ፈልግ

የዘመናዊ ስልኮች አጠቃቀም ወግ፣ የዘመናዊ ስልኮች አጠቃቀም ወግ፣ 

በናይጄሪያ፣ ጥላቻን በሚቀሰቅሱት ላይ ጠንከር ያለ ቅጣት እንዲበየንባቸው ሃሳብ ቀረበ።

በናይጄሪያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አስመልክቶ ውይይት እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህን አስመልክቶ ማሕበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሐሰት ወሬዎችን በማዳረስ የዜጎችን ሰላም በሚነሱ እና የጥላቻ ንግግሮችን በሚያሰራጩ ግለሰቦች ላይ ቅጣት እንዲበየንባቸው በማለት ሃሳብ ማቅረቡ ታውቋል። የቅጣት ብይኖቹ ሁለት ዓይነት መሆናቸውን አስታውቆ የመጀመሪያው የሞት ቅጣት ሲሆን ሁለተኛው እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት መሆኑን የተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል። በሌላ ወገን ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች “አምኔስቲ ኢንተርናሽናል”ን ጨምሮ ሌሎችም ድርጅቶች የቅጣት ብይኖቹ ተግባራዊ ከሆኑ በአገሪቱ ጠብን እንደሚቀሰቅስ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።    

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሞት ቅጣት ፍርድ ህብረተሰቡን ሊያስቆጣ ይችላል፣

በናይጄሪያ የኦዮ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ አማኑኤል አዴቶየስ ባዴጆ በመግለጫቸው የሞት ቅጣት ፍርድን ሙሉ በሙሉ ተቃውመው “የሰው ልጅ ሕይወት ክብሩ የማይጣስ፣ ቅዱስ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው” ብለዋል። ብጹዕ አቡነ አማኑኤል አክለውም የሞት ቅጣት ፍርድ ኅብረተሰቡን የበለጠ በማስቆጣት ጠብን የሚቀሰቅስ ይሆናል ብለው፣ በናይጀሪያ የዜጎችን ሰላም የሚነሱ፣ ጥላቻ የሚቀሰቅሱ ንግግሮች ለበርካታ የፖለቲካ አቀንቃኞች ሕይወት መጥፋት፣ አመጽ ለታከለበት የፖለቲካ ንግግሮች፣ ለዘር ማጥፋት ወንጀል ምክንያት ሆነው መቆየቱን የናይጄሪያ ሕግ አውጭ ክፍል ሊረዳው ይገባል ብለዋል።

በናይጄሪያ የዜጎች ስቃይ ይቁም፣

ብጹዕ አቡነ አማኑኤል አክለውም የናይጄሪያ መንግሥት ሕግ አውጭ አካል በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በከንቱ የሚሞተውን የሰው ቁጥር ለመቀነስ ጥረት ቢያደርግ የሻል ነበር ብለው ሕግን በማስከበር ረገድ የናይጀሪያ መንግሥት ከተቀሩት አጎራባች አገሮች ጋር ሲስተካከል እጅግ ወደ ኋላ መቅረቱን አስረድተዋል።

ስለሆነም ከናይጄሪያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የቀረበው ሀሳብ “ለኢፍትሃዊ የመንግሥት የሥራ አፈጻጸም መፍትሄን ማግኘት ፣ መሠረተ ልማትን ማሳደግ ፣ የሕግ የበላይነት ማስከበር ፣ የስራ እድሎችን ማመቻቸት፣ ልኑሮ ተስማሚ እና ዋስትና ያለበት አካባቢን መፍጠር መሆኑን ብጹዕ አቡነ አማኑኤል አዴቶየስ ባዴጆ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 December 2019, 15:41