ፈልግ

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰደዱ ክርስቲያኖች ቁጥር ጨምሩዋል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰደዱ ክርስቲያኖች ቁጥር ጨምሩዋል 

የቅ. እስጢፋኖስ በዓል ስናከብር የሚሰደዱ ክርስቲያኖች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ማስታወስ ያስፈልጋል!

የጎርጎስሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ዘንድ ጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት የገና በዓል በደማቅ ሁኔታ በትላንትናው እለት ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከተከበረበት የገና በዓል በመቀጠል ባለው እለት የቤተ ክርስቲያን የመጀመርያው ሰማዕት የሆነው የቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ በዓል እንደ ሚከበር ይታወቃል። የእዚህ የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ሰማዕት በመባል የሚታወቀው የቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ በዓል በታኅሳስ 16/2012 ዓ.ም. በቫቲካን ተከብሮ ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል። በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ይህንን የቅዱስ እስጢፋኖስን በዓል ለማክበር ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኝዎች ባሰሙት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ “ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ ይቅርታን ማድረግ እንደ ሚገባን ያስተምረናል” ማለታቸውን ይታወሳል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

መለኮታዊ የሆነውን ጌታ ፈለግ በመከተል ሰማዕትነትን የተቀበለው የመጀመሪያው ሰው ቅዱስ እስጢፋኖስ ነበር፣ ኢየሱስ ሕይወቱን ለእግዚኣብሔር በአደራ በመስጠት ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠና አሳዳጆቹን ይቅር በማለት እንደ ሞተ ሁሉ ቅዱስ እስጢፋኖስም እንዲሁ አድርጉዋል። እስጢፋኖስን በድንጋይ ይወግሩት በነበረበት ወቅት እርሱ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል” (የሐዋ. ሥራ 7፡59) ብሎ ተናገረ። እነዚህ ቃላት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ከተናገራቸው ቃላት ጋር በጣም ተመሳሳይ ናቸው፡ ኢየሱስም በመስቀል ላይ ሳለ “አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ በአደራ ሰጣለሁ” (ሉቃ 23፡46) ብሎ ከተናገረው የኢየሱስ ቃላት ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። የኢየሱስን አካሄድ በታማኝነት የተከተለው የእስጢፋኖስ ባህሪ እያንዳንዳችን በሕይወታችን የሚከሰቱትን አዎናታዊ እና አሉታዊ የሆኑ ነገሮችን በእምነት በእግዚኣብሔር እጅ ውስጥ በአደራ ማስቀመጥ እንደ ሚገባን እና ጽኑ ሆነን መኖር እንዳለብን የሚጋብዘን ጥሪ ነው። እኛ የመኖር ሕልውና አስደሳች በሆኑ ሁኔታዎች ብቻ የተሞላ ሳይሆን፣ ነገር ግን አንዳንዴ በመከራ እና በመጥፎ ስሜት የተሞላ ሊሆንም ይችላል። ነገር ግን በእግዚአብሄር መታመን አስቸጋሪ ወቅቶችን ለመቀበል እና በእምነት ለማደግ፣ እንዲሁም ከወንድሞቻችን ጋር አዲስ ግንኙነቶችን መመስረት እንችል ዘንድ ዕድሉን ያመቻችልናል። ይህም ማለት ደግሞ በእግዚኣብሔር እቅፍ ውስጥ ራሳችንን በማስገባት እርሱ በመልካም ነገሮች የተሞላ ባለጸጋ አባት መሆኑን እና ለልጆቹ የምያስብ አባት መሆኑን ማወቅ ማለት ነው።

የመጀመሪያው ሰማዕት በመባል የሚታወቀው የቅዱስ እስጢፋኖስን ዓመታዊ በዓል ስናከብር በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ የሚገኘው ስደት እና ወከባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ማሰብ ይገባናል።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን የሚረዳው የካቶሊክ ቤተክርስትያን የእርዳታ መስጫ ተቋም በቅርቡ ባወጣው አመታዊ ሪፖርት እንደ ገለጸው በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2019 ዓ.ም በዓለማችን ዙሪያ በሚገኙ በ20 አገራት ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች ለከፍተኛ ስደት መዳረጋቸውን ድርጅቱ ይፋ ካደረገው ሪፖርት ለመረዳት ተችሉዋል። ድርጅቱ በጥቅምት 13/2012 ዓ.ም ባወጣው አመታዊ ሪፖርት ጨምሮ እንደ ገለጸው በክርስቲያኖች ላይ ስልታዊ የሆኑ ጥቃቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን የገለጸ ሲሆን ይህ ጥቃት በአፍሪካ እና በደቡብ እስያ አገርት ሁኔታው እየተባባሰ መሄዱን ጨምሮ ገልጹዋል።

 “አሁን የምንገኝበት ሁኔታ እና የምንኖረው ሕይወት ዘላቂ በሆነ ውጥረት የተሞላ ነው፣ ምክንያቱም ማን ይሁን የት እና መቼ እንደሆነ ማንም ባያውቀውም፣ በሆነ ቦታ እና ሥፍራ ላይ አንድ ቀን ጥቃት እንደ ሚፈጸም ግን አዕምሮዋችን ያውቃል” በማለት በፓኪስታን የካራቺ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ካርዲናል ጆሴፍ ኩትስ የሁኔታውን አሳሳቢነት እና በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመውን ከፍተኛ ሽብር፣ ጥቃት እና ሰደት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያንትን ለሚረዳው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የእርዳታ መስጫ ተቋም የገለጹ ሲሆን ድርጅቱ ባወጣው አመታዊ ሪፖርት እንደ ገለጸው በአሁኑ ወቅት ከ300 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ክርስቲያኖች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለከፍተኛ ስደት እና እንግልት መዳረጋቸውን ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጸዋል።

በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ስረዓት ላይ መሳተፍ፣ የክርስቲያን ማህበረሰብን መንፈሳዊ ሕይወት የሚያነቃቁ ሐዋርያዊ የሆኑ ትምሕርቶችን እና እንቅስቃሴዎችን ማደረግ እና ማስተዋወቅ፣ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን ምልክቶችን መጠቀም ወይም በቀላሉ እምነትን የሚገልጹ ተግባራትን ማከናወን፣ ሐይማኖትን በነጻነት መግለጽ 20 በሚሆኑ የዓለማችን አገራት ውስጥ እነዚህን ተግባራት በነጻነት የመግለጽ መብት እየታገደ እና እየታፈነ መምጣቱን የገለጸው ሪፖርቱ በእዚህ የተነሳ የክርስቲያኖችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ጨምሮ ገልጹዋል።

“በሃይማኖታቸው ምክንያት በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ስደት ብዙ ገጽታዎች ሊኖሩት ይችላሉ” በማለት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን ለሚረዳው የካቶሊክ ቤተክርስትያን የእርዳታ መስጫ ተቋም የገለጹት በፓኪስታን የካራቺ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ካርዲናል ጆሴፍ ኩትስ፣ በኢራቅና በሶሪያ በሚገኙ ክርስቲያኖች እና ዛይዲ በመባል በሚታወቁ ማኅበረሰቦች ላይ እስላማዊ መንግስት እመሰርታለሁ የሚለው አይሲስ በመባል የሚታወቀው አሸባሪ ድርጅት በጭካኔ የተሞላ ጥቃት መፈጸሙ የሚታወስ ሲሆን ከእዚህ በቀጥታ ከሚከናወኑት ጥቃቶች ባሻገር በተቀነባበረ መልኩ መድልዎ፣ በቃላት የሚፈጸሙ የሽብር ተግባራት፣ ዝርፊያ፣ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ ጠለፋ እና በግዳጅ እምነታቸውን እንዲቀይሩ በሚደረጉ ተግባራት ምክንያት ክርስቲያኖች መብታቸውን እየተገፈፉ ወይም መብታቸው እየተገደበ መምጣቱን ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጹዋል።

በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ምክንያቶች ስደት እና መከራ የሚደርስባቸውን ክርስቲያኖች በመርዳት የሚታወቀው የካቶሊክ የእርዳታ መስጫ ተቋም በመላው ዓለም በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ስደት እና መከራ በሚፈጸምባቸው 140 ሀገራት ውስጥ በመንቀሳቀስ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደርገ የሚገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እርዳታ ሰጪ ድርጅት እንደ ሆነ የሚታወቅ ሲሆን ይህንን እርዳታ የሚያደርገው ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ብቻ ሳይሆን ለመላው የክርስቲያን ማኅበረሰብ እንደ ሆነም ተያይዞ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

26 December 2019, 11:54