወታችን አዲስ ትርጉም እንዲኖራት ያደርጋል።

ኢየሱስን የሕይወታችን ንጉሥ አድርገን እድንቀበል እና የእርሱ መንግሥት እንዲሰፋ ለማድረግ እውነት ለሆነው ለእርሱ ፍቅር ምስክርነት በመስጠት መኖር እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።

05 December 2019, 15:18