ፈልግ

የኅዳር 28/2012 ዓ.ም ዘመፃጉዕ (ዘአስተምህሮ 4ኛ) እለተ ሰንበት አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.     1ኛ ቆሮ 2፡1-16

2.    1ዮሐ 5፡1-5

3.     ሐዋ. 5፡34-42

4.    ዩሐ. 9፡1-14

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ፈወሰ

በመንገድ ሲያልፍም ከተወለደ ጀምሮ ዐይነ ስውር የሆነ ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ረቢ፤ ይህ ሰው ዐይነ ስውር ሆኖ እንዲወለድ ኀጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ራሱ ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እርሱ ወይም ወላጆቹ ኀጢአት አልሠሩም፤ ይህ የሆነው ግን የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ ሕይወት እንዲገለጥ ነው። ቀን ሳለ፣ የላከኝን ሥራ መሥራት አለብን፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል፤ በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ።”

ይህን ካለ በኋላ፣ በምድር ላይ እንትፍ ብሎ በምራቁ ጭቃ አበጀ፤ የሰውየውንም ዐይን ቀባና፣ “ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው፤ ሰሊሆም ማለት ‘የተላከ’ ማለት ነው። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም ተመልሶ መጣ። ጎረቤቶቹና ከዚህ ቀደም ብሎ ሲለምን ያዩት ሰዎች፣ “ይህ ሰው ተቀምጦ ሲለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። አንዳንዶቹም፣ “በርግጥ እርሱ ነው” አሉ። ሌሎችም፣ “ይመስለዋል እንጂ እርሱ አይደለም” አሉ። እርሱ ግን፣ “እኔው ነኝ” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም፣ “ኢየሱስ የሚሉት ሰው ጭቃ አድርጎ ዐይኔን ቀባኝ፤ ወደ ሰሊሆም ሄጄ እንድታጠብም ነገረኝ፤ ሄጄ ታጠብሁ፤ ማየትም ቻልሁ” ሲል መለሰ።

እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ያ ሰው የት አለ?” አሉት። እርሱም፣ “እኔ አላውቅም” አለ።

ፈሪሳውያን ሰውየው እንዴት እንደ ተፈወሰ ማጣራት ቀጠሉ። እነርሱም ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ኢየሱስ ጭቃ የሠራበት፣ የሰውየውንም ዐይን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበር። ስለዚህ ፈሪሳውያንም እንዴት ማየት እንደ ቻለ ጠየቁት። ሰውየውም፣ “እርሱ ዐይኔን ጭቃ ቀባኝ፤ እኔም ታጠብሁ፤ ይኸው አያለሁ” አላቸው።

ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ፣ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር፣ ከእግዚአብሔር አይደለም” አሉ። ሌሎች ግን፣ “ኀጢአተኛ፣ እንዲህ ያሉትን ታምራዊ ምልክቶች እንዴት ሊያደርግ ይችላል?” አሉ። በመካከላቸውም አለመስማማት ተፈጠረ። ስለዚህ፣ ዐይነ ስውር ወደ ነበረው ሰው ተመልሰው፣ “ዐይንህን ስለ ከፈተው ሰው፣ እንግዲህ አንተ ምን ትላለህ?” አሉት።

ሰውየውም፣ “እርሱ ነቢይ ነው” አለ። አይሁድ ወደ ወላጆቹ ልከው እስኪያስ ጠሯቸው ድረስ፣ ሰውየው ዐይነ ስውር እንደ ነበረና እንዳየ አላመኑም ነበር። እነርሱም፣ “ዐይነ ስውር ሆኖ ተወልዶአል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” አሏቸው።

ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ልጃችን መሆኑንና ዐይነ ስውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤  አሁን ግን እንዴት ማየት እንደቻለና ዐይኖቹን ማን እንደ ከፈተለት እኛ አናውቅም። ሙሉ ሰው ስለ ሆነ፣ ስለ ራሱ መናገር ይችላልና እርሱን ጠይቁት።” ኢየሱስን፣ ክርስቶስ ነው ብሎ የመሰከረ ሁሉ ከምኲራብ እንዲባረር አይሁድ አስቀድመው ወስነው ስለ ነበር፣ ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁድን ፈርተው ነው። ስለዚህ ወላጆቹ፣ “ሙሉ ሰው ስለ ሆነ እርሱን ጠይቁት” አሉ። ዐይነ ስውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው፣ “አንተ ሰው፤ እግዚአብሔርን አክብር፤ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት። እርሱም፣ “ኀጢአተኛ መሆኑን እኔ አላውቅም፤ ነገር ግን ዐይነ ስውር እንደ ነበርሁ፤ አሁን ግን እንደማይ ይህን አንድ ነገር ዐውቃለሁ” አለ።

እነርሱም፣ “ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዐይንህን ከፈተ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ፤ አላዳመጣችሁኝም፤ ለምን እንደ ገና መስማት ፈለጋችሁ? እናንተም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁ?” አለ። ከዚህ በኋላ በእርሱ ላይ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ አሉት፤ “የዚህ ሰው ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛስ የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን! እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደ መጣ እንኳ አናውቅም።”

ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እናንተ ከየት እንደ መጣ አለማወቃችሁ የሚያስደንቅ ነው፤ ይሁን እንጂ እርሱ ዐይኖቼን ከፈተልኝ። እግዚአብሔር የሚሰማው፣ የሚፈራውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን እንጂ፣ ኀጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዐይን የከፈተ አለ ሲባል፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ማንም ሰምቶ አያውቅም። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ይህን ማድረግ ባልቻለ ነበር።”

እነርሱም፣ “ሁለንተናህ በኀጢአት ተነክሮ የተወለድህ፣ አንተ እኛን ለማስተማር እንዴት ትደፍራለህ?” ሲሉ መለሱለት፤ አባረሩትም።

መንፈሳዊ ዕውርነት

ኢየሱስም ሰውየውን እንዳባረሩት ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ፣ “በሰው ልጅ ታምታምናለ ህን?” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታዬ፤ አምንበት ዘንድ እርሱ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አይተኸዋል፤ አሁንም ከአንተ ጋር የሚነጋገረው እርሱ ነው” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አምናለሁ” አለ፤ ሰገደለትም።ኢየሱስም፣ “ዕውሮች እንዲያዩ፣ የሚያዩም እንዲታወሩ፣ ለፍርድ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ” አለ። ከእርሱ ጋር ከነበሩት ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው፣ “ምን ማለትህ ነው? ታዲያ እኛም ዕውሮች መሆናችን ነው?” አሉት። ኢየሱስም፣ “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኀጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ስለምትሉ፣ ኀጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል” አላቸው።

የእለቱ አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን አቆጣጠር ዘመፃጕዕ ወይም ዘአስተምሕሮ 4ኛ ሰንበትን እናከብራለን። በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተነበቡት ንባባት አማካኝነት ለእያንዳንዳችን የሚሆን የሕይወት ስንቅ ይሰጠናል የሕይወት ምግብ ይመግበናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደ ወትሮው ዛሬም ወደ እያንዳንዳችን ይሠርፃል ፤ እኛም ወደ እኛ የመጣውን ቃል ሰሚዎች ብቻ ሳንሆን በተግባር እንድናውለው ያስፈልጋል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያ መልእክቱ “ከጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን አምነቱን ለእነዝህ ለቆሮንጦስ ሰዎች በሙሉ እምነት ይሰብክላቸው” እንደ ነበር ይናገራል፡፡ ስለዚህ ዛሬ በአጭሩ ንጉሥ የሆነ ክርስቶስ እምነታችንን በተግባር አንድናውለው ይጠይቀናል፡፡

እነዚህ የቆሮንቶስ ሰዎች ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ስለ ክርስትና እምነት ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፣ ነገር ግን እርሱ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሚናገረው ቃል ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ሥራውን ይሰራ ነበር፡፡

ይህ መንፈስ ቅዱስ ነው የሰዎቹን ልብ እያቀሰቀሰ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑና እንዲጠመቁ ሆነ፡፡ ሰው በእግዚአብሔር መንፈስ ካልተመራ በስተቀር የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱም ቢመጣ እንኳን ምን እንደሆነ ሊረዳሙ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ወደ ምድር ሲመጣ የእግዚአብሔር አብ ምሥጢር መሙላት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተገልጧል፡፡

ይህ የቅድስት ስላሴ ሦስተኛ አካል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በቤታችን፣ በእያንዳንዳችን ውስጥ አድሮ የእግዚአብሔርን ቃል እንድንረዳና በቃሉም መሠረት እንድንኖር ይጋብዘናል፡፡

በእግዚአብሔር መንፈስ የምንመራ ከሆንን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በውስጣችን ያድራል፡፡  የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ደግሞ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለፀው “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣በጐነት፣ እምነት፣ የዋህነተ፣ ራስን መግዛት” (በገላ. 5፡22 ) ናቸው ይላል፡፡

ስለዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችን እንዲያድር እንደ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሙሉ እምነት ራሳችንን ክፍት እናድርግለት፡፡ ቅዱስ መንፈስ በውስጣችን ሲያድር ሁሉንም ነገር በሙላት ይገልፅልናል፣ እኛም ልክ እንደ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ “በመካከላችሁ ሳለው ከእየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበር” ብሎ እንደተናገረው እኛም ይህ መንፈስ በውስጣችን ሲያድር አካሄዳችን፣ አስተሳሰባችን፣ እንቅስቃሴያችን ሁሉ በእግዚአብሔር መንፈስ የተመራ ይሆንልናል ፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ዩሐንስ በመልዕክቱ የዓለምን ፈተና ሁሉ ለማሸነፍ የእግዚአብሔርንም ትዕዛዝ ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር መንፈስ መወለድ እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡

ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለሚባል የሙሴ ሕግ መምህር የተናገረው ቃሉ ነው “እውነት እውነት እልሃለው ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” (ዬሐ.3፡5) እንዳለው ይሆናል ማለት ነው።

ቅዱስ ሐዋርያው ዩሐንስ በመቀጠል እግዚአብሔርን መውደድና ባልንጀራን መውደድ አንድ መሆናቸውን ይናገራል፡፡  እግዚአብሔርንና ባልንጀራን መውደድ ማለት በአጭሩ ከራስ ወዳድነት ሥሜት ነፃ መሆን ማለት ነው፣ ለራሴ ብቻ ከሚለው ሐሳብ ወጥተን ለሌሎችም ማሠብ መቻል ማለት ነው፣ ለራሴ ብቻ ከሚለው ሐሳብ ወጥተን ሌሎችም እኔ የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ እንደሚያስፈልጋችው መገንዘብ ማለት ነው ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን ወዳለው የሚል ሰው፣ ባልንጀራዬን እወዳለው የሚል ሰው፣ ከራስ ወዳድነት ስሜት የተላቀቀ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ሌሎችን በምንችለው አቅም ስንረዳ በእርግጥም እግዚአብሔርን በፍጹም ኃይላችን፣ በፍጹም ልባችን እንደምንወድ እናረጋግጣለን ማለት ነው፡፡ የዮሐንስ ወንጌልም ስለ አንድ ዓይነ ስውር ሆኖ ስለተወለደ ሰው ይናገራል፡፡  ይህ ሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው በሙሉ እምነት ሄዶ በሰሊሆም መጠመቂየ ታጠበ ተፈወሰም፡፡

ከዛም በኋላ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሰከረ “እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን ሰው እግዚአብሔርን ይሰማዋል” በማለት መመስከር ጀመረ። እኛም ዛሬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚሰጠን ቃል፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በእምነት ከተጓዝን እግዚአብሔር በእርግጥም ጸሎታችንን ይሰማል፣ ሐሳባችንን ሁሉ ይሞላልናል፡፡  ስለዚህ ዘወትር በእግዚአብሔር መንፈስ ለመመላለስ አንደ እርሱ ፈቃድ ለመመላለስ ጥረት እናድርግ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ተአምር በመፈጸሙ የዓለም ብርሃን መሆኑን አስመስክሩዋል፣ እያንዳንዳችን የተፈጠርነው እግዚኣብሔርን እንድናውቀው ነው፣ ነገር ግን በኃጢያታችን ምክንያት ከልጅነታችን ጀምሮ ዓይናችን ታውሩዋል፣ አዲስ የእምነት ብርሃን ያስፈልገናል፣ ይህንንም ብርሃን የሚሰጠን ኢየሱስ ብቻ ነው።በእዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ውስጥ የተጠቀሰው እና የዓይኑን ብርሃኑ መልሶ የተጎናጸፈው ሰው ለክርስቶስ የማዳን ሚስጢር  ራሱን ክፍት አድርጎ ነበር። ኢየሱስ የዓለም ብርሃን መሆኑን ለመረዳት በሚያዳግተን ወቅት ሁሉ “ይህ ዓይነ ስውር” የነበረው ሰው ይህንን እውነታ እንድንረዳ ያግዘናል፣ በተለይም ደግሞ በዙሪያችን የሚንጨላጨሉ ጥቃቅን ብርሃናትን እንዳንመኝ ይረዳናል።

እያንዳንዳችን በጥምቀት አማካይነት የክርስቶስ ብርሃን “በርቶልናል” በዚህም ምክንያት እንደ ብርሃን ልጆች ሆነን ራሳችንን እንድንመራ ተጠርተናል። እውነተኛ የሆነ ብርሃን መያዝ እና በብርሃን መጓዝ ምን ማለት ነው? ይህም ማለት በቅድሚያ ሐሰት የሆኑ ብርሃናትን ማስወገድ ማለት ነው። ሌላኛው ሐሰተኛ ብርሃን የሚባለው ደግሞ ራስ ወዳድነት ነው፣ ሰዎችን እና ነገሮችን ለእኛ ጥቅም፣ ደስታ እና ክብር ብቻ እንዲመች አድርገን በምንገመግምበት ወቅቶች ሁሉ ከእነዚህ ነገሮች ጋር ሐቀኛ የሆነ ግንኙነትና ሁኔታ መፍጠር አንችልም። “እግዚአብሔር ከኃጥአን ይርቃል የፃድቃንን ጽሎት ግን ይሰማል” (መ. ምሳ 15፡29) ይላል።  እኛም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንድንመላለስ፣ ጸሎታችንን፣ እንዲሰማንና ሐሳባችንን እንዲሞላልን የጽድቅን ጉዞ እንጀምር  ኃጢአትንና የኃጢአትን ዝንባሌ ሁሉ ልክ በሰሊሆም መጠመቂየ ታጥቦ እንደተፈወሰው ዓይነ ስውር የነበረው ሰው እንዳደርገው ሁሉ እኛም በምስጢ ንስሃ ታጥበን እንፈወስ፡፡ ለዚህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት የሆነች ከልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ፀጋና በረከት ታማልደን የሰማነውን በልባችን ያሳድርልን፡፡

ምንጭ፡ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛ ክፍል አገልግሎት

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

07 December 2019, 17:52