ፈልግ

“በኢየሱስ ብፁዓን፤ በዓለም ብፁዓን” (ማቴ. 5፣3-12)

መንፈሳዊ ማሳሰቢያ ታኅሳስ 09/2012 ዓ.ም

የኢየሱስ አስተሳሰብና የዓለም አስተሳሰብ እጅግ በጣም የተለያየ ነው። ብፅዕናን በተመለከተ ኢየሱስ ያለው አስተሳሰብ እና አተያይ እጅግ የተለያየ ነው። ለምሳሌ ኢየሱስ መንፈሳዊ የሆኑ ብፁዕ ሊያሰኙ የሚችሉትን ተግባራት በተመለከተ ሲናገር በአንጻሩ ደግሞ ዓለም ምድራዊ ብፁዕነት ያስባል። ኢየሱስ ብፁዓን የሚላቸው የዓለም ምስክሮች ናቸው፡፡ ዓለም ብፁዓን ብሎ የሚያደንቃቸው ሐብታሞችን፣ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን፣ በስኬት ጎዳና ላይ የሚራመዱ ሰዎችን ሲሆን፣  ኢየሱስ ብፁዓን የሚላቸው ደግሞ ከእዚህ በተቃራኒ ጎራ የሚገኙትን በመንፈስ ድሆች፣ የዓለም ሀብት ንቀው ደሃ መስለው የሚኖሩ ወይም የመነኑ፣ የሰማይን ሕይወት የሚፈልጉ ወዘተ… ሰዎችን ነው።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ዓለም ብፁዓን የሚላቸው ግን ሀብት የናቁትን አይደለም፡፡ ሐብት የሚስባቸውና የሚወዱትን ሰዎች ነው እንጂ። ኢየሱስ የዋሆችን ብፁዓን ብሎ ሲጠራቸው ዓለም ግን ኃይለኞችን፣ ብርቱዎችን፣ አመጸኞችን እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ ሰዎችን ብፁዓን ይላቸዋል። ኢየሱስ ደግሞ የሚያለቅሱትና የሚሰቃዩትን ሰዎች ብፁዓን ናቸው በማለት የሚጠራቸው ሲሆን፣ ምክንያቱም በሚመጣው ዓለም የሚደሰቱ እነርሱ ናቸው ይለናል። በተቃራኒው ደግሞ ዓለም የሚደሰቱ፣ የሚስቁ፣ በድሎት የሚኖሩ ስቃይን የማያዩ ብፁዓን ናቸው ይላል፡፡ “ጽድቅ እንደ እህል የሚርባቸው እንደ ውኃ የሚጠማቸው ብፁዓን ናቸው፣ ምክንያቱም ይጠግባሉና” () ይላል፡፡ ኢየሱስ ብፁዓን የሚላቸው ምድራዊ ሀብትና ግዛት የማይመኙ፣ ምድራዊ ፈተናን የሚታገሉ ሰዎችን ነው። ኢየሱስ የሚምሩ ብፁዓን ናቸው ሲል ዓለም ደግሞ ዓይን ለዓይን፣ ጥርስ ለጥርስ የሚሉ፣ በቀልን እንጂ ምሕረትን የማያውቁ፣ የሚወዱዋቸውን የሚወዱ የሚጠሉዋቸውን የሚጠሉ ብፁዓን ናቸው ይላለናል።

ኢየሱስ “ንጹ ልብ ያላቸው ብፁዓን ናቸው ምክንያቱም እግዚአብሔርን ያዩታልና” ሲል፤ ዓለም “ውጫዊውን ንጽሕና የሚወዱት፣ መልካቸው ቆንጆ የሆኑ፣ ጉልበት ያላቸው፣ መልካም ኑሮ የሚኖሩ ብፁዕን ናቸው ይለናል፣ ምክንያቱም በሰዎች ይታያሉና” በማለት ዓለም ሐሳቡን ያጠናክራል። ኢየሱስ “ሰላምን የሚወዱ ብፁዓን ናቸው፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” በማለት ሲናግር ዓለም ግን “ብፁዓን የሚባሉ ግርግር የሚፈጥሩ፣ የሚያውኩ፣ ጦርነትን የሚወዱ ናቸው” በማለት በተቃራኒው ጎራ ይሰለፋል።

ኢየሱስ “ብፁዓን የሚባሉ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ናቸው፤ ምክንያቱም መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” በማለት ሲናገር አሁንም ዓለም በተቃራኒው ጎራ በመስለፍ “ስለ ምድራዊ ሀብት የሚሰቃዩ ብፁዓን ናቸው፤ ዋጋቸውን እዚህ ያገኛሉና” በማለት ይናገራል። ኢየሱስ “ሰዎች በእኔ ምክንያት ሲረግሙአችሁና ሲያሳድዱአችሁ ያለምንም ምክንያት በእናንተ ላይ ክፉ ሲናገሯችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ ተደሰቱ ምክንያቱም ዋጋችሁ በሰማያት ከፍ ያለ ይሆናልና” በማለት ሲናገር ደግሞ ዓለም በአንጻሩ “አይደለም ሰዎች ቢወዱአችሁና ቢያከብሩአችሁ ስለእናንተ መልካም ቢናገሩ ያን ጊዜ ነው ብፁዓን የምትባሉት” ይለናል።

ኢየሱስ በሰማይ ብፁዓን ሊያደርገን ሲፈልግ ዓለም በምድር ብፁዓን ሊያደርገን ይፈልጋል፡፡ የኢየሱስ በነፍስ ብፅዕና ሊያደርገን ይፈልጋል ዓለም ግን በሥጋ ብፁዓን ሊያደርገን ይፈልጋል፡፡ የኢየሱስ ብፅዕና በብቃት፣ በትህትና፣ በድህንነት፣ በፍቅር፣ በምሕረት፣ በንጽህና፣ በየዋህነት ትገኛለች፡፡ የዓለም ብፅዕና ግን በሀብት፣ በምግብ፣ በመጠጥ፣ በጨዋታ፣ በደስታ፣ በኃይል፣ በአመጽ፣ በሁከት፣ በጦርነት የሌሎችን ሰላም በመንሳት፣ በሥጋ ፍትወት፣ ምኞት በመከተል ትገኛለች፡፡ የኢየሱስ ዘለዓለማዊ ብፅዕና ነፍሳችንን በሃሴት ሞልታ የምታስደስት ስትሆን የዓለም ብፅዕና ግን በሐሰትና በጊዜያዊ ደስታ የሰውን ልብ በማማለል ወደ ውድቀት ጐዳና የምትመራ ናት፡፡

በእውነት ብፁዓን ለመሆን ብንፈልግ ኢየሱስን እንከተል፤ እርሱ በሚሰጠው መመሪያና መንገድ ፍጹምና ዘለዓለማዊ ብፅዕና እንያዝ፡፡

19 December 2019, 11:25