ፈልግ

እግዚአብሔር ፈጣሪያችን አምላካችን ስለሆነ እንድናፈቅረው አዞናል። እግዚአብሔር ፈጣሪያችን አምላካችን ስለሆነ እንድናፈቅረው አዞናል።  

የእግዚአብሔር ፍቅር

እግዚአብሔር በምድረ በዳ ለእስራኤላውያን መጀመሪያ “እኔ ግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ አምላካችሁ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑራችሁ፣ ለሌሎች አማልክት አትስገዱ አላቸው” (ዘጸ 20፣ 1-2)። በታማኝ አገልጋዩ በሙሴ አድርጐ እንደፈጣሪያቸውና አምላካቸው አድርገው እንዲወድዱት አዘዛቸው፡፡ “በምትገቡባት መሬት ልትጠነቀቁ የሚገባችሁ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ይህ ነው […] ስማ እስራእል አምላክህን በመሉ ልብህ፣ በመሉ ነፍስህ፣ በሙሉ ኃይልህ ውደደው” (ዘዳ. 6፣1-5)። ኢየሱስ ለእኛ ለተከታዮቹ ክርስቲያኖች ይህን የአምላክን ፍቅር የያዘ ትዕዛዝ ደገመልን፡፡ ከጸሐፊዎች አንዱ “መምህር ሆይ በኦሪት ከሁሉ የሚበልጥ ትዕዛዝ የትኛው ነው?” ብሎ ኢየሱስን ሲጠይቀው እርሱም እንዲህ ሲል መለሰለት “እግዚአብሔር አምላክህ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያ ትዕዛዝ ይህ ነው” (ማቴ. 22፣36-38፣ ማር. 12፣28-30) በማለት መለሰለት። እግዚአብሔርን ልንወደው ይገባናል፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ እርሱ ስላዘዘን፣ በመቀጠል እርሱ ፍቅር ስለሚገባው፣ ሦስተኛ ደግሞ እርሱ ሰለሚያፈቅረን የሚጠቅመን የሰጠንን ትዕዛዝ ተግባራዊ ስናደርግ በመሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ በአፍ ብቻ ሳይሆን በተግባር ማሳየት ነው፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

1.     እንድንወደው አዞናል፡ እግዚአብሔር ፈጣሪያችን አምላካችን ስለሆነ እንድናፈቅረው አዞናል። እንደፈጣሪያችን ጌታችን የምናየው ከሆነ ይህን “ውደዱኝ” የሚል ትዕዛዝን በተግባር ማሳየት አለብን፣ ልንወደውም ይገባናል።

2.     ፍቅር ይገባዋል፡ እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ እርሱ ራሱ ፍቅር ነው፣ ሕይወት ሁሉ ከእርሱ የመጣ ነው፡ትልቅነቱ፣ ኃያልነቱ፣ ዕውቀቱ፣ ቅንነቱ፣ እውነቱ፣ ደግነቱ ወዘተ… ሊገመት አይቻልም፡፡ ይህ ነው ተብሎ በአሃዝ አይለካም። በእርሱ ሁሉ መልካምና ፍጹም ነው። መልካምና የፍጹም ነገርን ሁሉ የምንወድ ከሆነ በይበልጥ የመልካምና የፍጹም ነገር ምንጭ የሆነ እግዚአብሔርን ልንወደው ይገባናል

3.     እግዚአብሔርን ልንወደው ይገባናል ምክንያቱም ከጥንት ጀምሮ እርሱ ስለወደደን፡ ቅዱስ ዮሐንስ “እግዚአብሔር አስቀድሞ ስላፈቀረን እኛም እናፈቅረዋለን” (1ኛ ዮሐ. 4፣19) እያለ ያበረታታናል። እግዚአብሔር አኛን አስቀድሞ ወደደን፡፡ ሰዎችን ሲፈጥረን ከመላእክት በቀር ከሌሎች ፍጥረቶች ከፍ አደረገን ሥጋዊና መንፈሳዊ ጸጋንና ምድራዊ ሐብትን ሸልሞ በአምሳሉ በመልኩ ፈጠረን፡፡ በኃጢአታችን ከቀጣን በኋላ ከእርሱ ራቅን ነገር ግን እርሱ ፈጽሞ አልጨከነብንም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ማረን ምሕረቱን አወረደልን፣ መድኃኒት ላከልን፣ ከእኛ ጋር እንደገና እርቅ ፈጸመ፣ ልዩ ጸጋ ሰጠን እንደዚህ አድርጐ ያፈቀረንን እግዚአብሔር ልንወደው ይገባል፡፡

ፍቅር በፍቅር ነው የሚካካሰው፣ እንበርታ እርሱ አስቀድሞ እንደወደደን ልንወደው የሚገባን ብቻ ሳይሆን ከሁሉ አብልጠን በሙሉ ልባችን እንድንወደው ያስፈልጋል። ከልባችን የምንወደው ከሆነ ደግሞ በተግባር እንጂ በንግግር አይደለም ፍቅሩን መግለጽ የሚገባን። እውነተኛ ፍቅር የሚገለጸው የአምላክን ትዕዛዝ በመጠበቅ ብቻ ነው። ኢየሱስ “የምትወዱኝ ከሆናችሁ ትዕዛዞቼን ጠብቁ” (ዮሐ. 14፣15) ይለናል።

ወዳጆቹ ተብለን ከፈቃዱና ከትእዛዞቹ የምንወጣ ከሆንን ሁሉም ነገር ከንቱ ስለሚሆንብን በጥሞና ረጋ ብለን ራሳችንን እንመርምር፤ ብዙ ጊዜ ለእግዚአብሔር እውነተኛና ሙሉ ፍቅር አናሳይም፡፡ እርሱን ከመውደድ ራሳችንን፣ ሰውን፣ የዚህን ዓለም ሀብት፣ ደስታና ምቾት እንዲሁም ፍትወት አስበልጠን እንወዳለን፡፡ ስለራሳችንና ስለሌሎች ስንት መከራና ስቃይ እንጋፈጣለን; እግዚአብሔርን በእውነት የምንወደው ብንሆን በፈተና ጊዜ እንክደውም፣ በኃጢአታችን አንበድለውም፣ አናሳዝነውም ነበር፡፡ በልባችን የምንወደው ብንሆን ፈቃዱን ልንፈጽምና ዘወትር ልናስደስተው እንተጋ ነበር፤ ቅዱሳን ሰማዕታት እግዚአብሔርን በሙሉ ልባቸው አፈቀሩት በልባቸው ከእርሱ ፍቅር የሚበልጥ የዓለማዊ ነገሮች ፍቅር  አልነበራቸውም፡፡

ሰማዕታት በሙሉ ከልባቸው ያፈቅሩት ስለነበር ሕይወታቸውን ስለእርሱ አሳልፈው ሰጡ፡፡ ቅዱሳን ደግሞ በእውነት ያፈቅሩት ስለነበር ስለፍቅሩ ማናቸውንም ስቃይና መከራ ሲቀበሉ ደስተኞች ነበሩ፡፡ “በኃጢአት እግዚአብሔርን ከማሳዘን ፍቅሩን ከማጣት ሞት ይሻላል” ይሉ ነበር፡፡ አኛ ደግሞ የእነሱን ፈለግ ተከትለን እግዚአብሔርን ከሁሉ አስበልጠን በሙሉ ልባችን ልናፈቅረው ቁርጥ ፈቃድ እናድርግ።

11 December 2019, 13:10