ፈልግ

የኅህሳስ 12/2012 ዓ.ም የስበከተ ገና 1ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የኅህሳስ 12/2012 ዓ.ም የስበከተ ገና 1ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የኅህሳስ 12/2012 ዓ.ም የስበከተ ገና 1ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

 

1.     ዕብ 1፡1-14

2.     2ጴጥ. 3፡1-9

3.     ሐዋ. 3፡ 17-26

4.     ዬሐ. 1፡44-51

የእለቱ ቅዱስ ወንጌ

ፊልጶስም እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ ሁሉ የቤተ ሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፣ “ሙሴ በሕግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስን አግኝተነዋል” አለው። ናትናኤልም፣ “ከናዝሬት በጎ ነገር ሊወጣ ይችላልን?” አለ። ፊልጶስም፣ “መጥተህ እይ” አለው።

ኢየሱስም፣ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ፣ “እነሆ፤ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ” አለ። ናትናኤልም “እንዴት አወቅኸኝ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ፣ ገና ፊሊጶስ ሳይጠራህ አየሁህ” ሲል መለሰለት። ናትናኤልም መልሶ፣ “ረቢ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለ። ኢየሱስም፣ “ያመንኸው ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ ስላልሁህ ነውን? ገና ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ” አለው፤ ጨምሮም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይ ተከፍቶ፣ የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው።

የእለቱ አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን አቆጣጠር ዘስብከት 1ኛ ሰንበትን እናከብራለን። ዛሬም እግዚአብሔር በቤቱ ሰብስቦናል በቃሉም ያስተምረናልና የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን። በመጀመሪያው መልዕክት ሲነበብ እንደሰማነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መሆኑን ይናገራል።  ይህ አንድያ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ አስቀድሞ ስልጣንና ኃይል ሁሉ የእርሱ እንደነበረ በማቴ. 28፡ 18 ይገለፃል።

እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ የፈጠረው ከዚህ ከአንድያ ልጁ ጋር መሆኑን የዩሐንስ ወንጌል ም.1 ይናገራል፡፡ “በመጀመሪያ ቃል ነበር ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር ቃልም እግዚአብሔር ነበር፡፡  ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች እንኳን ያለ እርሱ አልሆነም፡፡”

ነቢያቶች አስቀድመው የተነበዩለት መላእክትም በፊቱ ቅዱስ፣ ቅዱስ እያሉ የሚያገለግሉት ይህንኑ አምላክ መሆኑን ዳዊት በመዝሙር 27፡7 ላይ ተናግሮታል፡፡ ስለዚህ በምድር ላይ የተፈጠረው ሁሉ የእርሱ ነው እኛንም በአምሳሉ የፈጠረን እርሱ ነው፡፡ ለዚህ ለፈጠረን ላዳነነ አምላካችን እኛም የድርሻችንን ክብርና አምልኮ ልናቀርብለት ይገባል፡፡

ለእግዚአብሔር አምላካችን የምናቀርበው ክብርና አምልኮ አይሁዳውያን ያቀርቡ እንደነበረው የሚቃጠል መስዋት ሳይሆን በእርሱ ቃል የሚኖር፣ በእርሱ ተስፋ የሚኖር የተፀፀተና ከኃጢያት የነፃ ልባችንን ሊሆን ይገባል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ዛሬ በተነበበው በእብራውያን መልእክቱ የሚያስተምረን ይህን ነው ፤ ከሁሉ አስቀድመን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪያችን መሆኑን እንድናውቅና ወደን እንድንቀበል ከዛም ለእርሱ ትዕዛዝ ተገዝተን በቃሉ እንድንኖር ለማድረግ ነው፡፡

2ኛ የጴጥ. 3፡1-9 ላይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ የሚመጣበት ጊዜ ስለዘገየ ከእንግዲህ አይመጣም የዓለም ፍጻሜ የማባል ነገር አይኖርም በማለት አንዳንድ የሐሰትን ትምህርት የሚየስተምሩ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የእርሱ መዘግየት እኛ ልጆቹ ከክፉ ሥራችን የምንመለስበትንና ከኃጢያታችን ፀድተን እንዲያገኘን በመፈለጉ ብቻ ነው፡፡

ደጋጋመን በምንሰራው ኃጢያታችን ምክንያት የቆሸሸውን ልባችንን ሕሊናችንን እንድናፀዳ ጊዜ ስለሰጠን ብቻ ነው፡፡

ጊዜና ቦታ በእኛ በሰዎች አመለካከት እንጂ እግዚአብሔር በጊዜ አይወሰንም፣ እግዜአብሔር መጀመሪያና መጨረሻ የለውም፣ እግዚአብሔር በቦታ አይወሰንም፤

ስለዚህ ነው በቁ.8 ላይ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን አንደ ሺ ዓመት ሺ ዓመት ደግሞ እንደ አንድ ቀን ይቆጠራል የሚለው፡፡

የክርስቶስ መምጣት ለእኛ የዘገየ ቢመስለንም ጥቅሙ ግን ለእኛው ነው በደንብ ተዘጋጅተን ከኃጢያታችን ጸድተን የዘለዓለም ሕይወት ወራሾች በመሆን የዘለዓለዊ ደስታን እንድንገኝ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰዎች አንድ እንኳ እንዲጠፋ አይፈልገም ለዚህም ጊዜ ሰጥቶናል፡፡  በዚህ ጊዜ ውስጥ እንድንዘጋጅ ያስፈልጋል፣፣  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደንገት በሚመጣበት ጊዜ ለመዘጋጀት ጊዜ አይኖርም፡፡

የኖህ መርከብ በሩ ከተዘጋ በኃላ እንዳልተከፈተና በመርከቡ ያልገቡት ሁሉ እንደጠፉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንገት በሚመጣበትም ጊዜ እኛም እንዳንጠፋ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠን ጊዜ ውስጥ መዘጋጀቱ ተገቢ ነው፡፡ በዮሐንስ ወንጌል 1፡44-51  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድርያስን እና ስምኦንን እንደጠራ ሁሉ ፊሊጶስንና ናትናኤልንም ጠራቸው የእርሱን ሕይወት መስካሪ አደረጋቸው፡፡

ይህ የሚመሰክሩት ሕይወት ምንድን ነው?  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወርዶ ሰው ሆኖ ስለ እኛ መዳን ሲል ተሰቃይቶ ተሰቅሎ ሞቶ ተቀብሮ በ3ኛው ቀን ከሙታን በመነሳት አንዳዳነን ከኃጢያት ቀንበር ነፃ እንደወጣን የመሰክራሉ፡፡ እነዚህ ሐዋርያቶች ይህንን ምስክርነት ሲሰጡ በሕይወታቸው ብዙ መከራና ሥቃይ ደርሶባቸዋል፡ አብዛኞቹም ሰማዕታት ሆነዋል፡፡ ዛሬም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ጥሪ ለእያንዳዳችን ይልካል ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድንመሰክር ይፈልጋል፡፡

ምን አልባት ልክ እንደጥንቱ ክርስቲያኖችና ነቢያቶች የደም ምሥክርነት ባይሆንም የሕይወት ምሥክርነት እንዲኖረን ይፈልጋል፡፡ እንደ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንድንኖር ይፈልጋል፡፡ በዚሁ ወንጌል ላይ ናትናኤል ወደ ክርስቶስ በቀረበ ጊዜ ጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እርሱ ምስክርነቱን ሰቷል “እነሆ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ” ቁ47፣ ይህም የሚያሳየን እግዚአብሔር ምንም እንኳን ደካሞች ብንሆንም የልብ ቅንነት ያላቸውን ሰዎች ይወዳል፣ ለተንኮል ራሳቸውን የማያዘጋጁትን ሰዎች ያቀርባል፣ ለንስሃ የተዘጋጁትን ልቦች የፈውሳል፣ ምስክሮቹም ያደርጋቸዋል ስለዚህ እኛም ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ እንዳለው እንደ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በእግዚአብሔር ጸጋ በመታመን እንደ እርሱ ፈቃድ ለመኖርና ለመመላለስ ምስክሮቹም ለመሆን እንድችል በረከቱን በልባችን ይሙላልን፡፡

እመቤታችን ኪዳነ ምሕረት የክርስቲያኖች ረዳት የሆነች ጸጋና በረከቱን ከልጇ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ታሰጠን፤የሰማነውን በልባችን ያኑርልን፡፡

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን 

 

22 December 2019, 11:23